Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መግለጫው ወደተግባር ይለወጥ

0 486

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መግለጫው ወደተግባር ይለወጥ

                                                          መዝገቡ ዋኘው

የሀገርን ታላቅነት የሚመሰክረው የመሪዎችና የሕዝብ ተናቦ መስራት መቻል ነው፡፡ መንግስትና ሕዝብ በአንድነት ሆነው፣ ነገን ከዚያም አልፎ መጪውን ትውልድ ያማከለ ራእይን ሰንቀው፤ ራእያቸውንም በጋራ ከውነው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን ሲሰሩ ሀገር ትለማለች፤ ትበለፅጋለች። በስኬቱም ህዝብ ደስተኛ፤ በመንግስትም የሚተማመን፤ በሀገሩም የሚኮራ ይሆናል፡፡

ዜጎች በመሪዎቻቸው ደስተኛ ካልሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትሕ እጦት፣ የሙስና፣ የጎጠኝነትና ዘረኝነት ችግሮች ፈጠውና ገጠው ከወጡ ህዝባዊ ቁጣ ይከሰታል፤ ያኔ ተቃውሞዎች በፈርጀ ብዙ መልኩ ይገልጻሉ፡፡ ግጭትና አለመረጋጋት ይከሰታል፡፡ በሀገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው፡፡

በአሁኑ ሰአትየህዝባዊ ቁጣውም ሆነ የግጭቶቹ መሰረታዊ መንስኤ በውል የታወቀ ከመሆኑ አኳያ መፍትሔው ችግሮቹን በመሰረታዊነት መፍታትና እልባት መስጠት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የሀገሩ ባለቤት መሪዎች አይደሉም፤ ሕዝብ ነው፡፡ መሪዎች በታሪክ ውስጥ ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ መሪዎች በዚች በተወሰነች የሰውኛ ዘመናቸው ለሀገርና ለትውልድ የሚበጅ፤ ምንግዜም በትውልድ ውስጥ ፈርጥ ሁነው የሚታወሱበት፤ አሊያም ሲነቀፉና ሲወገዙ የሚኖሩበትን ስራዎችን ሰርተው ሊያልፉ ይችላሉ፡፡

መሪዎች ምንም ሆኑ ምንም ከሕዝቡ ውስጥ የወጡ እንደመሆናቸው መጠን ከስራቸው  በተለያዩ ምክንያቶች  (በሕመም፣ በጡረታ፣ በሞት ወዘተ) ይነሳሉ፡፡ ይህ የተፈጥሮ ግዴታ ብቻ ሳይሆን፤ ከታሪክም የተማርነው እውነታ ነው፡፡ ሀገርና ሕዝብ ግን በማይቋርጥ የትውልድ ፍሰት ውስጥ ይተማሉ፡፡ ከአለም ተጨባጭ እውነታ የተገነዘብነው አቢይ ቁም ነገር ቢኖር ሀገራቸውን ለታላቅ እድገት፣ ልማትና ብልፅግና ያበቁ መሪዎች ሰፊ ራእይ የነበራቸውና ራእያቸውንም በማሳካት ህዝባቸውን በታማኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ መሆናቸውን ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የቆሙት ግን የሀገርና የሕዝብ ጠንቅ ከመሆናቸውም ባለፈ በታሪክ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡

የእነዚህ አይነት፣ ከህዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የቆሙ መሪዎችም ሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራር ተብዬ ሀላፊዎች፤ የሕዝብን ታላቅነትና ታሪክ ሰሪነት ሽረው፤ “ታሪክ ሰሪም መሪም እኛ/እኔ እና እኛ/እኔ ብቻ ነን/ኝ” በማለት በጠበበ አእምሯቸው የሚያሰሉ ጠባብ ቡደኖችና ግለሰቦች መቀፍቀፍና በየቢሮክራሲው መሰግሰግ ህዝብን ያስቆጣል፤ ሕዝባዊ ብሶትና ቁጣንም ይወልዳል፤ አገርን ከማቆርቆዝ አልፎ በህዝቦች መካከል ያልተፈለገ ጎጠኝነትና ዘረኝነትን በማስፋፋት ህዝብን ከህዝብ ያጋጫል፡፡ አብሮ የኖረ፤ የተዋለደና በደም የተሳሰረ ህዝብ ደግሞ ጎጠኝነትንና ዘረኝነትን አምርሮ ይጠላል፡፡ እንደማይበጀው ያውቀዋልና ይጠየፈዋል፤ ይዋል ይደር እንጂ የችግሩ ባቤቶችን በተባበረ ክንዱ ይቀጣቸዋል።

በታሪክ ውስጥ ድርጅቶችም ግለሰቦች በአንድ ወቅት ይነሳሉ፤ ይወድቃሉም፡፡ እንደነዚህ አይነት አስተሳሰብና አመለካካት ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች ታላቅና የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች እናትና አለኝታ የሆነችን ሀገር በተስተካከለ፣ ሚዛናዊነት ባለው ቁመና ሊመሩ አይቻላቸውም፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ ቁጣው የሚነሳውም ከዚሁና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት በየቦታው ያሉ ግጭቶችም መነሻ ምክንያቶች ሕዝቡ መሰረታዊ መብቱ በመነፈጉ፤ በስሙ የሚምሉና የሚገዘቱ አጭበርባሪዎች መሬቱን ዘርፈውና ቸብችበው ሜዳ ላየ ስለጣሉት ነው። ይህ ግፍና  በደል ሞልቶ ሲፈስ ደግሞ ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማንም ታዛቢ ከግልፅም በላይ ግልፅ ነው፡፡

የግጭቶቹም ሆነ የህዝባዊ ብሶቱ ዋነኛ መነሻ ሙስና አይሎና ገኖ የሕዝብን ሀብትን ተቀራምቶ፣ በቡድን ተደራጅቶ በመዝረፍ መክበር ከመጀመሩም በላይ፤ የሕዝብን መብትና ነጻነት፣ የፍትሕን ኃያልነት ረግጠው ባሻቸው የሚፈነጩ ነውረኞች ሞልተው በመትረፍረፋቸው ብቻ ሳይሆን፤ ተወልዶ ካደገበት ቀኤ እያፈናቀሉ እነሱ ባለመሬት፣ ባለሀብትና ንብረት ለመሆን ሲበቁ፤ በተፃራሪው ሕዝቡ በልማት በሽፋን ከቀኤው እንዲነሳ እየተደረገ መልሶ መሬቱን ጥቂት ባለሀብቶች እየገዙት ዜጎች የሰውኛና የዜግነት መብታቸው ተገፎ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሀገራቸውን እስከማማረር የደረሱበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። መፍትሄውስ? መፍትሄው የሕዝቡን ጥያቄ በሚገባው ልክ መመለስ ሲሆን፤ ይህንንም እንደሚያደርግ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ በሚገባ የገለፀ ሲሆን፤ የቀረው ነገር ቢኖር ተግባራዊ ማድረጉ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ወደፊት፤ በቅርቡ የምናየው ይሆናል።

በብዙዎች ተደጋግሞ እንደተገለፀው የግጭቶቹ ሁሉ መነሻ ምክንያት የጥቅም ግጭት ነው፤ የጥቂቶች መበልፀግና የብዙሀኑ ተጠቃሚ አለመሆን፡፡ ትናንት ምንም ያልነበራቸው፤ በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎች ከምንም ተነስተው ከየት አመጡት በማይባልበት ሁኔታ ሚሊየነርና ባለሰማይ ጠቀስ ፎቅ ባለቤት፣ አስመጪና ላኪ፣ ባለብዙ ምናምን የሆኑባት፤ በምድራችን አስገራሚ ሀገር ብትኖር የእኛዋ ኢትዮጵያ ነች ቢባል ተቃዋሚ የሚኖር አይሆንም፡፡ ይህም ሁኖ ሕዝብ የማያውቅ ይመስል አይናቸውን በጨው አጥበው ያለማፈር ስለዲሞክራሲ፣ ስለሕዝብ እኩልነት ወዘተ ሲደሰኩሩ መስማት ያማል፤ ሕዝብንም መናቅ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሌቦችን ሌቦች ብሎ በአደባባይ በሕዝብ ፊት ለሕግ እስካላቀረበ ድረስ አሁንም ችግሩ በቀላሉ የሚፈታ አይሆንም፡፡

የሕዝቡ ጥያቄ አጭርና ግልፅ ሲሆን፤ እሱም የመንግስትና የሕዝብን ሐብትና ንብረትን የመዘበሩ ሙሰኞች፤ ህዝብን ከህዝብ ያጋጩ ሴረኞችና ለንፁሀን ዜጎች ደም መፍሰስና ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ አካላት ባስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ የሚል ነው፡፡ ህዝቡ እያለ ያለው እነሱን ተሸክሞ ስለሰላምና እድገት ማውራት አይሞከርም፤ ሊታሰብም አይገባውም ነው፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ ለተፈጠረው ቀውስና አለመረጋጋት ዋነኛው ምክንያት በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች የፈጠሩት ቅጥ ያጣ፣ በስግብግብነት የተሞላ ዘረፋ መሆኑን፤ ይህም፣ ውሎ አድሮም ቢሆን፣ የአመራሩ ችግር እንደሆነ “በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅቱ አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን” በማለት ስህተቱን ተቀብሏል፤ ያሉትን ችግሮችም ሆነ የተፈጠሩትን ግጭቶች ለመፍታት ሳይቦዝን እንደሚሰራም ጭምር፡፡

ኢሕአዴግ በውስጡ፣ በድርጅቱ/በየድርጅቶቻቸው ውስጥ ተጠልለው በሕዝብ ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል በደልና ግፍ የፈጸሙትን፤ አይን ያወጣ ዘረፋ ሲያካሂዱ የነበሩትን ዘራፊዎች እያጋለጠ በሕዝብ ፊት ለሕግና ለፍትሕ ማቅረብ ካልቻለ ችግሩ እየከፋ ስላለመሄዱ ማረጋገጫ የለም። ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ከተፈለገ የተፈጠረውንና ሄድ መለስ የሚለውን ግጭትና የሰላም እጦት ለማስቆም ወገቡን አስሮ መስራት ይጠበቅበታል፤ ያለውም ምርጫ ይሄውና ይሄው ብቻ ነውና፡፡

ሕዝቡን በየወቅቱ ስብስቦ ማነጋገሩ ራሱን ችሎ መልካም ቢሆንም ህዝቡ ግን ምንም የምንጠብቀው አዲስ ነገር የለም የሚል ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ ከፓርቲው መግለጫ መረዳት እንደተቻለው ለስርአቱ አደጋ ሆነው የመጡት በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ በግል ጥቅም ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አመራሮች ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ ለሀገርና ለሕዝብ ልማትና እድገት በታሪክ ግዙፍ ሁነው የተመዘገቡ ስራዎችን የሰራ ድርጅት ነው፡፡ ይህንን ስራውን በማቆሸሽ ከሕዝብ ጋር ያላተሙትና ድካሙን መና ለማስቀረት እየሰሩ ያሉት ደግሞ የራሱ፤ የኔ ያላቸው ሰዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ አመራሮች በሕዝብ በደል፣ ግፍ፣ ጭቆና፣ አድሎአዊነት፣ ጎጠኝነት፣ ዘረኝነት ወዘተ ሲፈጽሙ የመቆየታቸው ምክንያት ነው ሕዝቡን ለመመረርና ለመንገሽገሽ ያበቁት፡፡

ሰው ተባብሮ ሀገሩን ያለማል እንጂ ጎሳና ዘሩን እየፈለገና እየመረጠ ወንበርና ሀብት የሚያድል ከሆነ ሀገር አለ(ኝ) ብሎ ማውራትም ሆነ መናገር ይከብዳል፡፡ ሁሉም በየፊናው እንዲህ በማድረግ ላይ ከተጠመደ ይሄንን በአይኑ ያየውና የሚያውቀው ሕዝብ ግጭት ውስጥ ቢገባ ሰላም፣ ቢደፈርስ ተጠያቂው አመራሩ እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ያልነበረ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ በየትኛውም ጠርዝ ሄዶ ሰርቶ አግብቶ ተዋልዶ በክብር ይኖርባት በነበረች ሀገር ውስጥ ዛሬ ከክልሌ ውጣ ከመንደሬ ልቀቅ ያፈራሀው ሀብት ከእኛ መሬት የተገኘ ነው ይዘህ አትሄድም የሚል ዘግናኝ ሀገራዊ በሽታ እንዲስፋፋ ያደረጉት እነዚህ ወገኖች/አመራሮችና ተከታዮቻቸው ናቸው ለዛሬው የከፋ ችግር ተጠያቂዎቹ፡፡

የፖለቲካ እብደትና ስካር መዳኛ የሌለው በሽታ ነው፤ ካላጠፋ አይቆምም፡፡ አሁንም ይህን በሽታ የተሸከሙ አመራሮችን ይዞ  በሀገር ደረጃ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ መጠበቅ መሞኘት ከመሆን አይዘልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዘብ ትላንት የመጣ፤ የተፈጠረ  አይደለም፡፡ ብዙ ሺህ ዘመናትን በጎዉንም ክፉዉንም ቀን አብሮ አሳልፎአል፡፡ በደም፣ በአጥንት፣ በስጋ ከሰሜን – ደቡብ፣ ከምስራቅ – ምእራብ ድረሰ ተቀላቅሎአል፡፡ ይሄንን ሕዝብ ለየትኛውም የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ለመለያየት መሞከር ትርፉ ተንገዋሎ መቅረት ነው፤ በታሪክ ተጠያቂ የመሆኑ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ።

በአሁኑ ሰአት እዚህም እዛም እየታዩት ያሉት ግጭቶች መሰረታዊ መነሻቸው የሕዝብ ብሶትና የፍትህ እጦት፣ የሰብአዊ መብት መረግጥ፣ ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነት እጦት፣ ብልሹ አመራር/አሰራር፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት የወለደው በሽታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ አገራት እንደታየው፣ የሀገርን ሰላምና ደሕንነት፣ የሕዝብን አብሮነት የሚንድ ከመሆንም አልፎ የከፋ አደጋን ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ከዚህ አደገኛ አዙሪት ፈጥነን መላቀቅ ካልቻልን ሁኔታው ወደ ባሰ አዘቅት እንዳያመራ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ዛሬ እንደ ቀላል የሚታየው ነገር ነገ ሀገራዊ አጣብቂኝ ውስጥ ሊከተንና መፈናፈኛ ሊያሳጣን ይችላል፡፡ የኢኮኖሚ ድቀትና ቀውስም ሊያስከትል ይችላል፡፡

በመሆኑም መንግስትና ገዥው ፓርቲ በገቡት ቃል መሰረት ባስቸኳየ ወደ ችግር መፍታቱና ህዝብን ማረጋጋቱ ስራ ሊገቡ ይገባል። ለዚህም ህዝቡና ላገር እናስባለን የሚሉ ወገኖች ሁሉ ከጎኑ ይቆሙ ዘንድ ወቅቱ ግድ ይላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy