Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሁለንተናዊ ለውጦቻችንን እውን ያደረገ ዕለት

0 267

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሁለንተናዊ ለውጦቻችንን እውን ያደረገ ዕለት

ዳዊት ምትኩ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት የጸደቀበት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ነው። የዛሬ 12 ዓመት ገደማ “የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን” ተብሎ መከበር ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ሁሉም ክልሎች በዓሉን የማስተናገድ ዕድል አግኝተዋል። በዚህ ዓመትም “በሕገ መንግስታችን የደመቀ ሕብረ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የተከበረው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በህዝቦች ዘንድ አንድነትና መፈቃቀርን በማጎልበት በእኩልነትና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት እንዲፈጠር ማስቻሉን እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች የማይተካ ሚና አበርክቷል።

ታሪክን የኋሊት ለመመልከት ያህል ያለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ገዥዎችን ተጠቃሚ ያደረጉት ሥርዓቶች ሀገራችንን በሁለንተናዊ መልኩ ጎድተዋታል፡፡ ምጣኔ ሀብቷን አድቅቀዋል፤ ዜጎቿን ለችጋርና ስደት ዳርገዋታል፡፡ ይህ የታሪካችን አንድ አካል መሆኑ ጨርሶ አይካድም፡፡

በተለይም የጥቂት መኮንኖች ስብስብ የነበረው ወታደራዊው አምባገነናዊ የደርግ ሥርዓት የህዝቡን የትግል ውጤት በመቀማት ይልቁንም እንደ መልካም የ“ሥልጣን ዱላ ቅብብሎሽ” አጋጣሚውን በመጠቀምና ድሉን ወደራሱ በመቀልበስ በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ጣጣ አምጥቶ ማለፉ የትናንት ትውስታችን ነው፡፡

ይህም ሆኖ ሕዝቦቿ ከደርግ ውድቀት በኋላ የተረጋጋች እና ዜጎቿም ተፈቃቅደውና አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መስርተው እርስ በርስ እየተከባበሩ በፈጠሩት ፌዴራላዊ ሥርዓት የፈጣንና ተከታታይ ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበት አገር ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡

ይህ እየጎለበተ የመጣውና የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባባት ያለች ሀገርን ለመመስረት እልህ አስጨራሽ ትግልንና የህይወት መስዋዕትነትን ጠይቋል፡፡ ይህ በታሪክ ሁሌም የሚወሳ ሀቅ ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ሕዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ጨለምተኞቹ ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም፡፡

አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ሥራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እድገትና አንድነት ሠላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም። ግና ‘ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ለብተና የሚዳርግ ነው’ እያሉ ማጥላላትና ማጠልሸት ምንም ትርፍ አላስገኘላቸውም።

ሰው በላውና ወታደራዊው አምባገነን የደርግ ሥርዓት በተደመሰሰበት ወቅት ለሌላ ትግል የሚጋብዙ ፈታኝ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች በሀገሪቱ መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ በወቅቱ ተራማጅ አስተሳሰብን የያዙ ፌዴራሊዝም ለዘመናት ደም አፍሳሽ የሆነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ያመኑ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በአንድ ጎራ ተሰለፉ፣፣

በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ሁለት ፅንፍ ጫፍ ላይ የወጡ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ወገኖች ነበሩ። በወቅቱ የታጠቁ ብሔር ተኮር ድርጅቶች መኖራቸው ቀዳሚው ጉዳይ ነበር፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ የችግሮቹ መፍትሄ መገነጣጠል ነው ብለው ያምኑም ነበር፡፡

በሌላኛው ወገን የሀገሪቱ መፍትሄ የሆነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደ መበታተን አደጋ በመቁጠር ባረጀ እና ባፈጀ የአንድነት ስም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎም መፈቃቀድን “በእኛ እናውቅልሃለን” የፖለቲካ እሽክርክሪት በማጦዝ ሀገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡

ታዲያ በወቅቱ እነዚህን ተግዳሮቶች በሰከነ ብስለት በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊት ሀገርን ለመመስረት ከፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ከባድ ትግል ማካሄድ ግድ ብሎ ነበር፣፣  ውጤቱም በተራማጅ ኃይሎች አሸናፊነት እልባት አገኘ፡፡

ከዚህ በኋላም ቢሆን ሁሉም ነገር ቀላል አልነበረም። መግለፅ በሚያስቸግር መልኩ ሀገሪቱ ከባድ ፈተናዎች እንደገና ከፊት ለፊቷ ተደቀነባት፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች የላቀ ስፍራ የያዘው እና የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት የሆነው ድህነትን የመዋጋት ዘመቻ ነበር፡፡

ታዲያ ይህ የጋራ ጠላት መፍትሄ የሚያገኘው በመንግሥትና በመላ ሀገሪቱ ዜጎች  የተባበረ ክንድ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ በቅድሚያ መንግሥት የመሪነት ሚናውን በመውሰድ ህዝቡን በአስተሳሰብ ደረጃ በድህነት ላይ ድል እንዲቀዳጅ የማድረግ ኃላፊነትን በሚገባ ለመወጣት ቆርጦ ወደ ትግበራ ተገባ፡፡

በወቅቱም ድህነትን የመታገል ታላቅ ጉዞ እንዴት ሊከናወን ይቸላል? ይህን የጋራ ጠላት ተዋግቶ ለማሸነፍ መሠረታዊ የሚባሉ ቁልፍ ጉዳዮችስ ምንድናቸው? የሚሉ ዐበይት ተግባራትን መለየት ወሣኝ ጉዳይ ነበር፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነውን ህገ መንግሥት ማፅደቅ ቁልፉ ተግባር ነው፡፡

ምንም እንኳን ህገ መንግሥቱን ለማፅደቅ መንግሥት መድረኩን ቢያመቻችም አንዳንድ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎችና የህዝቡን የሥልጣን ባለቤትነቱን በአቋራጭ ለመንጠቅ ያሰፈሰፉ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሁኔታውን በቀላሉ ሊቀበሉት አልፈቀዱም፡፡

ሆኖም በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት ሥልጣን ከህዝብ የሚመነጭ መሆኑን እነዚህ ወገኖች በግልጽ እንዲያውቁ የተለያዩ ጥረቶችን ከማድረግ አልቦዘነም፡፡ እናም ሥልጣን የሚገኘው ከኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰጥ ድምጽ እንደሆነም የማረጋገጥ ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡  

በዚህ ወቅት ‘ሀገሪቱ ህገ መንግሥት ሊኖራት አይገባም እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረገ ፈዴራላዊ ሥርዓት የምትገነባ ሀገር በምንም መልኩ ተጠቃሚ ልትሆን አትችልም’ የሚሉ ተቃራኒ አመለካከቶች ዋነኛ ፈተናዎች ሆኑ፡፡

ታዲያ እነዚህ ጋሬጣዎች ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እየተሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቅደውና ተማምነው ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገ መንግሥትን አፀደቁ፡፡ ይህ ህገ መንግሥትም የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በመሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎች ሊመልስ በቃ፡፡

ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ መግጠም ተያዘ፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከድህነት በላይ ጠላት እንደሌላቸውም አረጋገጡ፡፡ ይህን በጽናት ለመዋጋትም እጅ ለእጅ ተያያዙ፡፡ ሁለንተናዊ ለውጦቻቸውንም እውን አደረጉ፡፡ በዚህም ዛሬ ለሚገኙበት ዜጎች የሰላም አየር የሚተነፍሱበት፣ ልማትን እውን የሚያደርጉበትና ዴሞክራሲን የሚገነቡበት ዕለት በቁ፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy