Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራሊዝም ከዴሞክራሲና ከህግ የበላይነት ውጭ ሊታሰብ አይችልም!

0 337

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራሊዝም ከዴሞክራሲና ከህግ የበላይነት ውጭ ሊታሰብ አይችልም!

ዳዊት ምትኩ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ዴሞክራሲንና የህግ የበላይነትን የሞት ሽረት ጉዳይ ያደረገ ነው። ስርዓቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ማስፋትና ማጥለቅ ዋነኛው ተግባሩ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህም ውጤት አምጥቷል። ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ ከህግ በላይ እንዳይሆንም በፅናት በመስራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ፌዴራሊዝም ከዴሞክራሲና ከህግ የበላይነት ለይቶ መመልከት አይቻልም።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱን እውን ያደረገው ህገ መንግስታችን ነው። የአገራችን ህገ መንግስት ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ይፈጥራል። የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ መንግስቱን የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ሲያፀድቁ በጋራ ፍላጎት ላይ ተመስርተው በመሆኑ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ህገ መንግስቱ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጎናፅፍ መሆኑ ግልፅ ነበር።

በመሆኑም በዚህ ሂደት ውስጥ ህገ መንግስቱ የሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን አጎልብቷል። ለዚህም በህዝቦች መካከል የነበረው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ከፍተኛውን ድርሻ መጫወቱ አይዘነጋም።

እንደሚታወቀው እንደ እኛ ዓይነት በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባሉበት ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መኖሩ የግድ ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እስከተጠናከረ ድረስ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መኖሩ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ባለፈው ሩብ ምዕተ-ዓመት የተከናወነው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የማጎልበት ጥረት ምንም ችግር አልነበረበትም ማለት አይቻልም።

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ባለፉት ስርዓቶች የነበሩት ውስብስብ የብሔር ጭቆናዎች አኳያ አስተሳሰቡን በቀላሉ ማስረፅ አስቸጋሪ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ይሁንና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሀገራችንን አንድነት በማጠንከር ኢትዩጵያዊነት እንዲያብብ እያደረገ መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እርግጥ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ማንነት ተደፍቆ ሊመጣ አይችልም። ተከብሮ እንጂ። ከ26 ዓመታት በላይ ሁሉም ማህበረሰብ በራሱ ቋንቋ የመናገር መብቱ የተጠበቀለት በዚሁ ፅንሰ ሃሳብ መነሻነት ነው

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል። ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ነውና። እናም በአሁኑ ወቅት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በመጎልበት ላይ ይገኛል።

እርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከትምክህትና ከጠባብ ኃይሎች ጋር ለሚደረግ ትግል ዓይነተኛ መሳሪያ ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የራስን ማንነት እንደሚያከብር ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ አሉ ብሎ የመቀበል ጉዳይ በመሆኑ መተሳሰብንና የጋራ ልማትን ያረጋግጣል።

የአገራችንን ፌዴራሊዝም ዴሞክራሲን እውን ከማድረግ በላይ የህግ የበላይነትንም የሞት ሽረት ያህል በመመልከት ማንም ሰው ከህግ በላይ እነዳይሆን የሚያደርግ ነው። እንደሚታወቀው አገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው። ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚኖርባት ይመስለኛል።

ሰላም በህግ የበላይነት የምናተርፈው ትሩፋት ነው። በሰላም ውስጥ የምናስባቸውን የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎችን ዕውን እናደርጋለን። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ሊሆኑ አይችሉም። ሁላችንም በህግ ፊት እኩል እንስተናገዳለን። የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም ተካፋዩች እንሆናለን።

ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ ይሆናል። ይህ በማንም ላይ የሚሰራ ተግባር ነው።

አንዱን ዜጋ ከሌላው በማበላለጥ የሚከናወን የህግ አሰራር በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፤ መቼም ቢሆን። እናም የህግ የበላይነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስከበር ማለት የህገ መንግስቱን መንፈስ በሁሉም መስኮች ማስፈፀም ማለት መሆኑን የትኛውም ዜጋ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይመስለኛል።

የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በነበርንበት ወቅት እንኳን የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይነካ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ይህ ጥንቃቄ የተደረገው ህገ መንግስታዊው ፌዴራላዊ ስርዓት ለሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚያደርግ ነው። የቱንም ወገን ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሲባል የሚከናወን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የለም። ሥርዓቱ ለእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ቦታ የለውም።

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን የምታከብረው የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ስለሚያዛት ብቻ ነው። ስርዓቱ ደግሞ ህዝቦች በበርካታ መስዕዋትነት ያመጡት ነው። ራሳቸው ይሁንታ እነዚህ ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የፈቀዱት ነው። ሰብዓዊ መብቶችን በማይነካና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የህግ የበላይነትን የማስከር ስራ እንዲከናወን ይፈቅዳል።

ሰላምን እውን ለማድረግ፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የህግ የበላይነት እውን እንዲሆን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህም የህግ የበላይነትን ማስከበር የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሰሶ እንዲሆን ያደርገዋል።

በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም።

በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ ይሆንበታል። ይህ ካልሆነ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ የተገኙትን ትሩፋቶች ማጣጣም አይቻልም።

ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል።

ይህ ሁኔታ ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። የአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት የህግ የበላይነትን የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርጎ የያዘው ከዚህ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ነው። በመሆኑም የአገራችንን ፌዴራላዊ ሥርዓት ከዴሞክራሲና ባህል ግንባታና ከህግ የበላይነት ለይቶ ማየት አይቻልም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy