Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሥጋታችንን አስወግደን ተስፋችንን እናለምልም

0 375

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሥጋታችንን አስወግደን ተስፋችንን እናለምልም

ኢብሳ ነመራ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር በተያያዘ ወደግጭት ያደገ አለመግባበት ከተቀሰቀሰ ከረመ። ሁለቱ ክልሎች በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ወይም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ  የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በኩል አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል ድንበር ይጋራሉ። ሁለቱ ክልሎች የሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች በአሃዳዊው የመንግሥት ሥርዓት በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች ወይም ክፍለ አገሮች ተሸንሽነው ነበር። በወቅቱ ከኦሮሚያ ጋር በስተምሥራቅ የሚዋሰኑት የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢዎች ሐረርጌ በሚባለው ጠቅላይ ግዛት ወይም ክፍለ ሃገር ሥር የተጠቃለሉ ነበሩ። በስተምሥራቅ ደቡብ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢዎች ደግሞ ከፊሉ በባሌ ጠቅላይ ግዛት የተቀረው ደግሞ በሲዳማ ጠቅላይ ግዛት ሥር ነበር። በአሃዳዊው ሥርዓት የኢትዮጵያ ሶማሌም ኦሮሞም የሚባል በህግ እውቅና የተሰጠው ህዝብ አልነበረም።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባካሄዱት ትግል ማንነታቸው እውቅና አግኝቶ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ሲጀምሩ፣ ሁሉም ብሄሮች የህዝባቸው መኖሪያ የሆነውን መልከዓምድር በክልላዊ መንግሥት፣ በዞን፣ በልዩ ወረዳ ከለሉ፤ ራሳቸውን ለማስተዳደር በሚያመቻቸው ሁኔታ። ይህ ህገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው ክንውን ነው። በዚሁ መሠረት በዘውዳዊውና በወታደራዊው ደርግ ከፋፍለህ ግዛ ስልት ሁለትና ከዚያ በላይ ቦታ ተቆራርጠው የነበሩት፣ እንዲሁም ከሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአንድ አስተዳደር ሥር ተጨፍልቀው የነበሩት የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄሮችም የህዝባቸው መኖሪያ የሆነውን መልከዓምድር በክልላዊ መንግሥትነት አካለሉ።

ሁለቱ ክልሎች በጠቅላይ ግዛት ወይም ክፍለ ሃገር አንድ ላይ ተጨፍልቀው በነበረበት ዘመንም ቢሆን የየራሳቸው መልከዓምድር ነበራቸው። አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩት የሁለቱም ብሄረሰቦች ጎሣዎች ወሰናቸው የት ድረስ እንደሆነ ያውቁት ነበር። ይህም ሆኖ መልከዓምድራቸው በመሬት ላይ ሳይካለል ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ኖሯል። ይህም የወሰን ይገባኛል ውዝግብ ሊቀሰቀስ የሚችልበትን ሁኔታ ፈጥሯል። እናም ከ13 ዓመታት በፊት በ1997 ዓ.ም በሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች በወሰን ይገባኛል ጥያቄ መጠነኛ ግጭቶች ተቀስቅሰው ነበር። በዚህ ወቅት ለችግሩ እልባት ለመስጠት አወዛጋቢ በሆኑ ቀበሌዎች ህዝበ ውሣኔ ተካሄደ። ህዝቡ በዚህ ነጻ ህዝበ ውሣኔ የሚኖርበት መሬት ወደየትኛው ክልል እንደሆነ ወስኗል። ይሁን እንጂ ይህን ህዝበ ውሣኔ ተከትሎ የሁለቱ ክልሎች ወሰን መሬት ላይ ሳይካለል ቀረ። ወሰን የማካለሉ ሥራ ሳይከናወን የቆየበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ በሁለቱ ክልሎች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ ለሚፈልጉና ሌሎች ዓላማዎች ላላቸው ወገኖች መልካም አጋጣሚን አመቻችቷል።

ይህ የወሰን አለመካለል ከአሥር ዓመት በኋላ በተለይ በ2009 ዓ.ም ወሰኑ ይካለል በሚል ጥያቄ ሳይሆን በግጭት ተገለጸ። በሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች የሚኖሩ የሁለቱም ብሄሮች ጎሣዎች በአብዛኛው አርብቶ አደሮች ናቸው። ይህ የኑሮ ዘይቤ ካስከተለው ተዘዋዋሪነት ጋር በተያያዘ አብረው በኖሩባቸው ዘመናት በሙሉ አለመግባባትና ግጭት ሲያጋጥማቸው መኖሩ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህን ግጭት የሚፈቱበት የራሳቸው ባህላዊ ሥርዓት አላቸው። ወደጠቅላይ ግዛት ወይም ወደሃገር አስተዳደር ሚኒስቴር የሚደርስ ጉዳይ አልነበረም። ሁለቱ ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ከጀመሩም በኋላ ቢሆን በአርብቶ አደሮች መካከል ከሣርና ውኃ ሽሚያ ጋር በተያያዘ የወሰን ግጭት አጋጥሟል። ይህም ቢሆን የየክልሉ መንግሥታት ወይም ፌዴራል መንግሥት ጋር ሳይደርስ ነበር የሚፈታው። በ2009 ዓ.ም የተከሰተው ግጭት ግን ከዚያ ቀደም በነበረው ባህላዊ ሥርዓት ሊፈታ ያልቻለ ነበር።

የወሰን ግጭቱ በሁለቱ ብሄር ጎሣዎች መካከል ለዘመናት በቆየው ባህላዊ የእርቅ ሥርዓት ሊፈታ አለመቻሉ አንድ የሚያመለክተው ነገር አለ።  ይህም ግጭቱ የሁለቱ ህዝብ ግጭት አለመሆኑን፣ ግጭቱን የሚለኩሰው ሌላ በድንበር አካባቢ የሌለ ምናልባት የተለየ ፖለቲካዊ ፍላጎት ወይም ተገቢ ያልሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጠባቂ መሆኑን ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የሁለቱም ክልሎች እንዲሁም የፌዴራል መንግሥቱ በተደጋጋሚ መግለጫ ስለሰጡበት መልሼ ማንሳት አልፈልግም።

ያም ሆነ ይህ፣ በ2009 ዓ.ም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በሁለቱም በኩል የሠላማዊ ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ የቆየ ችግር ለመሆን በቅቷል። በተለይ 2010 ዓ.ም መግቢያ ላይ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ግጭት ለመሆን በቅቷል። 2009 መሰናበቻና 2010 መቀበያ ላይ በጷጉሜን ወር፣ በኦሮሚያ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አወዳይ ከተማ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጅ የሆኑ ንጹኃን ዜጎችን ህይወት ያጠፋ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እስከ ጅግጅጋ ከተማ ርቀው ይኖሩ የነበሩ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን የቀጠፈ ግጭት አጋጥሟል። የብሄራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፣ በግጭቱ ሣቢያ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች 629 ሺህ፣ ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ደግሞ 300 ሺህ  እንደሚሆኑ አስታውቋል። ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው። ይህ ለዜጎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት የሆነ ግጭት የወሰን ይገባኛል አለመግባባት በተፈጠረባቸው የድንበር አካባቢዎች የተቀሰቀሰ አልነበረም። ከድንበር ርቀው ባሉ አካባቢዎችም አጋጥሟል። ይህም ግጭቱ በቀጥታ የሁለቱ ክልሎች ህዝብ ግጭት እንዳልሆነ ያመለክታል።

ከዚህም በኋላ በሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች የፀጥታ ቀጠና ተከልሎ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትና በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቅ ተወስኗል። ይሁን እንጂ በ2010 እና ከዚያ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ቀንሷል ማለት ይቻል እንደሆን እንጂ ግጭቶች አልተቋረጡም። በተለያዩ ወቅቶች በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያና በአዋሣኝ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች ሰዎች የሚሞቱባቸው ግጭቶች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል። በምሥራቅ ኦሮሚያና አዋሣኝ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አካባቢ የነበረው ሁኔታ የተሻለ ሠላምና መረጋጋት የነበረው ቢሆንም አልፎ አልፎ የሰው ህይወት የሚጠፋበት ግጭት አጋጥሟል። ከዚህ በተጨማሪ መስከረም ላይ ጣሪያ ላይ ደርሶ በነበረው ግጭት በሁለቱም ክልሎች ተወላጆች ላይ ደርሶ የነበረው ጉዳት በአካባቢው የሠላምና መረጋጋት ድባብ እንዲጠፋና ውጥረት መሰል ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል።

ይህ ሁኔታ ሳይለወጥ ከሦስት ወራት በላይ ጊዜ አስቆጠረ። የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት እየሰሩ መሆኑ፣ ምናልባት ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሳቸው ባይካድም እስካሁን ይፋዊ ፖለቲካዊ ርምጃ አልተወሰደም። በህግ መጠየቅ ያለባቸው ተጠርጣሪዎችም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለው በይፋ ክስ አልተመሰረተባቸውም። በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረውን ወዳጅነት የሚያድስ ህዝባዊ የሠላም ኮንፈረንስ አልተካሄደም። በአጠቃላይ ሁለቱም ክልሎች፣ የፌዴራል መንግሥትም በግጭቱ ስለተፈናቀሉ ሰዎች በማውራትና እርዳታ በማሰባሰብ ሥራ በመጠመድ ነበር ጊዜው ያለፈው። አንዳንድ የህዝብና የግል መገናኛ ብዙሃንም ጉዳዩን የያዙበት አኳኋንም ግጭት በመቀስቀስ ባያሳማቸውም በሁለቱ ህዝቦች መካከል መተማመንን የሚያጎለብት ሥራ አልሰሩም ማለት ይቻላል።

በዚህ ሁኔታ ጉዳዩ ተጨባጭ የመፍትሄ ተስፋ ሳያሳይ እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ። በየወቅቱ ሲያግጥም የነበረውና ለአንድ፣ ለሁለት . . . ሰዎች ሞት ምክንያት እየሆነ እልባት ሳይበጅለት የቆየው ግጭት ባለፈው ሣምንት ማክሰኞ በኦሮሚያ ምሥራቅ ሐረረጌ ዞን ሜታ ወረዳና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰርከማ ወረዳ አዋሣኝ አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ ተቃውሞ ቀስቅሷል። አንድ ሰው በመሞቱ በስሜት ተነሳስተው በሜታ ወረዳ ጨለንቆ ከተማ ላይ ለተቃውሞ የወጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፌዴራል ፀጥታ አስከባሪ ኃይል ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል። በዚህም የ15 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።

የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩ በብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት እንዲጣራ ውሣኔ አሳልፎ ሳለ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ሁኔታውን የሚመረምር ኮሚቴ አዋቅሮ ሥራ ጀምሮ ባለበት ሁኔታ በምዕራብ ሐረርጌ ሌላ ግጭት ተቀሰቀሰ። በምዕራብ ሐረርጌ ዳሩ ለቡ እና ሃዊ ጉዲና በተባሉ ወረዳዎች ከታህሳስ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት በኦሮሚያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ላይ አስከፊ ጥቃት ተፈፀመ።

ይህን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሣና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ መግለጫ አውጥተዋል። አቶ ለማ መገርሣ የተፈፀመው ድርጊት እጅግ ዘግናኝ መሆኑን ገልፀዋል። በሁኔታው የተሰማቸውን  ሐዘንም በመግለጽ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ህዝቡን እንደማይወክሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለው ለፍርድ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ “በምዕራብ ሐረርጌ በዳሩ ለቡ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ ለደህንነታቸው ሲባል በአካባቢው በአቅራቢያ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ላይ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። በራሴና በፌዴራል መንግሥት ስም በንጹኃን ዜጎች ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ለመላው የአገራችን ህዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ። መንግሥት ድርጊቱን እያወገዘ ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ያቋቋመ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፤ የማጣራቱ ሂደት እንደተጠናቀቀም አስፈላጊውን ርምጃ የሚወሰድ ሲሆን የማጣራት ሂደቱን ውጤት ለሕዝቡ በዝርዝር እንደምንገልጽ ከወዲሁ ለማሳወቅ እፈልጋለሁ። በተመሳሳይም በጨለንቆና ሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሣቢያ በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሞትና መቁሰል አደጋ አጋጥሟል። በድጋሚ በመንግሥትና በራሴ ስም በዜጎቻችን ህልፈተ ሕይወት ምክንያት የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ለመላ የአገራችን ህዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ። የፀጥታ ኃይሎቻችን መንግሥት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሠላም እንዲያረጋግጡ ተልዕኮ ሰጥቷቸው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፤ የጨለንቆን ግጭት ጨምሮ ተልዕኳቸውን እየፈፀሙ ባሉበት ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶች ካሉ አሠራሩን ተከትሎ መንግሥት የሚያጣራ ሲሆን የማጣራቱ ሂደት እንደተጠናቀቀም ውጤቱን ለሕዝቡ በዝርዝር ይፋ የምናደርግ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ” ብለዋል።

በአጠቃላይ፤ በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ክቡር የሰው ህይወት መጥፋቱ፤ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውና የዜጎች ሐብትና ንብረት መውደሙ ብቻ ሳይሆን፤ ችግሩ በፍጥነት ካልተወገደ እንደ አገር አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሊጥለን እንደሚችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ሥጋት ገልፀዋል።

ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥጋት ሁሉም ሠላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይጋራዋል። ኢትዮጵያ አሁን ወደብልጽግና ማማ የሚያደርሰውን መሰላል ጨብጣ የመወጣጣቱን ጉዞ ጀምራለች። በሌላ በኩል በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱትና ከአጋጣሚነት ወደመደበኛነት እየተሸጋገሩና እየሰፉ የመጡ ግጭቶች ከጨበጥነው የብልጽግና መወጣጫ መሰላል ላይ እንዳይፈጠፍጡን ሥጋት ውስጥ ገብተናል። አሁን ከተስፋና ተስፋችንን ሊያጨልም ግብግብ ከገጠመን ሥጋት ጋር ተናንቀን ያለንበት ወቅት ነው። መንግሥት ሥጋት ላይ የጣለን አደጋ አይሎ ከመፈጥፈጣችን በፊት ሥጋታችንን አስወግዶ ተስፋችንን የሚያለመልም ፈጣን ርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅበታል። ህዝቡም አገሪቱን ለማተራመስ ግጭት ከሚቀሰቅሱ ቡድኖች ሴራ ራሱን ተከላክሎ ሠላሙን ሊያረጋግጥ እንዲሁም መንግሥት ሠላም ለማስከበር የሚወስዳቸውን ርምጃዎች ሊደግፍና ተግባራዊነታቸው ላይ ሊሳተፍ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy