Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሴቶችና ፌዴራሊዝም

0 463

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሴቶችና ፌዴራሊዝም

                                                   ታዬ ከበደ

የአገራችን ሴቶች በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ትኩረት የተሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ሴቶች የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 35 ላይ የተሰጣቸውን መብቶችና ትኩረት  ተጠቅመው ለራሳቸውና ለአገራቸው በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። የእነርሱን የልማት ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም መንግስት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችንና ፓኬጆችን በመቅረጽ ከፌዴራላዊ ፅርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በህገ መንግስቱ “የሴቶች መብት” አንቀፅ 35 ስር በተዘረዘሩ በዘጠኝ ንዑሳን አንቀፆች አማካኝነት እነዚህ የሴቶች ልዩ ትኩረትና ተጠቃሚነት ተገልፀዋል። በተለይም በንዑስ አንቀፅ ሶስት ላይ፤ “ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው።

በዚህ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግስትና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው” በሚል ሴቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበሩባቸው የተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በበታችነትነና በተጨቋኝነት መንፈስ ያሳልፉ የነበረው ሁኔታ በህገ መንግስቱ ፍፁም መሻሩና የቀረ መሆኑ ተመልክቷል።

ይህ ብቻ አይደለም። በዚሁ አንቀዕ ንዑስ አንቀፅ ስድስትና ሰባት ላይ፤ ሴቶች በብሔራዊ ልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በፕሮጀክቶች ዕቅድና አፈፃፀም፣ በተለይም የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ፕሮጀክቶች ሃሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ እንዲሁም ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት ያላቸው መሆኑን፤ በተለይም መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው ብሎም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።

ከሴቶች መብቶች ጋር በተያያዘ የተገለፁት ሌሎች አንቀፆችም ቢሆኑ፤ ሴቶች በህብረተሰቡ የህይወት መዘውር ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው በህግ የተደረገላቸውን ልዮ ትኩረትና ጥበቃ የሚተነትኑ ናቸው።

በዚህ መሰረትም ከህገ መንግስቱ አኳያ ሴቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ እየሆኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የኢፌዴሪ መንግስት ህገ መንግስቱን ተከትሎ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፖሊሲዎች እና እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል። ፖሊሲዎቹና እርምጃዎቹ ተግባራዊ የሆኑት በሽግግር መንግስቱ ቻርተር እንዲሁም ኋላ ላይም ህገ መንግሰቱ በስራ በዋለባቸው 23 ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ነው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከተሳትፎ አኳያ የሴቶች አጀንዳዎች በሁሉም ዘርፎች እንዲካተቱና ተጠያቂነትን በሚያጎሉ መንገድ ክትትል የማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ ገቢራዊ ሆኗል። በመሆኑም ሴቶች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአደረጃጀታቸው የአባላት ብዛትና በአመራር ሰጪነት ብቃት እንዲሁም በፖለቲካው መስክ የሚያደርጉት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጠናከሩ የሚያደርጉ ስራዎች ዕውን ሆነዋል።

ከምጣኔ ሃብት ተሳትፎና ተጠቃሚነት አኳያም፤ በመንግስት ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ሴቶች በተለያዩ ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን ችለዋል። በዚህም አበረታች ሊባል የሚችል ውጤት ተመዝግቧል። በተለይም ሴቶች መሬት፣ ብድርና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ሃብቶችን የመጠቀምና የመቆጣጠር መብት እንዲጐናፀፉ ተደርጓል።

በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የሴቶችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝተዋል።

በቤት ውስጥ ያለባቸውን የስራ ጫና ለመቀነስም ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶችን የአማራጭ ኢነርጂና የተለያዩ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህም የሴቶችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብና ያለ ብዙ ድካምና እንግልት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በስልጠና፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸትና የቁጠባ ባህላቸውን የሚያበረታታ እንቅስቃሴም ተከናውኗል።

በህገ መንግስቱ ጥበቃ ያገኙት እንደ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር መብታቸውም የመሬት ተጠቃሚነት የባለቤትነት መብታቸውን አረጋግጧል። ይህም የባለቤትነት ስሜቱን ይበልጥ በማረጋገጥ በተዘረጋው የኤክስቴንሽን አገልግሎት በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የሴቶችን እኩል የመሬት ተጠቃሚነትን መብት ለማረጋገጥ የክልል መንግስታት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በአባወራዎችና በእማወራዎች ስም በጥምር የመመዝገብ እርምጃ በመውሰዳቸውም፤ ሁለት ሚሊዮን እማወራና ዘጠኝ ነጥብ 11 ሚሊዮን እማወራና አባወራ በጥምረት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል።

በጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ዘርፍ ውስጥም ቢሆን የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ነው። በዚህም በስልጠና፣ በመስሪያና በመሸጫ ቦታ እንዲሁም በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። በግንባታ፣ በንግድና በከተማ ግብርና በመደራጀትም ተጠቃሚነታቸውን ከፍ አድርገዋል። በከተማ በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶች የቤት ባለቤት የመሆን፣ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር ህገ መንግስታዊ መብታቸው ዕውንና ተፈፃሚ ሆኗል።

በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም የሚሳተፉ ሴት አንቀሳቃሾች ብድር እንዲያገኙና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ሲሆን፤ ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሸጋገሩበት አቅጣጫ ተቀምጦም ተግባራዊ እንዲሆን በመደረጉ በመስኩ ያላቸው ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሊሆን ችሏል።

ላለፉት 23 ዓመታት ሴቶች በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የመሰረተ-ልማት አውታሮችም ተጠቃሚነታቸው እየጎላ መጥቷል። ለአብነት ያህል ውሃን በቀላሉ ማግኘት መቻሉ የሴቶችን ህይወት ይበልጥ ቀላል እንዲሆን አድርጎታል። ይህም ሴቶች ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚያባክነኑትን ጊዜና ጉልበት በመቀነስ በምርት ተግባር ላይ እንዲያውሉ አድርጓቸዋል።  

በመንገድ መሰረተ-ልማትም በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ የተዘረጋው የሀገራችን የገጠር ቀበሌዎች ክረምት ከበጋ በሚያስኬዱ መንገዶች እንዲገናኙ በመደረጉ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት በማሳየቱ፤ በርካታ የገጠር ከተሞችንና ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ከመቻለሉም በላይ፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት የጎላ እንዲሆን አድርጎታል። የአገልግሎቱ መስፋፋት ሴቶችን ወጪ፣ ጊዜና ማገዶ ቆጣቢ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።

በማህበራዊ መስክም ሴቶች ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መጥቷል። በተለይ ጎታች የህብረተሰቡን ባህልና አመለካከት የመቀየር፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን የሚገድቡ እንቅፋቶችን የማቃለልና የመደገፍ ተግባራት ስራዎች ተከናውነዋል። ባለፉት ስርዓቶች የነበረው የስርዓተ ፆታ ልዩነትም እየጠበበ መጥቷል።

ሴቶች በገንዘብ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡም፤ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ ስልጠና በመስጠትና ተጨማሪ የትምህርት ጊዜ በማመቻቸት ትምህርታቸውን በውጤታማነት እንዲፈፅሙ እየተደረገ ነው።  

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይ ቢኖር፣ ሴቶች በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ያገኙት ከፍተኛ ተጠቃሚነነት ነው። በጤና የልማት ሰራዊት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች በተከናወኑ አመርቂ ስራዎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋኑ ከፍ በማለቱ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆን ችለዋል። ታዲያ እነዚህ በህገ መንግስቱ ላይ ተቀምጠው ላለፉት 23 ዓመታትና ከዚያ በላይ በስራ ላይ ውለው ውጤት የተገኘባቸው ተግባራት መሰረታቸው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy