Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሁሉን በብሔር ስም የማጦዝ አባዜ

0 449

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሁሉን በብሔር ስም የማጦዝ አባዜ

                                                  ዘአማን በላይ

በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት አልቆመም። እጅግ በሚበዙትም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደታቸው ሳይቋረጥ ቀጥሏል። እንዲያውም በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ የመማር ማስተማሩ ሂደት ፈፅሞ አልተስተጓጎለም—መደበኛው ሂደት እንደቀጠለ ነው። ለዚህም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ ካሉት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አንዳቸውም የመማር ማስተማር ሂደታቸውን እንዳላቋረጡ መጥቀስ ይቻላል።

ርግጥ የተማሪዎቹ ጥያቄዎች ከብሔር ጉዳይ ጋር ያልተያያዘና እንዲያውም የጥያቄያቸው መነሻ የአስተዳደር ችግሮች አሊያም ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ካወጣው የመውጫ ፈተናና መሰል ጉዳዩች ጋር የተያያዘ ነው። ሆኖም ሁሌም እዚህ ሀገር ውስጥ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ለጉዳዩ ቀንድና ጭራ እያበጁለት ሴራ የሚጎነጉኑ ፅንፈኞች ጥያቄዎቹን በብሔር ሽፋን በማበጀት ሊያጦዙት ሲሞክሩ ይስተዋላል።

ይሁንና የፅንፈኞቹ ማናቸውንም ጉዳዩች ከብሔር ጋር እየሰፉ የማጣበቅ ፍላጎት መሰረተ ቢስ ነው። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተገነባ ያለው ስረዓት የብሔሮችን መብት የሚያከብርና በዴሞክራሲ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ የሚመራ እንጂ አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር እንዲጋጭ ምንም ዓይነት በር የሚከፍት ስላልሆነ ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ተጠቃሚዎቹ የተማሪዎችን ጥያቄዎች ወደ ብሔር ሽኩቻ የሚለውጡት ሃይሎች መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም። ተማሪዎች የህይወታቸው አንድ ክፍል የሆነውን ትምህርትና ውዱን ጊዜያቸውን ባልተገባ ሁኔታ ማሳለፍ የለባቸውም። የኋላ ኋላ ተጎጂው እነርሱው ራሳቸው መሆናቸውን መንዘ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።

ግጭቱ ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኝ አብዛኛው ተማሪ ትምህርት ፈላጊና ጊዜውን በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍ የሚሻ አይደለም። ለአንድ ተማሪ እንኳንስ ዓመት ቀርቶ አንድ ሳምንት ባልተገባ ሁኔታ ትምህርት መቋረጡ ምን ያህል ሊጎዳው እንደሚችል ግልፅ ነው። ይህ ደግሞ ከህይወቱ ላይ ጊዜ የመስረቅ ያህል መሆኑ አይታበይም። ከተማሪው ህይወት ላይ ጊዜ እየሰረቁ እነርሱ የግል የተላላኪነት ፖለቲካቸውን በየማህበራዊ ድረ ገጾች የሚያስተጋቡ ሃይሎችን የጥፋት መለከት ባለመስማትና አንድን ብሔር ከሌላው ጋር የሚያጋጭ ስርዓት ሀገራችን ውስጥ አለመኖሩን በማወቅ ካልተገባ ሁኔታ መታቀብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ተማሪዎች እንክርዳዱን ከገብሱ በመለየት ለዚህ ዓይነት መሰረት አልባ ውዥንብር መጋለጥ የለባቸውም።

ርግጥ ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ ማንሳት ህገ መንግስታዊ በምት ነው። ማንም የሚገድበው አይደለም። ዳሩ ግን የጥያቄዎቹን ምላላሽ ለማግኘት የሚኬድባቸው መንገዶች ተገቢ አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። ሰላማዊ ጥያቄዎች ምላሻቸው መገኘት ያለበት በሰላማዊ ሁኔታ እንጂ በሁከትና በብጥብጥ አይደለም።

ሰላማዊ ጥያቄን አንስቶ ምላሹን ከብሔር ጋር ማገናኘት ምንም ዓይነት ሚዛን የሚደፋ አመክንዮ የለውም። አመክንዩ ከሌለው ጉዳይ ደግሞ ተጠቃሚው የጥያቄው ባለቤት ሳይሆን በጥያቄው ሳቢያ ሁከትና ነውጥ እንዲነሳ የሚሹ ፅንፈኞች ብቻ መሆናቸውን ተማሪዎች ሁሌም ሊያስታውሱት የሚገባ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሀገራችን ውስጥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ከተከበረ ከ26 ዓመታት በላይ ሆኖታል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት ሁሉም ኢትጵያዊ በህግ ካልተደነገገ በስተቀር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች እኩል መብት እንዲኖራቸው ተደርጓል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ተረጋግጧል። ዜጎች በህግ ፊት እኩል ሆነዋል። የሚከተሉት የኃይማኖትና እምነትም በእኩልነትን የሚታዩበት ህገ መንገስታዊ ስርዓት ተረጋግጧል። ፍትሕን እንዲቋደሱና በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ሁነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። በዚህ አዲስ የእኩልነት ግንኙነትም ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል።

የህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ ይህ እንዲረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ ተደርጓል።

ባለፉት መንግስታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር እንዲያረጋግጡ ተደርጓል። ይህም የትኛውም ብሔር የበላይም የበታችም ሳይሆን ከሀገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ አስችሏል።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነቶች አዲስ የእኩልነት መንፈስ መክፈቱንነና እንደ ማረጋገጫ መሣሪያ ስለተወሰደም በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሰረት ተደርጓል። ይህ ሁኔታ ባለበት ስርዓት ውስጥ ለብሔር ግጭት የሚዳርግ ምክንያት የለም።

በአንድነት መንፈስ አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየታገሉ ያሉት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በምንም ዓይነት አስተሳሰብ የሚጋጩበት ምክንያት የለም። ዩኒቨርስቲዎቻችን የዚህ አንድ ማህበረሰብ መገለጫዎች እንጂ በየብሔሩ ጎራ ለይተው የሚፋለሙበት መድረክ ሊሆኑ አይገባም።

በየዩኒቨርስቲው ያለ ወጣት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ነው። ይህ ወጣት ዛሬ ተምሮ ሀገሩን ሊለውጥ የሚችልበት የትምህርት ገበታ ተዘርግቶለታል። በዚህ የትምህርት ገበታ ላይ ተቀምጦና ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ የሀገራችን የነገ ተስፋ መሆን ይኖርበታል። ጥያቄ ካለውም የጥያቄው ጭብጥ ከብሔሩ ጋር የማይገናኝ ሆኖ ሳለ ለምን ፅንፈኞች ጉዳዩን ከዚህ የብሔር ሁኔታ ጋር እንደሚያገናኙት በሰከነ መንፈስ ማጤን ይኖርበታል።

በየዩኒቨርሲቲው የሚገኝ ወጣት እንደሚገነዘበው አዲሲቷ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያሳየችው ውጤትም አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው የምጣኔ ሃብት እድገት መሠረት ሆኗል። በዚህም ሀገራችን የሚሊየሙን የልማት ግብ ከማሳካት ባሻገር፤ ለጥራት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

ይህ ሁኔታም ዛሬ በውጭ ባለሙያዎች የሚከናወን ስራ በእጅጉ እየቀነሰ ነው። በልማቱ ስራ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ የውጭ ሙያተኞች ዕውቀት ጥገኛ እንዳንሆን አድርጎናል። አሁንም ድረስ በውጭ ባለሙያዎች የሚሰሩ ስራዎች ያሉ በመሆናቸው ወጣቶች እነዚህን ስራዎች ለማከናወን ትምህርታቸውን በአግባቡ ሊከታተሉ ይገባል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ ባለተራዘመ ጊዜ ውስጥ በወጣቶቻችን እልባት ሊሰጠው ይገባል። ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር በአፋጣኝ ልንተም የግድ ይለናል። ለዚህ ደግሞ የሀገሪቱ ተስፋ የሆኑት የዩኒቨርስቲ ወጣቶች ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱን የሀገሪቱን ትልቅ አደራ የተሸከመ ወጣት የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ሆን ብለው ወደ ብሔር ጉዳዩች በማጦዝ የሁከት አውድማ እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ ፅንፈኞችንና ጭፍራዎቻቸውን ለይቶ በማወቅ ፊቱን ሀገሪቱ ወደምትጠብቅበት ተምሮ ወገንን የማገልገል ትክክለኛ መስመር መመለስ ይኖርበታል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy