Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹ማባሪያ የሌለው መንደርተኝነትና ጎጠኝነት እየረበሸን ነው››

0 431

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አባተ ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

የወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. ብቻ 25 ሺሕ ተማሪዎችን በመደበኛውና በኤክስቴንሽን ፕሮግራም በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ አንድ ሺሕ መምህራንና አንድ ሺሕ አምስት መቶ የአስተዳደር ሠራተኞችን ይዞ የማስተማር ሥራውን እያከናወነ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እሑድ ታኅሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተካሄዶ በነበረው የአማራና የኦሮሞ ምሁራን ኮንፈረንስ ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) ተገኝተው ነበር፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ዕጩ ምሩቃን ከመመረቃቸው በፊት የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱ ካሳወቀበት ጊዜ ጀምሮ፣ በአብዛኛው በዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ፈተናውን አንወስድም በማለት እየተቃወሙ ናቸው፡፡ በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በተጣበበ ጊዜ ዘመኑ ተናኘ ከዶ/ር አባተ ጌታሁን ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2011 ዓ.ም. ይሰጣል ከተባለው የመውጫ ፈተና እንጀምርና ተማሪዎች ቅሬታ እያነሱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን በመቃወምም ትምህታቸውን ጥለው የወጡ ተማሪዎች እንዳሉና የመማር ማስተማር ሥራቸውን ያቋረጡ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ዶ/ር አባተ፡- ሁለቱ ነገሮች ፈተና እየሆኑብን ነው፡፡ አንዱ ሦስት ዓመት የነበረው አምስት ዓመት፣ አምስት ዓመት የነበረው ሰባት ዓመት ሆኗል የሚባለው አሉባልታ ነው፡፡ ሁለተኛው ሲኦሲ የሚባለው የመውጫ ፈተና ነው፡፡ በእኛ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎች የምንኮራባቸው ናቸው፡፡ እንዲያውም በጉጉት ነው የሚጠብቁት፡፡ የመውጫ ፈተና የሚያስፈራ አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ አስፈሪ በሆነ መልክ አቀረቡት፡፡ ዓመቱ ጨምሯል የተባለውም ውሸት ነው፡፡ የውሸት ሪፖርቶች በመኖራቸው ምክንያት ተማሪዎች ፍርኃት ውስጥ ገብተዋል፡፡ እኛ እንድንጋጭ የሚፈልጉ አገሮች ሊያጋጩ የሚችሉበት አንደኛው ሥፍራ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የሚያጋጩት ደግሞ በብሔር ነው፡፡ ሌላው እምነት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አሉባልታ በመንዛት ማለት ነው፡፡ ሁላችንም ላይ ይህ ነገር ተነስቶ ነበር፡፡ እኛ ጠንካራ የሆነ የተማሪ ፖሊስ አለን፡፡ ኅብረ ብሔራዊ የሆነ፡፡ እኔ በየስድስት ሰዓቱ ሪፖርት እቀበላለሁ፡፡ በእኩለ ሌሊት ሳይቀር እኔ ራሴ እገባለሁ፡፡ ችግር እንዳይከሰት በቅርበት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሔርን መሠረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ይህ ጉዳይ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ምን ይመስላል?

ዶ/ር አባተ፡- ፈታኝ እየሆነብን ያለው ጉዳይ ይኼ ነው፣ ጎጠኝነት ነው፡፡ ሁለት ተማሪዎች ወይም ጓደኛሞች መቀላለድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እንደ አገር ልንሠራበት የሚገባው ጉዳይ ይህ ነው፡፡ እናንተም የሚዲያ አካላት ልትሠሩበት የሚገባ ነው፡፡ በአንድ ኦሮሞ ወይም በአንድ ትግሬ፣ በአንድ አማራ ወይም በሌላ መካከል መቀላለድ ከባድ ሆኗል፡፡ ሌላው ጠልፎ ለሌላ ዓላማ ይጠቀምበታል፣ ይጠቁምበታል፡፡ ትልቁ ሥፍራ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ነው ያለው፡፡ እኛ ጋ አሁን የመደበኛውንና የኤክስቴንሽኑን ጨምሮ 25 ሺሕ ተማሪዎች አሉ፡፡ ከሁሉም ፈተና የሆነው ጎጠኝነት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ሊፈታ የሚችል አካል ታጣለህ፡፡ ሁሉም በጎሳው፣ ሁሉም በብሔሩ ይሸጎጥብኃል፡፡ ሰው ላይ እየሠራን አይደለም፡፡ ሰው መሆን በቂ ነው፡፡ ሰው በሚለው ነገር ላይ አልሠራንም፡፡ እባካችሁ እናንተም ሥሩበት፡፡ ሰው በብቃቱ ሳይሆን በጎጡ እየተሸጎጠ እያስቸገረን ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ችግር ለመፍታትና ድርሻችሁን ለመወጣት ምን እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር አባተ፡- በዚህ ሴሚስተር ያደረግነው ነገር መጀመርያ ተማሪዎች ሲመጡ በብዝኃነት ላይ፣ በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ላይ፣ በዴሞክራሲያዊ አንድነት ላይ ብዙ ውይይቶችን አድርገናል፡፡ ይኼንን ለማስተናገድ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ማስታወቂያ አውጥተን ኦሮሚኛ፣ ትግርኛና ሌሎች በርከት ያሉ ቋንቋዎችን እያስተማርን ነው፡፡ ብዝኃነት በተግባር እንዲረጋገጥ እየሠራን ነው፡፡ ዘንድሮ ለመምህራንና ለተማሪዎች ብዝኃነትን እንዲያስተናግዱ፣ አንድነት ልዩነትን፣ ልዩነት አንድነትን እንዳይጨፈልቀውና እንድንቻቻል ትምህርት እየሰጠን ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መፍትሔው ክላሽ አይደለም፡፡ ያለንበት ዘመን የኮሙዩኒኬሽን ዘመን ነው፡፡ እዚህ ላይ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር፣ ታዋቂ ብሎግረስ ከሚባሉት ጋር በብዝኃነትና አንድነት፣ እንዲሁም በዴሞክራሲዊ ብሔርተኝነት ላይ እየሠራን ነው፡፡

በእኛ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያላችሁ ሐሳብ ምንድነው ብለን አንድ ቀን ሙሉ ውይይት አደረግን፡፡ ማንም ሰው ሳይገለል ውይይት አድርገናል፡፡ ለዚች አገር ምንድነው መፍትሔዋ? ብዝኃነትና አንድነት ነው ወይስ መነጣጠል ነው? ወይ ሌላ እስኪ ያላችሁን መፍትሔ አምጡ ብለን ተወያይተናል፡፡ በጣም የሚገርም ውይይት ነበር፡፡ ይህን ለማስተካከል ኅብረተሰቡ ባለቤትነትን ይዞ እንዲሠራ ማስተማር ነው፡፡ ባለፈው ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የተደረገውን የትስስር መድረክና የአሁኑን የሁለቱን ክልሎች የምሁራን ውይይትም አንድ በአንድ ወስደን እንወያይበታለን፡፡ እኔው ራሴ ጽሑፍ አቀርባለሁ፡፡ በአንድ ቀን ሁለት መድረኮች አካሂደናል፡፡ በመልካም አስተዳደር እሴት ግንባታ ላይ ሁለት ጽሑፎችን አቅርቤያለሁ፡፡ እንዲህ እያደረግን ነው መሄድ ያለብን፡፡ ማስተማር፣ ማስተማር፡፡ ይህ ነው መፍትሔው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡   

ሪፖርተር፡- እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መሠራት ያለባቸው ሌሎች ጉዳዮች ምንድናቸው ይላሉ?

ዶ/ር አባተ፡- ሚዲያው ልዩነት ላይ ሳይሆን አንድነት ላይ መሥራት አለበት፡፡ ጥቅጥቅ ካለ ጨለማ ውስጥ ትንሽ ብርሃንን እያየ፣ ያንን ብርሃን የሚያጎላ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ በእኛ አገር ጨለማን ነው የሚያጎሉት፡፡ ወደኋላ እያዩ ወደፊት መሄድ አይቻልም፡፡ ወደኋላ እየተመለከትህ ልትሄድ አትችልም፡፡ ስለዚህ ወደኋላ በርካታ ታሪኮች ይኖራሉ፡፡ ጠንካራም፣ መጥፎም ታሪኮች አሉ፡፡ ለማንም የተሰጡ አይደሉምና ወደ ኋላ ከሠራናቸው ሥራዎች ጥሩዎችም መጥፎዎችም ታሪካችን ናቸው፡፡ አንንቃቸውም፡፡ እነሱ ላይ ሳናተኩር ወደፊት መጓዝ ከጥቅጥቅ ጨለማ ወደ ብርሃን እየሄድንና ብርሃኑ ላይ እያተኮርን፣ ጨለማውን እየተውን ብንሄድ ጥሩ ነው፡፡ ዓለም ዛሬ ከስድስት ሺሕ እስከ ስምንት ሺሕ ሊሆኑ የሚችሉ ቋንቋዎችና ባህሎች አሏት፡፡ ልዩነትንና አንድነትን አስታርቀን የማንሄድ ከሆነ ከአንተና ከእኔ ይጀመራል፡፡ አንድነትና ብዝኃነትን ማስተናገድ ካልቻልን ግጭት የሚጀምረው ከራሳችን ነው፡፡ ይህንን በአግባቡ ማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ሚዲያ በዚህ ላይ ቢሠራ ጥሩ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያሳዝነኛል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ብንጀምር ‹የብዝኃነትና የህዳሴ ድምፅ› ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? ልዩነት ውበት ነው ካልን ልዩነት ለአንድነታችን መሠረት ነው፡፡ ይኼ ማጠንጠኛችን ነው፡፡ ”ዩናይትድ አሜሪካንስ” የሚለው ደስ ይላል፡፡ ‹‹ዩናይትድ ዊ ስታንድ ዲቫይድድ ዊ ፎል›› ይላሉ፡፡ የተከፋፈለች ከተማ አትረጋም ለማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ብንሠራ፡፡ ይህንን ካልሠራን ማንም አሸናፊ፣ ማንም ተሸናፊ አይኖርም፡፡ ዛሬ የሕዝብ ብዛትና የተፈጥሮ ሀብት አይደለም ወሳኙ፡፡ አንድነትህንና ልዩነትህን አክብረህ የሰላም አርበኛ ስትሆን ነው አገር የምታድገው፡፡ እልህ አያስፈልግም፡፡ ተሸንፎ ማሸነፍ እንማር፡፡ ተሸንፎ ማሸነፍን ከተማርን አገር እንገነባለን፡፡ በዩኒቨርሲቲያችን እያየን ያለነውም በሃይማኖትም፣ በጎጥም፣ በመንደርም የመከፋፈል አዝማሚያ ነው፡፡ ማባሪያ የሌለው መንደርተኝነትና ማባሪያ የሌለው ጎጠኝነት እየረበሸን ነው ያለው፡፡ መንግሥትና ሚዲያውም አብረን እንሥራ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም አብረን እንሥራ፡፡ ተማሪዎቻችን በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ወይም አካዴሚክ በሆነው ብቻ ሳይሆን በዚህ ተሞርደው የተስተካከለ ዜጋ እንዲሆኑ መሥራት  ይገባናል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ደግሞ ወደ መማር ማስተማሩ መለስ እንበልና በወሎ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ሒደቱ ምን ይመስላል?

ዶ/ር አባተ፡- ተማሪዎችን በወቅቱ ጠርተን በሁለት ካምፓሶች እያስተማርን ነው፡፡ ደሴ ዋናው ካምፓስና ኮምቦልቻ ሁለተኛው ካምፓስ አሉን፡፡ መማር ማስተማሩ በጥሩ ሁኔታ  እየተካሄደ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ተሟልቶ ነው ትምህርት የጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን መሥራት አንዱና ትልቁ ኃላፊነታቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ረገድ ምን ያከናወናቸው ሥራዎች አሉ?

ዶ/ር አባተ፡- አንድ ዩኒቨርሲቲ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው መማር ማስተማር ነው፡፡ ሁለተኛው ጥናትና ምርምር ነው፡፡ ሦስተኛው የማኅበረሰብ አገልግሎት ነው፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በእነዚህ ሦስት ዘውጎች እየሠራ ነው፡፡ አራተኛው የሰላም እሴት ግንባታ ነው፡፡ እነዚህን አራቱን ነው አጣምረን እየሄድን ያለነው፡፡ መማር ማስተማርን በተመለከተ ግቢያችን ውስጥ በተቻለ መጠን በርካታ ሥራዎችን እያከናወንን ነው፡፡ ከእኛ አልፈን ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብተን ጥራት ላይ ችግር እንዳይፈጠር ከደሴ፣ ከደቡብ ወሎ፣ ከከሚሴ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር የጋራ ውል አለን፡፡ ከሃያ ሴክተሮች ጋር የጋራ ውል አለን፡፡ በመርህ ነው የምንሄደው፡፡ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ከታች ጀምረን በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ላይ እንሠራለን፡፡ ባለፈው ዓመት ያከናወንነው ችግር ፈቺ ሥራ በተከታታይ ሁለት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ሊያስመርጠን ችሏል፡፡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መምህራንን እየመረጥን በአምስት ትምህርቶች ቅዳሜና እሑድ እናስተምራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ዓይነቶቹ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር አባተ፡- ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ባዮሎጂ፣ ሒሳብና እንግሊዝኛ ናቸው፡፡ ጥሩ ተሞክሮ የሆነን የዘጠነኛና የአሥረኛ ክፍሎችን መምህራን ከስድስት ያህል ትምህርት ቤቶች እንደ ሞዴል ወስደን የአቅም ግንባታ እየሠራን ነው፡፡ መምህራኑ እኛ መምህራን ዘንድ ሳምንቱን በሙሉ ይማራሉ፡፡ በአጠቃላይ ጥራትን የሚያስጠብቁ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ በግብርና ላይ በርከት ያሉ ቴክኖሎጂዎችን አምጥተናል፡፡ ምርጥ ዘሮችን አምጥተናል፡፡ ለኅብረተሰቡ እናከፋፍላለን፡፡ ምርታማ የሆኑ በርከት ያሉ የስንዴ፣ የገብስና የሽንብራ ምርጥ ዘሮችን በማከፋፈል ላይ ነን፡፡ ሴቶችን ያሳተፉ በርካታ ጥናቶችን ሠርተናል፡፡ ሌላው የሰላም እሴት ግንባታ ነው፡፡ የሰላም እሴት ግንባታ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ደቡብ ወሎ ላይ አብረን ነው የምንሠራው፡፡ የፀጥታ ኃይሉም፣ እኛም፣ የሃይማኖት አባቶችም አብረን እንሠራለን፡፡ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች ይቀርባሉ፡፡ የተለያዩ የአቅም ግንባታዎችን እንሠራለን፡፡ ኦሮሚኛ ቋንቋን በትርፍ ጊዜ እናስተምራለን፡፡ ብዝኃነትን በተግባር በማለት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 89 ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ዘንድሮ 300 ተመዝግበዋል፡፡ ዓረብኛ፣ ኦሮሚኛና ግዕዝ እያስተማርን ነው ያለነው፡፡ ለቋንቋዎች ማበልፀጊያ ጠንከር ያሉ ሥራዎችን እናከናውናለን፡፡ የሰላም እሴት ስትገነባ ባህሉንና ቋንቋውን ማወቅ አለብህና በዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡ አሁንም ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ጠርተን በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ከፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከክልሉ ፀጥታ ቢሮ ጋር በመሆን ጥሩ የሆነ ጽሑፍ ቀርቦ ትምህርት ተቀሳስመናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዘንድሮው በዩኒቨርሲቲያችሁ ምን ያህል ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች አሉ?

ዶ/ር አባተ፡- ቅድም እንደነገርኩህ 25 ሺሕ ተማሪዎች አሉን፡፡ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን ጨምሮ 2,500 ሠራተኞች አሉን፡፡ በመጀመርያ ዲግሪ ወደ 67 የሚሆኑ የትምህርት መስኮች አሉን፡፡ በሁለተኛ ዲግሪም በርካታ የትምህርት መስኮች አሉን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy