Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥቂት ስለ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት

0 378

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጥቂት ስለ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት

                                                       ዘአማን በላይ

የሀገራችንን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ማየት የማይሹ ፅንፈኞች የራሳቸው የሆነ አጀንዳ የላቸውም። አዲስ አበቤዎች እንደሚሉት “በአቦ ሰጥ” (በደመ ነፍስ) የሚጓዙ ናቸው።   ፅንፈኞቹ ስራቸው እዚህ ሀገር ውስጥ አንድ ነገር ከተፈፀም እርሱን ይዞ መጮህ፣ መለፈፍና መደስኮር ነው። የኢትዮጵያን በጎ ከማይመኙት የውጭ አዝማቾቻቸው የሚቀበሉትንና በባዶ ቅል የሚመሰለውን የቁራ ጩኸታቸውን ጥሩንባ በየማህበራዊ ሚዲያዎች ይነፋሉ፤ ያስነፋሉ። የአሉባልታ ፈረስ ነጂዎች ሆነው ይዳክራሉ። የአሉባልታ መናጆ ፈረሳቸው እስከ የት ድረስ እንደሚሄድ እንኳን በቅጡ የማያውቁ ‘የተረት- ዓለም’ ጋላቢዎች ናቸው።  

ግና የሚያስተጋቡት አሉባልታዊ ጩኸት ሀገራችን ውስጥ የተከናወነን ነገር ገልብጦ በማጦዝ ህዝብን ለማሳሳት የመሞከር ተልዕኮን ያነገበ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ አዋጅ፣ ህግና ዕቅድ በተባለ ቁጥር እነርሱን እንደሚመለከታቸውና ፍላጎታቸውን ሁሉ መና የሚያስቀርባቸው መሆኑን ስለሚያውቁ መያዣና መገነዣ ያጣሉ። ይራወጣሉ። ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን የጥላቻ አታሞ ይደልቃሉ። ያስደልቃሉ። ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ያወጣውን ዕቅድ አጣሞ በማቅረብ ህዝብን ለማሳሳት እያደረጉት ያለው ጥረት የዚህ ተግባራቸው ሁነኛ አስረጅ ነው። እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ የምክር ቤቱን አጠቃላይ ገፅታና ያወጣውን የጋራ ዕቅድ በጥቂቱ በመቃኘት ለውድ አንባቢዎቼ ሃቁን ለማሳየት እሞክራለሁ። መልካም ንባብ።…

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 55 (1) ላይ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ለፌዴራሉ መንግስት በተሰጠው የስልጣን ክልል መሰረት ህጎችን ማውጣት እንደሚችል ደንግጓል። በዚህ መሰረትም “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት” በአዋጅ ቁጥር 257/1994 ህግ ሆኖ በፓርላማው እንዲወጣ ተደርጓል። ይህ አዋጅ ህግ ሆኖ ከፀናበት ከጥቅምት 1994 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በስራ ላይ የዋለ ነው። የስራ ላይ  ቆይታው ከ16 ዓመት በላይ መሆኑ ነው።

ምክር ቤቱ በአዋጅ እንዲቋቋም የተደረገው፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሚከሰቱም ሆነ አመጣጣቸው ሊታይ ከሚችል አደጋዎችና ፈተናዎች በመጠበቅ ረገድ ተጨማሪ ዋስትና ሊያስገኝ የሚችል አሰራር መቀየስ በማስፈለጉ ነው።  

አዋጁ እንደሚያስረዳው የምክር ቤቱ ተግባራት ሶስት ናቸው። አንደኛው፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት የሚመለከቱ የውስጥ፣ የውጭና የመከላከያ ፖሊሲዎች እንዲጣጣሙ በማድረግና በሚገባ ተግባራዊ መሆናቸውን በመከታተል ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማማከር ስራን ማከናወን ነው።

ሁለተኛው ተግባር ሶስት ገዳዩችን የያዘ ነው። እነርሱም ለሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት የስጋት ምንጭ የሆኑ ሁኔታዎችን በመገምገም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ርምጃዎች ሃሳብ ማቅረብ፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወዱ ርምጃዎችን የሚመለከቱ የአፈፃፀም መመሪያዎችን ማመንጨት እና የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት በሚነካ ማናቸውም ጉዳይ ላይ መምከር ናቸው።  

ሶስተኛው ተግባር ደግሞ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 93 መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲደነገግም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ የሚወሰኑ ተግባሮችን ማከናወን ነው።

በአዋጁ ላይ እንደተመለከተው፤ ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ሲሆን፤  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ አካላትን ያካተተ አባላት አሉት። ያም ሆኖ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ የምክር ቤት አባላትን የመሰየምና ማንኛውም ሰው ሙያዊ ምክር ለመስጠት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በአስረጅነት እንዲገኝ መፍቀድ እንደሚችሉ አዋጁ ያስረዳል። ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አዝማማሚያዎች ካሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማናቸውም ጊዜ ስብሰባ መጥራት ይችላሉ።

ታዲያ ይህን አዋጅ ተመርኩዞ ከመሰንበቻው በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእስረጅነት አሊያም ይመለከታቸዋል ያሏቸውን አባላት ሰብስበው በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መምከራቸውና የጋራ ዕቅድ ማውጣታቸው ይታወሳል።

በዚህ መሰረትም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሃይሎች እንዲሁም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አዛዦች በውይይቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርገው ለሀገሪቱ ይበጃል ያሉትን የጋራ ዕቅድ ነድፈዋል። በዕቅዱ ላይም የጋራ መግባባት ተይዟል። ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴም ተገብቷል።

ይህ ዕቅድ ሀገራችን ለአንድ ዓመት የምትመራበት ወጥ የሰላምና የፀጥታ ሰነድ ሲሆን፤ አሁን ያለውን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የወጣ ነው።ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ከአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በስተቀር የሀገራችን ሰላምና መረጋጋቱ ጥሩ የሚባል ቢሆንም፤ በምክር ቤቱ የተተለመውን ዕቅድ ገቢራዊ ለማድረግ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ስራው ይከናወናል። ይህም ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት አመጣጣቸው ሊታይ ከሚችል አደጋዎችና ፈተናዎች በመጠበቅ ረገድ ተጨማሪ ዋስትና ሊያስገኝ የሚችል ነው።

ርግጥ የሀገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ እንዳይደናቀፍ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ያዘጋጀው ዕቅድ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑ አያጠያይቅም። ምክንያቱም እንደ እኛ ያለ በሁሉም መስኮች በአፍላ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚገኝ ሀገር በተለያዩ ሰንካላ አስተሳሰቦች ምክንያት ልማቱ መደናቀፍ ስለማይኖርበት ነው። በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኝ ትንሽ ቦታም ቢሆን የሚከሰቱ አላስፈላጊ ንትርኮችና የሰላም እጦቶች፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እውን ለማድረግ የሚሹትን የልማት ዕድገት በመጎተት አሉታዊ ሚና መጫወታቸው አይቀርም።

ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት “ከልማታችን አንድም ጋት ወደ ኋላ የሚመለስን ሁሉ የሀገራችን ጠላት ነው” ማለታቸው ይታወቃል። ይህ አባባላቸው ሀገራችን ድህነትን ለመቅረፍ በምታደርገው ጥረት አሜኬላ እሾህ ሆኖ የሚሰለፍ ማንኛውም አካል ኢትዮጵያ ጠላቷን ድል እንዳትነሳ የሚያደርግ እርሱም በጠላትነት የሚፈረጅ መሆኑን ለመግለፅ ነው። ከዚህ አኳያ የኤርትራ መንግስትና በእርሱ ያለቀ ሳንባ የሚተነፍሱ እንደ ግንቦት ሰባትና ኦነግ የመሳሰሉ እንዲሁም ለባዕዳን አድረው የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ የሚሹ ቅጥረኞች በዚህ ረገድ የሚፈረጁ ናቸው።

ርግጥ ከጀመርነው ሁለንተናዊ ዕድገት ስንዝርም ያህል ቢሆን ሊጎትተን የሚችልን ክስተት አዝማሚያውን በመመልከት ከስር ከስር መፍታት ሀገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ይህ ኃላፊነትና ግዴታ የተጣለው ደግሞ በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ላይ በመሆኑ ዕቅድ ወጥቶ በጋራ ተግባራዊ መደረጉ ወቅታዊ ርምጃነት አጠያያቂ አይሆንም።

በመሆኑም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የሚመራው ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት፤ በሀገሪቱ የሚከሰቱ የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ እንዲሁም ግጭቶችን ለመፍታት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ አንዳንድ ፅንፈኞችና አጫፋሪዎቻቸው እንደሚሉት “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሀገሪቱ ውስጥ እውን እንዲሆን የሚያስችል ነባራዊ የፀጥታ ችግር ባለመኖሩ ነው።

ምክር ቤቱም ቢሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማውጣት ስልጣን የለውም። ምክንያቱም በ1994 ዓ.ም በወጣው የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በሚደነገግበት ወቅት፤ የደህንነት ምክር ቤቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሰረት የሚወሰኑ ተግባሮችን የመፈፀም ተግባር ብቻ ያለው በመሆኑ ነው።

የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ አዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተግባሩን ለመወጣት ሲንቀሳቀስ ሙሉ ኃላፊትን ይዞ ነው። ይኸውም ምክር ቤቱ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት በሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ላይ በመምከር ርምጃ መውሰድ ይችላል። ይህ የሚደረገውም ከምክር ቤቱ ሚና ጋር ተያይዞ ነው—በሀገሪቱ ላይ የሚፈጠሩ ወይም ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችንና ስጋቶችን በመቅረፍ በአስተማማኝ ሰላም ውስጥ ሀገሪቱ የጀመረችው የልማት ጉዞ እንዳይደናቀፍ ለማድረግ።

ታዲያ ምክር ቤቱ በያዘው ዕቅድ ላይ ምናልባት እጅግ በጣም ትንሽ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ውስን ለሆኑ ጊዜያት ሊገደቡ ይችላሉ። ይህም መብቶቹን ለመገደብ ምክንያት የሆኑት መሰረታዊ ጉዳዩች ሲቀረፍ በፍጥነት የሚነሳ ይሆናል። እናም ሁኔታው ፅንፈኞቹ በአሉባልታ እንደሚያስወሩት “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ጋር ምንም ዓይነት ተዛምዶ የለውም። አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሀገራችንን ወደ ተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስገባት አንዳችም ምክንያት የለምና።

የምክር ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚገልፀው የስጋት ምንጭ የሆኑ ጉዳዩች ተለይተዋል። በእነዚህ ጉዳዩች ዙሪያ ሁኔታዎች ይገመገማሉ። ማናቸውም የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ተግባራት ያለ ህዝብ ተሳትፎ ስለማይሳካ ቢደቱ ህዝቡ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ “ምክር ቤቱ ችግሮችን ለመፍታት ህዝቡን በዋናነት በማሳተፍ ላይ አተኩሮ ይሰራል፤ ተከታታይ የህዝብ ውይይቶችም ይካሄዳሉ” ያሉት እውነታ ይህንኑ የሚያመላክት ነው። ርግጥ ህዝብ በቀጥተኛ ባለቤትነት ተሳታፊ የሚሆንበት ማንኛውም ዕቅድ እጅግ አጥጋቢ ውጤት እንደሚያመጣ ግልፅ ነው። የምክር ቤቱም የሀገርን ሰላም ከሚያውኩ አዝማሚያዎች፣ ፈተናዎችና አደጋዎች ለመታደግ የተለመው ዕቅድ ህዝብን ያቀፈ በመሆኑ ስኬታማነቱ አጠያያቂ አይሆንም።

ታዲያ ይህ ይሆን ዘንድ፤ የምክር ቤቱ ዓላማ የሀገራችንን ሰላም በማረጋገጥ የተከሰቱና የሚከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍ የስጋት ምንጮችን ማድረቅ መሆኑን በመገንዘብ፤ ማንኛውም የሀገሩን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚሻ ዜጋ ሁሉ ከምክር ቤቱ ዕቅድ ጎን በመቆም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል እላለሁ።         

 

 

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy