Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌስቡክ፤ የቀለጠው መንደር

0 502

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌስቡክ፤ የቀለጠው መንደር

                                                                                           መዝገቡ ዋኘው

እንዲህ  ያለ ጉድኛ ዘመን ላይ እንደርሳለን ተብሎ ለመገመት ያስቸግር ነበር፡፡ ሳያዩት ያለፉት ጻድቅ ናቸው እንበል መሰል በድሮው ቋንቋ፡፡ ነግቶ እስኪመሽ መሽቶም እስኪነጋ ድረስ ሀሳብ ከሀሳብ፤ መልካሙ ከጥፉው፤ በጎው ከአስከፊው፤ ጎጠኛው ዘረኛውና መንደርተኛው በአንድ ጎራ፤ የአንድነት ኃይሉና የመገንጠል አቀንቃኙ በሌላ ጎራ ተሰልፈው በቀላልና በከባድ የቃላት ውርጅብኝ ሲሞሻለቁ፤ አንዱ በሌላው ላይ ከባድ ማጥቃት ሲሰነዝር ሌላው መከላከል ሲያደርግ . . . ጉድ ያልነው፣ በታሪካችን ያልነበረና ያልተመዘገበ ጦርነት ሲካሄድ ውሎ ያድራል፡፡ ይህ ሁሉ ቱማታ ለሀገርና ለሕዝብ በሚበጅ መልኩ ቢሆን ኖሮ ምንኛ መታደል በሆነ ነበር፡፡

በቀለጠው የፌስቡክ መንደር የሚነዙት፣ የሚዘሩት፣ የሚረጩት መርዘኛና ዘረኛ የቃላት ጥይቶች መጋዘናቸው አያልቅም፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ያባሉ ዘንድ የሚረጩ ናቸው፡፡ እሳት ይተፋሉ፡፡ እያንዳንዱ የፌስቡክ ጸሀፊ ነኝ ባይ ፍጹም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ሕዝብን ያህል ግዙፍ ኃይል እንዳሻው እየተነሳ በቦርቃቃ አፉ ሲሳደብ፣ ሲዘልፍ፣ ሲያንቋሽሽ . . . ተው ይሄ ነገር ደግ አይደለም፤ ከባሕላችን ከወጋችን ውጭ ነው የሚል ከስንት አንዱ ብቻ ነው፡፡

በቀለጠው የሁካታና የጫጫታ መንደር በሆነው የፌስቡክ ሰፈር ሰላም የለም፡፡ ጭር ሲል አልወድም የሚሉ፣ ኃላፊነት የጎደላቸው፣ የማይሰማቸው ጋንጩሮችና አጋንንቶች አይሳካላቸውም እንጂ ሀገር ሰላም ከመንሳት እስከማፍረስ የሚዘልቅ ቅስቀሳ እስከማድረግ ዘልቀው፤ ጎራ ለይተው ይፋለማሉ፡፡ በየትኛውም መልኩ ከአብሮነት፣ ከመከባበርና ተቻችሎ በአንድነት ከመኖር ውጪ ለዚህች ሀገር የሚበጃት ሌላ ነገር የለም፡፡ የፌስቡክ አሸባሪዎች ትርምስ፣ ቅጥፈትና የሀሰት ወሬ ለሀገራችን በምንም መልኩ አይበጃትም፡፡ ሆን ተብሎ ሰላምዋን ለማደፍረስ የሚሰራ ስራ በመሆኑ በአግባቡ ማጤኑ ነው የሚጠቅመው፡፡ መስከንና መርጋትንም ይጠይቃል፡፡ እነሱም፣ በቃላት ጦርነት ውስጥ የተሰለፉት ተዋጊዎች እኛ ማን ነን ብለው ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል፡፡ በማሕበራዊ ድረ ገጽና በፌስቡክ የሚለቀቁት ወሬዎች የፈጠራ፣ የተጋነኑ፣ በሌለ መነሻ ችግሮችን የሚያባብሱና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስዱም በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ በስሜትና በቆስቋሽ ወሬዎች ከመንጎዱ በፊት በጥንቃቄ ሊያስተውል ይገባል፡፡

የፌስቡከኞች ፌዝ ከእውነታው ፍጹም በራቀ በማይገናኝ መልኩ የሚያሰራጩትና የሚነዙት በጎጥና በዘር ላይ መሰረት ያደረጉ ወሬዎች ችግሩ በሰላም እንዳይፈታ ከማግዘፍ ውጪ ለአብሮነት ለሰላማችን በፍጹም አይጠቅሙምና ሊወገዙ ይገባል፡፡  ሕብረ ብሔራዊ በሆነች ሀገር ውስጥ ዘረኝነትን ማራመድ፣ ይህንንም መሰረታዊ መርህ አድርጎ መግፋት የኋላ ኋላ መዘዙ ብዙና መመለሻ የሌለው ነው፡፡ ትንሹንም ትልቁንም በዘር መነጽር የማየት በሽታ ስለትልቅዋ ሀገር አብሮነትና ተቻችሎ ከጥንት ጀምሮ የኖረውን ባሕል የሚንድና ያልተጠበቀ ችግር የሚፈጥር ነው፡፡

የቀለጠው መንደር የፌስቡክ ሽብርተኞች ስለሀገርና ስለሕዝብ ሰላም ከማሰብ ይልቅ ነውረኛ በሆኑ ብእሮቻቸው ዘረኝነትን እየሰበኩ በማንአለብኝነት ስሜት የሕዝቡን አብሮነት ለመናድ እንቅልፍ አጥተው በማደር ተግተው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት አመታት አብዛኛዎቹ በሕግ ይጠየቁ የነበሩት እንደዛሬዎቹ አይንአውጣዎች በገሀድና በአደባባይ በጎሳና በዘር አፍራሽ ፖለቲካ ውስጥ ሕዝብን ከሕዝብ በሚያጋጭ አጀንዳ የተጠመዱ አልነበሩም፡፡ የቀረቡባቸው ክሶች መረጃዎች አብዛኛዎቹ የሚሉት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት በሕዝብ ላይ ለማስነሳት የሚሉ ነበሩ፡፡ ይህ አካሄድ ትላንትም ተደረገ ዛሬ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም፡፡

የቀለጠው መንደር አሸባሪዎች ኃላፊነት የሚሰማቸው ግለሰቦች አይደሉም፡፡ በጎሳና በዘር ካባ ተጠልለው የሚያፏጩ ከንቱዎች ናቸው፡፡ በቀለጠው የፌስቡክ መንደር የቃላት ተኩሱና እሩምታው ተግ አይልም፡፡ ውርጅብኝ ይወርዳል፡፡ ዶፍ በረዶ የሚጥል ከባድ ዝናብ ማለት ነው፡፡ ድርጊቱ ማንንም የማይጠቅም ተራነት ብቻ ሳይሆን ከሰውኛነት መፋታት፤ ከሰብአዊነት በታች መሆንም ነው፡፡ አንድ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ መብቱም ነጻነቱም ሊከበር ይገባል፡፡ በደልና መንገላታት፣ የተለየ ጥቃት፣ አድልዎና መገለል ሊደርስበት አይገባም፡፡

የፌስቡክ ተዋናዮች የቀለጠው መንደር ሁከተኞች በሚሰነዝሩዋቸው የወረዱ መልእክቶች ምን ያህል አስታየየት ሰጪዎች በኮሜንት ውስጥ እንደሚሰድቧቸው፣ ምን ያህል የሕዝብ ተቀባይነትና ተደማጭነት እንደሌላቸው፣ ይህንን መለኪያ አድርገው ሊታረሙ እንኳን  የሚችሉ አይነት አይደሉም፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት በአደባባይ መስራት የከፋ ጸረ ሕዝብነት ነው፡፡

ይልቁንም ስለሀገር ሰላም፣ ስለሁሉም ዜጎች ሰብአዊ መብትና ፍትሕ መከበር፣ ስለጋራ ሀገራዊ ችግሮች እንዴት ሊፈቱ እንደሚችሉ ሰፋ ባለ ግንዛቤ ቢሰሩ ነበር በሕብረተሰቡ ዘንድ ሊከበሩና ሊደመጡ የሚችሉት፡፡ ሶሻል ሚዲያው የፌስቡኩ መንደር የዘመናችን ከባድ የኃሳብ ውጊያና ፍልሚያ የሚካሄድበት፣ ሰላም የሚባል የማይታሰብበት፣ ሀይ ባይም ሆነ ሰላም አስከባሪ የማይገባበት ስድ መሬት ነው።

በፌስቡክ ጦር ሜዳ ውስጥ ተኩስ አቁም የለም፡፡ ትንሽ ተገግም አይልም፤ እንደ አብሪ ብቅ ብለው ጭረው ትንሽ ተኩሰው ወደ ምሽጋቸው የሚመለሱ አስተኳሸች አሉ፡፡ እነሱ ጥይት አያባክኑም፡፡ የተመረጠች ኢላማ ላይ ብቻ ተኩሰው ወደ ምሽጋቸው ይገባሉ፡፡ ከዚያ በኋላ እንግዲህ የሚለው የማያልቅበት ምልአት ከያለበት ለምን ተነካሁ ብሎ ከየምሽጉ ከከተማው ከፎቁ ከኮንዶሚኒየሙ ከቢሮው ከመስሪያ ቤቱ ከሀገር ውስጥና ከባሕር ማዶ ሁኖ ይህ ቀረው የማይባል ፋታ የማይሰጥ ምላሽ ያዥጎደጉዳል፡፡

የመልስ ምቱ ሊሰሙት የሚከብድና የሚዘገንን ነው፡፡ የስድቡ፣ የዘለፋው፣ የነቆራው፣ የአሽሙሩ፣ የማላገጡ አይነት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ነው፡፡ ነጮቹ እንዲህ አይነቱን ትንሽ ወርውሮ ብዙ ሀሳብ የመቀበሉን ስራ የሕዝብ አስተያየትና ሙቀት መለኪያ ይሉታል፡፡ እየሆነ ያለውም ይሄው ይመስላል፡፡ ኃሳብን በጨዋነት መግለጽ ሲቻል ሕዝብን መስደብ ከሁሉም የከፋው አይነት ተግባር ነው፡፡ የትኛውም ሕዝብ ቢሆን አይሰደብም፡፡

በሀገሪቱ ከጥንት ጀምሮ ሲነገሩ የኖሩና ያሉ ቀላልና ከባድ ስድቦች ዘለፋዎች አሽሙሮች ነቀፋዎች ተረቦች አጥንትና ልብ የሚሰብሩ ጸያፍ ቃላት ያንተ ያለህ እስኪያስብል ድረስ በቀለጠው መንደር ይዘንባሉ፡፡ እንደ ጉድ ይወርዳሉ፡፡ ለጫሪዎቹም ለተንኳሾቹም መጥኔ ይሥጣችሁ የሚያስብል ነው፡፡ ሰው ብረት ለበስ ነው ለካ ይሄን ያህል ሕሊና ሰባሪ መንፈስን ቀንጣሽ ስድብ ሲወርድበት የሚችል ብርቱና ጠጣር አለት ነው ያሰኛል፡፡ ግን እኮ ስድብ ጨዋነት አይደለም፤ ሀገርና ሕዝብን አይወክልም፡፡

የቀለጠው መንደር የፌስቡኩ የሁከት ሰፈር የከፋ ዘግናኝ ምልልስ ለማድረግ የፈጠነ ነው፡፡ የትኛውም አይነት ሀሳብ ይጻፍ ጦርና ዘገሩን ነቅንቆ ይነሳል፡፡ በል ያዝ እንግዲህ፣ የት አባትክንስና፣ ደሞ አንተ ብሎ ይሄን ባይ ሌባ፣ አውደልዳይ፣ ከሀዲ፣ ሞጭላፋ፣ ድስት ፊት፣ አፈ ሰፌድ. . .  የስድብና የነቀፌታ ዶፉ በረዶ ቀላቅሎ ያለማቋረጥ ይዘንባል፡፡ ደግነቱ የሚታይ ቁስለኛ የለም፡፡ በስውር ተኩሱ ከባድ ቁስል የቆሰለ የተጎዳ እልፍ አእላፍ ይኖራል፡፡ ለግዜው አምቡላንስ ተጠርቶ የተነሳ አላየንም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይህ በቀለጠው መንደር እየታየ ያለው የቃላት ጦርነት ከአካል በላይ ታላቅ የመንፈስና የሕሊና ቁስልና ሕመም የሚያስከትል ነው፡፡

የቀለጠው መንደር የፌስቡክ ወረዳና ሰፈር ነው፡፡ በዚህ ሰፈር ሰላም የሚባል ነግቶ እስኪመሽ የለም፡፡ የቃላት ጦርነትና ፍልሚያ ብቻ ነው ነግሶ የሚገኘው፡፡ በፌስቡክ የሽብርተኞች መንደር  እርቅ የለም፡፡ ሽማግሌ፣ አደራዳሪ፣ ተደራዳሪ የሙባል የለም፡፡ ጎራ ለይተው ሲከታከቱ የሚውሉ የሚያድሩ የቃላት ጥይት የማያልቅባቸው መደዴና ስልጡን ተኳሾች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ መንደሩ የቧልት የነገረ ሰሪዎች መንደር ነው፤ የስራ ፈቶች መንደር ነው፡፡ እንዲያውም መንግስት በማሕበር ቢያደራጃቸውና በአንድ ላይ እንዲኖሩ ቢደረግ ሌላው ሰላም የሚያገኝ ይመስለኛል ያሉ አዛውንት አጋጥመውኛል፡፡

በቀለጠው የፌስቡክ መንደር ሙጢ ሙጢው ይሄ እንደው ምላሱን አሹሎ ምላስዋን አሹላ እየተውረገረገች ወገብዋ ላይ ነጠላዋን ታጥቃ ስማ አንጂ አንተ እኔን እከሊትን ነው እንደዚህ የምትለው? ይሄ የሰው ልክ የማያውቅ . . .   እና የሚመስሉ ስድቦችን የሚያወርዱት አይነት ናቸው የቀለጠው መንደር ሰዎች፡፡

በስም ማጥፋት፣ በወሬ፣ በአሉባልታ ተጠምደው ወሬ ሲያርሱ ውለው የሚያድሩ፣ ከስራ የተፋቱ ወሬ ቀቃይ፣ አገንፋይ፣ አቡኪና ጋጋሪዎች የቀለጠው መንደር ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄንን ግዜያቸውን የሀገር ችግር ለመፍታት ሀሳብ ቢያፈልቁበት፣ ቢወያዩበት፣ ስለሕዝብ አብሮነት ቢነጋገሩበት የመፍትሔ ሀሳቦችን ቢያመነጩበት ምንኛ መታደል በሆነ ነበር፡፡

መሪጌታው በበቀደም እለት በታላቅ ጉባኤ መወድስ ሲያሰሙ የፌስቡክ አጋንንቶች ብለው ተቀኙ አሉ፡፡ ምነው አንድ ወይንም ሁለት ሰባት ጸበል ቢያዙላቸው በሚል መደመም አይቀርም፡፡ የፌስቡክ አጋንንት የእኛ ሀገር አጋንንት አይደለም፤ ከአውሮፓ የመጣ አጋንንት ነው የሚሉም አሉ፡፡ የእኛው ምሱ ይታወቃልና ጮሆ ይወጣል፡፡ ይሄ ግን ጋንጩሬ የሚባለውና እርስ በእርስ ማባላት፣ ማናከስ፣ ማመስ፣ ማተራመስ የሚወደው አይነት ነው ሲሉ የቀለጠው መንደር አባላት ራሳቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ መባሉ ልክፍቱ ቀላል አይደለምና ነው፡፡

የቀለጠው መንደር የፌስቡክ ጋንጩሮች ሁነኛ አጋፋሪዎቹ መደበኛ ስራ አጋጭ፣ አናጭ፣ አባላ፣ አተራምስ፣ አናክስ፣ ቆስቁስ፣ ሰላም ንሳ፣ ወትውት፣ አንጫጫ፣ አፍጫጫው ሲሆን፤  መተዳደሪያ መርሀቸውም መሆኑ ከሰላማዊው የፌስቡክ ሠራዊት የተለዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት፣ ለሕዝብ አብሮነትና አንድነት ፈተና ሁነው የቀረቡ ናቸው፡፡ ልንታገላቸው ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ሳይቃጠል በቅጠል ነውና ጉዳዩ ፈጣን ህጋዊ እርምጃን ይሻል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy