Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቅይጥ የምርጫ ስርአት: ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መጎልበት

0 478

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቅይጥ የምርጫ ስርአት:

ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መጎልበት

 

 

ዮናስ

መንግስት የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት የበለጠ እንዲጎለብት አለኝ በሚለው  የጸና አቋም መነሻነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ከገዢው ፓርቲ ጋር እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ከገለጸ አመት ከሩብ አካባቢ ሆኗል። ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ሊደራደሩባቸው በሚሿቸው አጀንዳዎች ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ውይይት፤ የምርጫ ህግና ስርአትን በማሻሻል ጉዳይ ላይ ለመደራደር የተስማሙ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም የተቋቋመው የድርድር አጀንዳ አደራጅ ኮሚቴ ከፓርቲዎቹ የቀረቡትን ርዕሰ ጉዳዮች ጨምቆና ተመሳሳዮችን አጠጋግቶ፣ 13 አጀንዳዎች ለድርድር እንዲቀርቡ ባመቻቸው አግባብ በእነዚሁ በተመረጡ 13 አጀንዳዎች ላይ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ድርድራቸውን “ሀ” ብለው መጀመራቸውም በተመሳሳይ የሚታወስ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይልቁንም መድረክና ሰማያዊ “ለድርድር ብለን ያቀረብናቸው አጀንዳዎች ተቆርጠው ቀርተውብናል” የሚል አቤቱታ ማቅረባቸውና  ቀርተዋል ተብለው ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከልም “ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ሳይቀር ብሄራዊ መግባባት ማድረግ ያስፈልጋል” የሚለው ሃሳብ አንዱ ሲሆን፤ አሁን ያለው ባለአርማ ሰንደቅ አላማ ጉዳይም ህዝብን እያግባባ ባለመሆኑ ድርድር ሊደረግበት ይገባል የሚል መከራከሪያ ቀርቦ የነበረና አብዛኞቹም ያልተስማሙባቸው አጀንዳዎች ሆነው በመገኘታቸው ይህንና መሰል አጀንዳዎች ያቀረቡ እና በአጀንዳነት ያልተያዘላቸው ፓርቲዎች ከድርድሩ እራሳቸውን እንዳወጡም ይታወሳል።   

በ2008 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍሎች ከተቀሰቀሰው አመጽ በኋላ በተከፈተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ንግግር ለማድረግ የተገኙት ዶ/ር ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ፤ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት እስከ ማሻሻል የሚደርስ ተሃድሶ መንግሥት እንደሚያከናውን በገቡት ቃል መሰረት የተጀመረው ድርድር ሲወድቅ ሲነሳ ፤ ሲደገፍ ሲጣጣል ፤ሲሞካሽ ሲብጠለጠል በርካታ ወራትን ካስቆጠረ በኋላ ከሰሞኑ አብላጫን እና ተመጣጣኝ ውክልናን በሚቀላቅለው ቅይጥ የምርጫ ስርአት ላይ በመስማማት ከባዱን ዳገት የወጡት መስለዋል። ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በምክር ቤቱ ተገኝተው በፕሬዝዳንቱ ንግግር ላይ ለቀረበው ማሻሻያ ሞሽን ለምክር ቤቱ አባላት ባብራሩበት ወቅት፣ መንግሥት ከሚያከውናቸው ዓበይት ተግባራት መካከል የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት ማሻሻል አንዱና ዋነኛው እንደሚሆን በገቡት ቃል መሰረት የተከናወነ ነው።

ምንም እንኳን ፓርቲዎቹ የሚወያዩባቸውን ዓበይት አጀንደዎች ለመቅረፅና የድርድሩ አካሄድ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ለመስማማት ባደረጉት ቅድመ ድርድር ላይ በርከት ባሉ እና ከዓላማው ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ሲወዛገቡ ለተመለከተ የትም የማይደርሱ እንደሆነ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፤በአገሪቱ ተመዝግበው የሚገኙ 15 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር በተለያዩ የአገሪቱ የምርጫ ሕግ ማዕቀፎችና የምርጫ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት ማካሄድ ሲጀምሩ ደግሞ ብዙወች እንደገና ወደተስፋ መመለሳቸውም ይታወሳል።

ይህም ሆኖ በዚሁ አጀንዳ የመቅረፅና ገለልተኛ የሆኑ አደራዳሪዎች ድርድሩን ሊመሩት ይገባል በማለት ሲከራከሩ የቆዩት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) ያቀረቡት ሐሳብ፣ በተለይ ከገዥው ፓርቲ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ድርድሩ በቅድመ ድርድር ደረጃ እያለ አቋርጠው መውጣታቸው ስለአጀንዳችን እና ስለመድበለ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ሊታወስ ይገባል።

በመጀመርያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅን አዋጅ 573/2003ን በተመለከተው    የድርድር ውጤት መሠረት አንድ ፓርቲ በአገር አቀፍ ፓርቲነት ለመመዝገብ የሚያስፈልግ የነበረው 1,500 አባላት ሲኖሩት ነው የሚለው የአዋጁን አካል፣ ወደ 3,000 ያደገ ሲሆን፤ የክልል ፓርቲዎች የመሥራች አባላት ቁጥርን ከነረበት 750 ወደ 1,500 ከፍ እንዲል ሆኗል። በዚህ መሠረት ከድርድሩ የወጡት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ይህ የድርድሩ ውጤት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ፣ አዳዲስ ፓርቲዎች ወደ መጫወቻ ሜዳው እንዳይገቡ ይከለክላል የሚል ምክንያት በማቅረብ ከድርድሩ ውጭ ለመሆን ቢወስኑም፤ሃገር እመራለሁ የሚል አንድ ፓርቲ 3ሺህ ሰው ጭንቅ ሀነብኝ ሲል አስቀድሞም ወደፖለቲካው መስክ የገባው ለሌላ አላማ እንጂ ስለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አለመሆኑን የሚያመለክት ነው። ገዥውን ጨምሮ አሁንም በድርድር ላይ የሚገኙት ፓርቲዎች ወቀሳውን ሲያጣጥሉ የሚደመጡትም ስለዚህና ከጀርባቸው ያለውን ተልእኮ የተገነዘቡ ስለሆነ ነው የሚሉ ታዛቢዎችም እየተደመጡ ነው።  

በዚህም ተባለ በዚያ መውደቅ መነሳቱ ጋብ ብሎ በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ የያዙትን ድርድር አሁን የቀጠሉበት መሆኑ በራሱ የተደራዳሪ ፓርቲዎችን ህዝባዊ ውግንና የሚያረጋግጥ ይሆናል። በዚህም መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅን በማሻሻል የተጀመረው ድርድር ወደ ሁለተኛው አጀንዳ፣ ማለትም የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ 532/99ን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ሰሞንኛ ድርድር  የሃገሪቷ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን ተስማምተዋል።

ፓርቲዎቹ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን ቢስማሙም፣ የቅይጡ የመቶኛ ድርሻ ላይ መስማማት ተስኗቸው ለሁለት ወራት ያህል ድርድር ሲያደርጉ የነበረ መሆኑ እዚህ ላይ ሊወሳ ይገባል።ስለዚሁ መዘግየት  ጎልተው የወጡት ልዩነቶች ደግሞ ገዥው ፓርቲና ለዚህ ድርድር ዓላማ ሲባል ኅብረት በፈጠሩት 11 የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት የመቶኛ ድርሻ መጠን መለያየት ምክንያት እንደሆነም ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።

አሥራ አንዱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቅይጡ የመቶኛ ድርሻ እኩል 50 በ50 እንዲሆን የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በተናጠል እንዲሁ የተለያዩ የመቶኛ ድርሻዎችን በአማራጭነት አቅርበዋል። ለምሳሌ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) 75 በመቶ የተመጣጣኝ ውክልናና የ25 በመቶ የአብላጫ ውክልና ሥርዓት እንዲኖር ያቀረበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የተመጣጣኝ ውክልና እንዲሆን ሐሳቡን አቅርቧል።ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ እነዚህን የመቶኛ ድርሻዎች ሲያቀርቡ ገዥው ፓርቲ በበኩሉ መጀመርያ ላይ የ90 በ10 የመቶኛ ድርሻ፣ ከዚያም 85 በ15፣ እንዲሁም በመጨረሻ የ80 በ20 የመቶኛ ድርሻ በማቅረብ የመጨረሻው እንደሆነ አስታውቋል።

በእነዚህ ምጣኔዎች ላይ ሁለት ወራት ያስቆጠረው ድርድር በመጨረሻ በኢህአዴግ የሰጥቶ መቀበል መርሆ ተገዢነት የ80 በ20 የመቶኛ ድርሻ በፓርቲዎቹ ተቀባይነት አግኝቶ፣ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትትዩ እንዲሆን ተስማምተዋል።ፓርቲዎቹ ከስምምነት የደረሱበትን ነጥብ ተከትሎ ግን የሃገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ከዚህ ቀደም ከነበረበት የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት፣ ወደ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት ይሸጋገራል።የተለያዩ ጉዳዩን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ይህ ቅይጥ ትይዩ የሚገባለው የምርጫ ሥርዓት ሁለቱን የምርጫ ሥርዓቶች በአንድ ላይ የሚይዝ ሲሆን፤በቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት መሠረት አገሪቱ 80 በመቶ የአብላጫ፣ 20 በመቶ ደግሞ የተመጣጣኝ ውክልናን የሚያቅፍ የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች።የቅይጥ የምርጫ ሥርዓትን መከተል በአብዛኛው የመወከልን ጥያቄ ምላሽ የሚያስገኝ ሲሆን፣ በተጨማሪም የመራጮች ድምፅ እንዳይባክን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ይላሉ መረጃዎቹ።

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ልዩነት መኖር ጤናማ አካሄድ ነው። ጤናማ የማይሆነው ከላይ የተመለከቱ ህጋዊ መሰረት የሌላቸውን እና ይልቁንም ከድርድሩ መነሻና አላማ ጋር ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ የልዩነት ሃሳቦችን አንስቶ ለማሳጣት መሞከር ነው። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በድርድር ወቅት ልዩነት መፈጠሩ አዲስ ነገር አለመሆኑና ድርድር እስከሆነ ድረስም የሚጠበቅ ነው።ግን ደግሞ በያንዳንዱ ጉዳይ ተቀራርቦ መነጋገር መቻል ዋንኛ ጉዳይ ነው። በአካሄድ ጉዳዮች ላይ የሚኖር ልዩነትም  መሰረታዊ  ችግር  አይደለም፤ሊሆንም አይችልም። ችግር የሚሆነው ላይመለሱ በህግና ህገመንግስታዊ አግባብ የተቀበሩ አጀንዳዎችን አግበስብሶ እንወያይ ማለትና ለፓርቲዎች ከተሰጠ ስልጣን በላይ ርቆ የህዝብን መብትና ፍላጎት የሚጻረሩ ጉዳዮች ላይ ካልተደራደርን ብሎ አሻፈረኝ ማለት ነው።  

ምንም በማያሻማ መልክ ሃገሪቷም ሆነች ህዝቦቿ  በድርድር ወቅት  ከፓርቲዎች  የሚፈልጉት የህዝብንና የአገርን ጥቅም ቀዳሚ አጀንዳቸው  በማድረግ የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት  ለማጎልበት  ወደሚያስችል አጀንዳ እንዲመጡ ነው።  የዴሞክራሲ ስርዓቱን በማጎልበት  ልማትን ማፋጠን የሚያስችል የመደራደሪያ አጀንዳ እንዲያቀርቡ ነው።  ሁሉም የፖሊቲካ ፓርቲዎች ሰጥቶ መቀበልን እንደመርህ  ሲከተሉ ማየትን እንጂ ያልበላን ቦታ ላይ እንዲያኩልን አይደለም።

ለአገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዕድገት፣ ብልፅግና፣ እንዲሁም ለሕዝብ የተሟላ እርካታ ሲባል ጤነኛ የሆነ ሥርዓት መገንባት መቼም ቢሆን የማይታለፍ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ገዢው ፓርቲ ከላይ የተመለከተውን የእንደራደር ጥያቄ ጨምሮ በርካታ መደላድሎችን  ከመፍጠር ጀምሮ ውክልናን ለተመለከተው አጀንዳ ያሳየው የሰጥቶ መቀበል መርሆ ሊያስመሰግነው የሚገባ እና ሌሎቹም በቀሩትና ለድርድር በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ በዚህ አግባብ እንዲጓዙ መልእክት የሚያስተላልፍ ውሳኔና ስምምነት ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy