Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕዝባዊ ጥያቄዎች ሰላማዊ መንገድን ይሻሉ

0 311

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕዝባዊ ጥያቄዎች ሰላማዊ መንገድን ይሻሉ

ዳዊት ምትኩ

የትኛውም ዓይነት ህዝባዊ ጥያቄዎች በሰላማዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ህብረተሰቡ ሰላምን በዘለቄታ ሁኔታ ማረጋገጥ የሚችለው ሰላምን በባለቤትነት መንፈስ ይዞ  ሰላሙ እንዲጠበቅ ራሱ መስራት ሲችል ነው። ያለ ህዝቡ ቀጥተኛ ታሳትፎ በፀጥታ ኃይል ስምሪትና ጥበቃ ብቻ አስተማማኝ ሰላምን ማምጣት ስለማይቻል ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድና አግባብ ባለው ሁኔታ ማቅረብ ይገባል።

ማናቸውም ዓይነት ጥያቄዎች የሚመለሱት በሰላማዊ መንገድ እንጂ በሁከት አይደለም። ሁከት የሰላማዊ ጥያቄዎች ማስፈፀሚያ ሊሆን አይችልም። ሆኖም አያውቅም። በመሆኑም ጥያቄዎችን ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው፣ በተቀመጠው አሰራርና ህግ መሰረት ማቅረብ ይገባል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ማንኛውም ሰው ያሻውን ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። ማንም አይከለክለውም። ሆኖም እየኖርንበት ያለው አገር ህግና ስርዓት ያለው እንደመሆኑ መጠን፤ ጥያቄዎች ሲቀርቡ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መሆን ይገባቸዋል። የሁከት መንገድ ራስን፣ አካባቢን፣ የስራ ቦታንና አገርን ከመጉዳት ውጭ አንዳች ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም። በሰላም እንጂ በሁከት ሰላማዊ ጥያቄዎቹን መመለድስ የቻለ፣ የበለፀገና ተጠቃሚ መሆን የቻለ አገር መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም። አይመስለኝምም።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላምን ጥቅም የሚገነዘብ ነው። የሁከትን ጥፋት ደግሞ ከቅርብ ጊዜው የኪራይ ሰብሳቢዎችና የኮንትሮባንዲስቶች ተግባር መረዳት ተቻለ ይመስለኛል። እናም የሰላሙ ጠባቂ ህብረተሰቡ ራሱ መሆኑን በመገንዘብ ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል።

በዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር የፀጥታ ሃይል ብቻ በማሰማራት ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የየቀየው ባለቤት ህዝቡ ነው። በፀጥታ ሃይል የሚሰጥ ምላሽ መሰረቱ ምናልባት ነገሮችን ለማረጋጋት ይጠቅም ይሆናል። ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ሎሆን የሚችል አይመስለኝም። እናም የየመንደሩ ጠባቂና የሰላም ዘብ ህብረተሰቡ እንደመሆኑ መጠን ለሰላሙ መትጋት ይኖርበታል።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ከአገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ከ26 ዓመታት በላይ በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። እናም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የአገራችን ህዝብ ይመስለኛል።

ይህ ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ ማቅረብ ይችላል።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና መደግ እንደሚቻል ሩብ ክፍለ ዘመንን እልፍ ባለ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትምህርት እንደወሰደ ራሱ እማኝ ነው።

አምባገነኑና የዕዝ ኢኮኖሚ መርህን የሚከተለው የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊት የአገራችን ምጣኔ ሃብታዊ አሃዝ ከዜሮ በታች እንደነበር የማይዘነጋው ይህ ህዝብ ስለ ሰላም ቢናገር የሚበዛበት አይደለም።

አምባገነኑ ስርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዕዋትነት በሚገባ ይገነዘባል። ያኔ ተራራ የሚያክለውን የአገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎችን ቢሰንቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣና ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪትን ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በማወቁ ሌላ መንገድ እንዲቀየስ ማስፈለጉን የሚያስታውስ ህዝብ ነው።

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ሃይሎችና በሀገራችን የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል። ይህ አዋጅም በወቅቱ ሰላሙን ተነጥቆ በነበረው የየአካባቢዎቹ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ ያለው ስለነበረ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ተችሏል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። ይህ የሆነው ህዝቡ የየቀየው ሰላም ባለቤት ሆኖ ስለተንቀሳቀሰ ነው። ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት እስከሆነ ድረስ የሚፈጠር የሰላም እጦት አይኖርም። የሚነሱ ጥያቄዎችንም አግባብ ባላቸውና በሰላማዊ መንገዶች ማቅረብ ይቻላል።

ሰላም እንደ እኛ ላለ አገር የህልውና ጉዳይ ነው። ህዝቡ ጥያቄዎቹን ሰላማዊና ህጋዊ ማድረግ ይኖርበታል። በህገ መንግስታችን ላይ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ዓይነት ዓላማ ማራመድ እንደሚችል ተደንግጓል። በዚህ ድንጋጌ መሰረትም ጥያቄዎችን በህጋዊ መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል። ጥያቄው ህዝባዊ በመሆኑም የየትኛውም ሁከት አራማጅ ሃይል እጅ መኖር የለበትም።

እርግጥ የሀገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም—ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ጭምር እንጂ። አዎ! ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም። የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሰላምነትን ማንገስ አይቻልምና።

በመሆኑም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም— ይጠብቃቸዋል እንጂ። ለፀረ ሰላም ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የዜጎች ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም። በተለይ ወጣቶች ከእነዚህ ሃይሎች የተንሸዋረረና ሰላምን ከሚያሳጡ አስተሳሰቦች ራሳቸውን መቆጠብ ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቶች እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን ይሻሉ። ተጠቃሚነታቸውን ግን ማሳካት ያለባቸው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። አገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው።

ሆኖም ተጠቃሚነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ ከሁከትና ከብጥብጥ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። እንዲያውም ሰላምን በማወክ ተግባር ላይ የተሰማሩትንም ሆነ ሊሰማሩ የተዘጋጁትን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማስተማር የሚኖርባቸው ይመስኛል። በመሆኑም ስለ ሰላም ሲባል ጥያቄዎችን ማቅብ መብት ቢሆንም፣ አቀራረቡ ግን ሰላማዊ መንገድን የተከተለ መሆን እንዳለበት ወጣገቶች ቀዳሚ አስተማሪዎች መሆን አለባቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy