Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልካም አስተዳደርን ለማስፈን…

0 689

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

መልካም አስተዳደርን ለማስፈን…

 

ወንድይራድ ተስፋዬ

 

የመልካም አስተዳደር ሥራ በአንድ ጀንበር ተከናውኖ ችግሮቹ በአንድ ለሊት ይወገዳሉ ተብሎ አይታሰብም። ሂደት ነው። ዓመታትን ይጠይቃል። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገራት ካለባቸው የማስፈፀም አቅም ውስንነት አንጻር ሲታይ ደግሞ ይህን እውነታ ይበልጥ ያጠናክራል። በኢትዮጵያ አሁን ያለው የመልካም አስተዳደር ትግበራ አፈፃፀም የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መሻሻል እያሳየ ስለመምጣቱ የሚያስማማ ይሆናል።

 

ዛሬ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየገለበተ መጥቷል። ይሁንና በጥቂቶች ዘንድ ይህንን በተገቢው መንገድ የመገንዘብ ችግር አሁንም ቢሆን ሲንፀባረቅ ይስተዋላል። የኢ ዴሞክራሲያዊ ካባን ከውስጥ ደርበው የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ነን ባይ ተቃዋሚዎች ይህ በህዝቡ ዘንድ የማይደገፍ እኩይ ሴራ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ህዝብን እንደ ህዝብ የሚንቅ ማንኛውም አካል የመጨረሻ ዕጣ ፈንታው ተንቆ መወርወሩ አይቀርምና ነው። እዚህ ላይ አንድ እውነታን ማንሳት ፈለግሁ። ይኸውም መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግሥት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ማንኛውም ህዝብ ያልተሳተፈበት ጉዳይ ውጤታማና ተፈፃሚ ሊሆን አይችልምና።

 

በመሆኑም በመንግሥት በኩል መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት የሚከናወኑ ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው መላው ህዝብም ዛሬም እንደ ትናንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ግድ ይለዋል። በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ በጎ ተግባር ነው።

 

መንግሥት ምንም እንኳን ግዴታው ቢሆንም ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ሥር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የዜጎች አቤቱታ የሚደመጥበት እንዲሁም ተገቢው ምላሽ የሚሰጥበት የእንባ ጠባቂ ተቋምን አቋቁሟል።

ለዴሞክራሲው ግንባታ እውን መሆን ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት “መልካም” ተብሎ ሊሞካሽ ይገባል። ዳሩ ግን ያለ አንዳች ማስረጃ በመንግሥትና በዴሞክራሲ ተቋማቱ ላይ በደፈና ጥላቻ እየታጀቡ ማንኳሰስ ተገቢ አይሆንም። ክንዋኔዎችን በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ከሚያይ ተፎካካሪ ፓርቲም አይጠበቅም። ከዚህ በፊት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ደጋግሜ ሀሳቤን  ገልጫለሁ። አሁንም እደግማለሁ። የሚሞግተኝ ከመጣም በአክብሮት ተቀብዬ አስተናግዳለሁ።

በኢትዮጵያ እውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ሥርዓት መሠረት ዜጎች የፖለቲካ መሪዎቻቸውንና ተወካዮቻቸውን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማሉ፤ ይሽራሉ። ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማካይነት በቀጥታ የሥልጣን ባለቤት የሆነበት ይህ አሠራር በሥርዓቱ ውስጥ ወሣኝ ሚና ይኖረዋል። ሆኖም በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት መኖራቸው ደግሞ አልቀረም። በዚህ የአሠራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚው፣ ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው።

እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ የሚሆኑ ናቸው። ሆኖም ግን የየራሳቸው ነፃነት አላቸው። እዚህ ላይ ሥራ አስፈፃሚውና ሲቪል ሰርቪሱ ማንም እንዳሻው የሚፈነጭባቸው አካላት አለመሆናቸውን ማወቅ ይገባል።

 

ከዚህ ይልቅ ህዝቡና የህዝቡ ተወካዮች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን መቀበል የግድ ነው። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው በኢትዮጵያ የህዝብ ሉዓላዊነት መሣሪያዎች፣ አገልጋዮችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች ከሆኑ ጥቂት የማይባል ዓመታትን አስቆጥረዋልና ነው። እዚህ ላይ ጥቂት ማሣያዎችን ብንጠቃቅስ ምን ይለናል?

 

የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱ የተጠቃሚው መብትና ጥቅም እንዳይሸራረፍ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ይህ ተግባርም መንግሥት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተኪያ የሌለው ድርጊት መሆኑን እንደሚያምንና በቁርጠኝነት ለመተግበርም በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሱን የሚያመላክት ነው።

 

ሌላው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ነው። ተቋሙ የዜጎችን አስተዳደራዊ በደል ተገቢው ምላሽ እንዲያገኝ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። በስሜት ብቻ እየተገፋፉ የተቋሙን ስም ለማጥፋት መሯሯጥ እንዲሁም መንግሥት በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረት በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ታውሮ ላለመቀበልና ለማጣጣል መሞከር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። አሁንም ይህንኑ አቋሜን እንደያዝኩ እገኛለሁ።

 

ራሱ ተቃዋሚ ነኝ ባዩ አካልም ቢሆን አመለካከቱ ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ በእንዲህ ዓይነቱ ጭፍን እሳቤ ጉዞው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ ደንቃራ እሾህ መሆኑ አይቀርም። እዚህ ላይ መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ሥርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሥርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምርም የነገሰበት ነው። ለምን ቢባል ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሥልጣን የህዝብና የህዝብ ብቻ መሆኑን በግልፅ አስቀምጧልና ነው። ሥልጣን የተገልጋዩ ህዝብ መሆኑ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር እመርታ የራሱ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚካድ አይደለም።

 

መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሐሳብ ጉዳይ አይደለም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ተግባሩ ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ላይ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብም ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ህዝቡ በህገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን ሥልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበትም ዕድል ይፈጥራል።

 

ታዲያ የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲተገበር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። እያከናወነም ይገኛል። ቀደም ሲል የጠቀስኩት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ችግሮችን እየተከተታተሉ በማረም ለመልካም አስተዳደር ግንባታው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ከተቋቋሙት ገለልተኛ አካላት ውስጥ ለማሣያነት ተጠቃሾች ናቸው። ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እነዚህ አካላት እንዲቋቋሙ በአዋጅ ከማፅደቅ ጀምሮ ተግባራቸውንም የመልካም አስተዳደር እመርታን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈፅሙ እስከ ማድረግ ድረስ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

 

እነዚህ ገለልተኛ አካላት ህዝቡ በህገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡለት መሠረታዊ መብቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። እስካሁንም ድረስ በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጡ ነው – አቅም በፈቀደላቸው መጠን።

 

ይህ ሲባል ግን የመልካም አስተዳደር ችግር በአገሪቱ ውስጥ ፈጽሞ የለም ማለት አይደለም። ሆኖም በአስቸኳይ መፈታት ያለባቸው ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሄ እየተሰጣቸው ነው። ሌሎችም እየታዩ በሂደት ምላሽ እያገኙ ነው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ችግር በሂደት የሚስተካከል መሆኑ አይቀሬ ነውና።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy