Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መጠናከር የሚገባው ችግሮችን የመቅረፍ ሂደት

0 596

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መጠናከር የሚገባው ችግሮችን የመቅረፍ ሂደት

                                                        ዘአማን በላይ

ጥልቅ ተሃድሶው ሲጀመር ህዝቡን እያማረሩ ያሉ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተነቅሰው መለየታቸው ይታወቃል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል የተወሰኑት በመቀረፍ ላይ ናቸው። ችግሮቹ አፈፃፀማቸው ሲታዩ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም፤ በአብዛኛው ሲታይ ግን የህዝብን እርካታ ለማምጣት ብዙ መስራት የሚጠይቅ መሆኑ ግልፅ ነው። ህዝብን ከሚያማርሩ ችግሮች ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል። ታዲያ ይህን ችግር ለመቅረፍ በጥልቅ ተሃድሶው መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ብዙ ስራዎችን አከውኗል።

መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አንድ መርህ እንደመሆኑ መጠን፤ የሀገራችን ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ በሁሉም ደረጃዎች የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲቋቋሙና እንዲጠናከሩ፣ የዳበረ የፍትህ ስርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት፣ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላት ውስጥ የግልፅነት፣ የተጠያቂነትና የህዝብ አገልጋይነት መርህ እንዲሰፍንና የተግባር መመሪያ እንዲሆን ብሎም በሁሉም መስኮች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ብርቱ ጥረት መደረጉ አይታበይም።

ሆኖም የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ህብረተሰቡን በቀጥታ የሚነኩ ከመሆናቸው በላይ፤ የችግሮቹ መንስኤዎች ውስብስብ ናቸው። አንዳንዶቹ የአመለካከት ጉዳይ ያለባቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎችና ጥገኞት እንዲፈጠሩ የሚቆሰቁሷቸው እንዲሁም ዕድገቱ ከፈጠረው የፍላጎት መናር ጋር ተያይዘው የሚታዮ ይመስለኛል።

ከአመለካከት አኳያ የመንግስት ስራ አስፈፃሚ የሆኑ አካላት የመንግስትን ስልጣን የያዙት ለራሳቸው መገልገያነት አስመስለው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። በዚህም ኪራይ ሰብሳቢነት እየገነገነ ሄዷል። የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ሀገራችን እንደ ህልውና ጉዳይ የያዘችውን ከድህነት የመውጣት ራዕይዋን የሚያሰናክል አሜኬላ እሾህ ከመሆን በዘለለ፤ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን ላይ የሚፈጥረው አደጋ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ስለምትገነዘብ ነው። መንግሰት ከዚህ ሀገራዊ የህልውና ጉዳይ አንድምታ በመነሳት ኪራይ ሰብሳቢነትን በአጠቃላይ፣ ሙስናን ደግሞ በዋነኛነት በመዋቅሩ ውስጥ የሚገኙት የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎቶች ሁለንተናዊ ሁኔታን ተላብሰው ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የህዝብ አገልጋይነት እንዲሰፍን ትግ ጀምሯል። ትግሉ ግን አሁንም ካሉት ውስብስብ ሁኔታዎች አንፃር በበቂ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ለማለት አያስችልም።

ባለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡት ስነ-ልቦናዊ ጫናዎች፣ ሁለትም ዴሞክራሲያችን ገና በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ከጉዳዩ ግንዛቤ አኳያ የዳበረና በተጠያቂነት ብሎም በግልፅነት ሊሰራ የሚችል የመንግስት አስፈፃሚ አካል አለመኖር የፈጠሩት ችግሮች የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ይመስለኛል።

እናም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ መንግስትንና ህዝብን በቀጥታ የሚያገናኝ በመሆኑ ሁለቱም አካላት በየፊናቸው የበኩላቸውን መፍትሔዎች መውሰድ ይኖርባቸዋል። መልካም አስተዳደርን ዕውን ከማድረግ አኳያ በዋነኛነት ሊያጋጥም የሚችለው ችግር የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ነው።

የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ የሆኑትን ጠባብነት፣ በጎሳ በዝምድና እና በጥቅም ላይ የተመሰረተ የቡድንተኝነትና የኔትወርክ ትስስርን ማዳከም ብሎም ማክሰም የልማታዊው መንግስታችን ወሳኝ እርምጃ መሆን አለበት።

የእያንዳንዱ አስፈፃሚ መስሪያ ቤት የምደባ መስፈርት በሰራተኛውና በህዝቡ በግልፅ እንዲታወቅ ብቻ ሳይሆን፣ የመስሪያ ቤቱ ባለቤት የሆነው ግብር ከፋዩ ህዝብ እንዲተችበት ማድረግ ይገባል።

ይህም በህዝብና በመንግስት መካከል ማናቸውን ተግባራት ተመካክሮ ለመስራት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፣ ህዝቡ በመንግስት ላይ ይበልጥ አመኔታ እንዲያሳድር ያደርጋል።   

እነዚህ ተግባራት በአንድ ጀምበር የሚፈፀሙ አይደሉም። በአስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም ተገልጋዩ ህዝብ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል። በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ውስጥ የሚገኙ አመራሮች፣ ሰራተኞችና የህብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ ወቅት የሚዲያ ዘገባ ብቻ ከአስተሳሰባቸውና ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደማይቻል ግልፅ ነው።

ርግጥ ባለፉት ስርዓቶች ሲገለፁ የነበሩት ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በአንድ ጀንበር ስለማይፈቱ እነዚህ ሁኔታዎች ለፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በበቂ ሁኔታ አለመፈፀም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ይመስለኛል።

ሙስናን የማይጠየፍ፣ ይልቁንም ለሙስና የተለየ ትርጉም በመስጠት “በልተህ አብላኝ” የሚል አስተሳሰብ የበላይነት ባገኘበት ወቅት ይህን ጉዳዩን በበቂ ሁኔታ መታገል የሚያስቸግር ይመስለኛል።  

በሌላም በኩል ጥገኞችና ኮንትሮባንዲስቶች የሚፈጥሩት ችግር የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚፈለገው መጠን እልባት እንዳያገኙ የሚያደርጉ ናቸው። በጥገኝነትና በኮንትሮባንድ ስራ ውስጥ የሚናኙ ሃይሎች በየአካባቢው ጥቃቅን ችግሮችን በመፍጠር፣ አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር በማጋጨት አላስፈላጊ ጥቅምን ለማጋበስ የሚያደርጉት ጥረት መልካም አስተዳደር እውን እንዳይሆን ማነቆ ሆኗል።

የኢፌደሪ መንግስት በሚከተለው ልማታዊ መስመር የሀገራችን ዕድገት እየተሳለጠ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ዕድገት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የገንዘብ ተቋማት ጭምር ሳይቀር የተረጋገጠ ነው። ዕድገቱ በሁሉም ዘርፎች ፍላጎቶችን እያናረ ነው።

የተለያዩ የኢንዱስትሪ መንደሮች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተገነቡ መሆናቸው የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ጨምሯል፣ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ እየተለወጠ በመሆኑ የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች ፍላጎት እየጨመሩ ነው። ሌሎች…ሌሎችም።

እነዚህ ሁሉ የፍላጎቶች መናር በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የራሳቸውን ጫና መፍጠራቸው አይቀርም። የሚፈጥሩት ጫና ግን አገልግሎቶቹን በጥራትና ተደራሽ በሆነ ሁኔታ መፍታት የሚቻል ነው። ያም ሆኖ ግን በጊዜያዊነትም ቢሆን እነዚህ ችግሮች በመልካም አስተዳደር ጉዳይ እንደ ተግዳሮት መቅረባቸው አይቀርም። እናም ችገሮቹን በዘላቂነት መፍታት ይገባል።

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በመንግስት ወይም በተገልጋዩ ህዝብ ላይ ብቻ ከተወረወረ ውጤት ሊገኝ አይችልም። እየታዩ ላሉት ችግሮች መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል። ቀደም ሲል የተገኙትን ድሎች ይበልጥ በማጠናከር መንገስትም ይሁን ሀብረተሰቡ በበለጠ ሁኔታ እጅ ለእጅ መጓዝ ይኖርባቸዋል። ማናቸውንም ችግሮች ለመፍታት “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን ሀገራዊ ብሂል እያስታወስን ከተጓዝን የማንወጣው ዳገት የማንወርደው ቁልቁለት ሊኖር አይችልም።

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy