Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መጋለጥ የሚገባቸው የብጥብጥ ኃይሎች

0 355

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መጋለጥ የሚገባቸው የብጥብጥ ኃይሎች

                                                         ታዬ ከበደ

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው በመሰረቱት ሕገ መንግስት በጋራ ሰርተው ለማደግ ቃል ገብተዋል። ይህ ቃላቸው ግጭትንነና ብጥብጥን የሚፈቅድ አይደለም። ይህም በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የሚነሱ ብጥብጦች ሕዝብን የማይወክሉና በኪራይ ሰብሳቢዎችና በኮንትሮባንዲስቶች የተቀነባበሩ መሆናቸውን የሚያስረዳን ነው። በመሆኑም አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር በማጋጨት የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ እነዚህን ጥቂት የብጥብጥ ኃይሎች ህብረተሰቡ ከውስጡ እየለየ ማጋለጥ የሚገባው ይመስለኛል።

ኢፌዴሪ ህገ መንግስትን እንደ ችግር ጊዜ መውጫ አድርጎ መመልከት ተገቢ ነው። ለዚህም ሩቅ ሳንሄድ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንደ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውንና ሁከት ለመለወጥና ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ በማድረግ ላይ የሚገኘውንና በህገ መንግሰቱ መሰረት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መጥቀስ ይቻላል። ይህም ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ችግሩን በህገ መንግስቱንና በህገ መንግስቱ አግባብ ብቻ የሚፈታ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ታዲያ ይህን መሰሉ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ዕውን እንዲሆን በሙሉ ድምፁ ካፀደቀው ህዝብ በስተቀር ማንም ከመሬት ተነስቶ ሊጥሰው አሊያም እንዲቀር ሊያደርገው አይችልም። የራሱ የሆነ ህግና ስርዓት ያለው በመሆኑም በገዥው ፓርቲም ይሁን በተቃዋሚዎች ወደ ጎን ሊባል አይችልም።

ከዚህ ይልቅ ህገ መንግስቱን ለሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮች እንደ መፍትሔ ማፍለቂያ መጠቀም ይገባል። በተለይም በአጎራባች ክልሎች ውስጥ ሰነከባለሉ በመጡ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና በግጦሽ ሳቢያ የሚፈጠቱ ችግሮችን በህገ መንግስቱ አግባብ መፍታት ይገባል።

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ህብረ ብሔራዊ ሆኖ መዋቀሩ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተመቸ ከመሆኑም በላይ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ማንነቶችንና የጋራ እሴቶችን እያጎለበቱ መምጣታቸውን ያሳያል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አዲሱ ሥርዓት ከተመሠረተ ወዲህ በተወሰኑ አካባቢዎች በጎሣዎች መካከልና በአንዳንድ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ፌዴራል አወቃቀሩ የፈጠራቸው አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም፡፡

ዛሬ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ መጠነኛ ግጭቶች ቢኖሩም በመላ አገሪቱ የተረጋገጠው ሰላም አለ። ይህም የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንዲኖር በማስቻሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት መላ አቅማቸውን አቀናጅተው በድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ መዝመታቸው የሥርዓቱ ስኬቶች አንዱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ መብቶች ስለተመለሱላቸው ሀገራቸውን ለመለወጥ እንደ አንድ ማኅበረሰብ በልማት አጀንዳዎች ላይ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ህገ መንግስቱ የሰላም ዋስትና መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡  

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት አገራችን የምትከተለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለት፣ አካላቸውን ያጡለትና ለተግባራዊነቱም የተረባረቡለት ነው። ይህ ዕውነታም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተስማምተው ያፀደቁትና የሉዓላዊ ሥልጣናቸው ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት እነዚሁ ህዝቦች እስካሉ ድረስ ፈራሽ የሚሆንበት ምንም ዓይነት ዕድል አለመኖሩን የሚያመላክት ነው።

ከዚህ ይልቅ የሀገራችን ህዝቦች በሙሉ ፈቃደኝነታቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ በሀገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን እየፈቱበት የሀገራችንን አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በመፍትሔነት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ሆኗል።

ይህ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎት ልክ እንደ መቃወም መብት ሁሉ ህገ መንግስታዊ መብት ነው። ይህ መብትም በጥቂቶች ፍላጎት የሚቀለበስ ሊሆን አይችልም። እናም ህገ መንግስቱን የማሻሻልም ይሁን የመተው አሊያም የማፅናት መብት የሀገራችን ህዘቦች እንጂ የጥቂት ፅንፈኞች ፍላጎት ሊሆን አይችልም። እርግጥ የሀገራችን ህዝቦች እስካሉ፣ ብዝሃነታቸውን ህገ መንግስቱ እስካረጋገጣላቸው ድረስ ሥርዓቱ ዘላቂ ይሆናል።

ምንም እንኳን አንዳንዶች በብሔርና በጎሳ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም፤ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን ከእነርሱ ምልከታ የተለየን ሁኔታ ነው። ብዝሃነት የመጪው ዘመን ዕድላችን በር መክፈቻ ሆኗል።

ሆኖም በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ብዝሃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ ትምህርት ሰጥተው አልፈዋል።

በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የብዝሃነት አያያዝ ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል። በዚህም ብዝሃነት በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ ሊሆን ችሏል።

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የብዝሃነት መሰረቶች የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሶሶና ማገር ናቸው። መሰረቶቹም በስርዓቱ የፖለቲካ ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ናቸው።  በኢፌዴሪ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አካሄድም ይህንኑ ሃቅ የሚደግፍ ነው።

የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት በብዝሃነት ውስጥ ላሉ ማንነቶች የሰጠው መብት ከብዙ ፌዴሬሽኖች ጋር ሲነጻጸር የላቀና ብዙ ማንነቶች ላሏቸው አገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል። የተለያዩ አገራት ተወካዩች አገራችን ውስጥ እየመጡ ስለ ፌዴራላዊ አወቃቀራችንና አሰራሮቹ ልምድ የሚቀስሙት ለዚሁ ነው።

የአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ገፅታው ይህ ከሆነ ዘንዳ ሥርዓቱን ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ የብጥብጥ ሃይሎችን ማጋለጥ ያስፈልጋል። እነዚህ የብጥብጥ ሃይሎች በትምክህትና በጥበት ሠረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች የታወሩ ዘረኞች ናቸው።

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የትምክህትና የጥበት ኃይሎች በቅርቡ በጥብቅ የሚያቆራኛቸውን ነገር አግኝተው ፍቅራቸው ጣራ መንካቱን እናስታውሳለን፡፡ ይሁን እንጂ ትምክህትና ጥበት አምሳያዎች ቢሆኑም በአንድነት መስራት ስለማይችሉ አንደኛው ራሱን የበላይ በማድረግ መብት ለሌላኛው ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ‘የእገሌ ብሔር ልሂቃን’ እያለ ስም በማውጣት በማንነት ጥያቄዎች ላይ ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ ጥንብ እርኩሱን ሲያወጣ ይስተዋላል።

ይህ የወል የመተቻቸት በሽታቸውም በጋራም ሆነ በተናጠል ብዝሃነት መለያዋ በሆነች ታላቅ ሀገር እንዳይኖሩ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ በአንድ ወቅት “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል እሳቤ በሽብር በአመፃ አውድማ ላይ ተሰማርተውና በጥፋት ጋብቻ ተጣምረው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መገለጫ የሆነችውን አገራችንን ለማተራመስ ሞክረው ብዙም ሳይቆዩ አንዱ በሌላኛው ላይ ጣቱን ለመቀሰር በቅቷል፡፡ ያም ሆኖ እነዚህን የብጥብጥ ሃይሎች ማጋለጥ ያስፈልጋል።

የትምክህትና የጥበት ሃይል ተግባሩን የሚፈፅምበት መንገድ ይታወቃል። ይኸውም የሆነ አጋጣሚን እንደ ምክንያት ወስዶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመቀየር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ብጥብጥን መፍጠር ነው። ይህን ሃቅ ህብረተሰቡ ማወቅ አለበት። አውቆም ከውስጡ እያንጓለለ በማጋለጥ ሰላሙንና ዕድገቱን ማሳለጥ አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy