Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስለሀገራችን ልማትና ሰላም የምሁራን ሚና

0 567

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስለሀገራችን ልማትና ሰላም የምሁራን ሚና

 

ዮናስ

 

ከሰሞኑ “የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ቅኝት ኮንፈረንስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ኮንፈረንስ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተካሂዶ ነበር።  ከሁለቱ ክልሎች የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ምሁራን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙ ምሁራን፣ ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች (ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለን ጨምሮ) የሁለቱም ክልሎች የቢሮ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን፣ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተማሪ ተወካዮችና የደብረ ብርሃን ከተማ የማኅበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት ይህ መድረክ ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ለሚገኙ ግጭቶች መላ ለመዘየድ ያለመ እንደሆነ ከቀረቡት የጥናት ወረቀቶች መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የተጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረውና ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ተካሂዶ በነበረው የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፈረንስ ላይ የተላለፉ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሆነ በአዘጋጆቹ በኩል በእለቱ የተገለጸ ሲሆን፤ የሁለቱ ክልሎች ምሁራን ኮንፈረንስ በሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር ለአገር ግንባታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑም ተገልጿል።ስለሆነም በሃገሪቱ፤ ይልቁንም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚስተዋሉና ከጊዜ ወደጊዜ ከልክ እያለፉ የመጡ ብሄር ተኮር ግጭቶችን ከማስወገድ አንጻር ፋይዳቸው የጎሉትን ማውሳት ካለንበት አጣብቂኝ አኳያ ተገቢ ይሆናል።

 

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ታምራት  ኃይሌ ያቀረቡት መነሻ ጽሑፍ ስለ አጀንዳችን ወሳኝ ነጥቦችን ይዟል። ካሳለፍናቸው ጥቂት አሥርት ዓመታት ጀምሮ ስለሕዝቦች እኩልነትና ነፃነት የተነገረውንና የተሠራውን ያህል ስለሕዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት መወያየትና ማሰብ አለመቻላችን ለከፈልናቸው ዋጋዎች የጎላውን ድርሻ ይይዛል።ስለሕዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት በተመለከተ ሁለት ማዕቀፎች የተረሱ መሆናቸውም በጽሁፋቸው ላይ የተወሳ ሲሆን፤ እነሱም ኩታ ገጠም መልክዓ ምድራዊና ተቋማዊ የግንኙነት ማዕቀፎች መሆናቸው ተመልክቷል።

 

የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች በኩታ ገጠም የሚኖሩ መሆናቸውን ያመለከተው የዶ/ር  ታምራት ጥናት፤  ለብዙ መቶ ዓመታት ያዳበሩት ታሪካዊ ግንኙነት በርካታ መልክ  እንደነበረው አውስቶ፤ ሁለቱ ሕዝቦች በጉርብትናና ባልተቋረጠ ግንኙነት መወራረሳቸውን ያረጋግጣል።አማርኛ ቋንቋ ከአፋን ኦሮሚፋ፣ እንዲሁም አፋን ኦሮሚፋ ከአማርኛ ቋንቋ ብዙ ተወራርሰዋል፡፡ በጥሞና ላስተዋለ ታዛቢ መበደርና መዋስ የሚያመለክተው አምኖ መቀበልን፣ መግባባትንና ማክበርን ነው፡፡ በኢኮኖሚው ዘርፍም በኩታ ገጠም መልክዓ ምድር በመኖራቸው የምርትና የቴክኖሎጂ መመሳሰል ከፍተኛ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይላል።

 

ስለሆነም በየክፍለ ዘመናቱ በተፈጠረውን የኃይል ግንኙነት ታሪክ፣ ከሁለቱ ሕዝቦች የግንኙነት ታሪክ ጋር ማምታታት ሳይንሳዊም ጤናማም አይደለም፡፡ ይህም የኦሮሞንና የአማራን ሕዝቦች ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ በሌሎች ሕዝቦች ሊሂቃን ጭምር የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ግንኙነቶችን ጭምር የሚመለከት ነው።

 

ያም ሆኖ ግን እየተስፋፉ በመጡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የንግድና ሌሎች የማኅበራዊ ምጣኔ ተቋማት ውስጥ የሕዝቦች ግንኙነት አዲስ ጠባይና ግብር በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ወንድማማችነት ባለመኖሩ ነፃና እኩል መሆኑ የታወቀለት ግለሰብ ሌላ መሰሉን ተጠራጥሯል፣ ሸሽቷል፡፡ ውድ የሆነ ጊዜውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ጠልፎ ለመጣል አውሏል፡፡ወንድማማችነት ባለመኖሩ የተነሳም በዓለም አቀፍ የካፒታሊዝም ውድድር፣ ነፃና እኩል ነን ባይ ሕዝቦች የሰጧቸውን ብቻ ተቀባይ ከመሆን ያለፈ ዕጣ ፋንታ እንዳይኖራቸውም አድርጓል። በማለት ወቅታዊውን የሕዝቦች ገጽታ ይተቻል።

 

ለልማትና ዕድገት ምቹ የሆኑ ጉዳዮች ማኅበራዊ እሴቶች ስለመሆናቸው አጽንኦት የሚሰጠው እና ‹‹የሕዝቦች አንድነትና የምሁራን ሚና›› በሚል በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ መምህር አቶ ሥዩም ተሾመ የቀረበው ጽሁፍ፤ማኅበራዊ እሴቶቹ እውቀትና ነፃነት መሆናቸውን ይጠቅሳል። እውቀትና ነፃነት የሌለው ማኅበረሰብ ከድህነትና ኋላቀርነት ጋር ተላምዶ ይኖራል።እውቀትና ነፃነት የተለየ ነገር ለመሥራት፣ የተሻለ ነገር ለመፍጠር፣ አዲስ ነገር ለመሥራት፣ አገር ለመቀየር የሚያስችሉን ቁልፍ ማኅበራዊ እሴቶች ናቸው የሚለን ይህ ጥናት፤ ድህነት በሥልጣኔ መቃብር ላይ የሚበቅል አረም ነው በማለትም ከተዘፈቅንበት ማጥ መውጫውም ይኸው እውቀትና ነፃነት መሆኑን ይጠቁማል።

 

ልዩነት ያለና የሚኖር ተፈጥሮአዊ ጉዳይ እንደሆነ የሚያብራራው የአቶ ስዩም ጥናት፤ልዩነት ሲጠፋ ነፃነት እንደሚገደብ ጠቅሶ፤ ሰው መፈለግ የሚገባው እና መፈልግም ያለበት በልዩነቱ መናቆርን ሳይሆን በአገርና በቋንቋ ሳይከፋፈል በሰውነቱ እኩል መታየት ብቻ ነው ሲል ያስጠነቅቃል፡፡ አያይዞም፤-

እኔም እንዳንተ እኩል መብትና ተጠቃሚነት ይገባኛል ብሎ የሚያስብ ትውልድ ሲገነባ ደግሞ የመንግሥት ድርሻና ኃላፊነት ይህን እኩልነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህን እኩልነት ሊያረጋግጥ የሚችል ፖለቲካዊ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ይህን ሲመቸን የምንፈጥረው ነገር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ከማክበር ነው የሚመነጨው፤ ሲልም መንግስትን ያሄሳል።

 

የምሁራን ድርሻን በተመለከተም፣ “የመንግሥትን ሥራ መተቸት፣ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች መለየት፣ የግንዛቤ ለውጥ ማምጣት፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ በዚህም የለውጥ ሐሳቦችን ማስረፅ፣ ለዕድገትና ለብልፅግና ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ መዳበር መሥራት ግዴታ አለባቸው፤” የሚለው ይህ ጥናት ፤ ምሁራን መንግሥትን መፍራት የለባቸውም፡፡ ምሁራን መንግሥትን በሚፈሩበት አገር መንግሥት ደግሞ ፍፁም አምባገነን ይሆናል፡፡ መንግሥት አስፈሪ በሆነበት አገር ምሁራን የመንግሥት ቃል አቀባይ እንደሚሆኑ ይጠቁማልና ስለከፈልናቸው ዋጋዎች ምሁራኑም ድርሻ ያላቸው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ነፃነት ሲባል በአገሪቱ ሁለንተናዊ መስተጋብሮች እኩል የመሳተፍና የመጠቀም፣ እንዲሁም እኩል ግዴታን የመጣል መርህ እንደሆነ አስረጅ ጠቅሶ የሚያወሳው የአቶ ስዩም ጥናት፤ ይህን ባለገናዘበ አግባብ የሄድንበት መንገድ በአገሪቱ እየተከሰተ በመጣው የብሔርተኝነት ስሜትና እየተስተዋሉ በሚገኙ ዘግናኝ ድርጊቶች መገለጡን ያረጋግጣል፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው ዋጋ እያስከፈሉን ለሚገኙት ግጭቶች ዋነኛ ምክንያቱ የብሄር ልዩነት ሳይሆን የዜጎች ነፃነት ማጣትና መታፈን መሆኑን ሲሆን፤ምንጩ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን ምሁራኑም መሆናቸውን ነው። ይህን ለማስተካከል ደግሞ በተመሳሳይ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የምሁራን ድርሻም ያስፈልጋል ማለት ነው።

 

የብሔርተኝነት ስሜት እያየለና አገራዊ አንድነት እየተሸረሸረ በቡድን የመደራጀት አባዜ እየተስተዋለ መምጣቱ ላይ ልዩነት ከሌለን፤ችግሩን ለማስተካከል ምሁራንና አክቲቪስቶች ሰፊ ሥራ ሊያከናውኑ ይገባል የሚለው የጥናቱ ምክረ ሃሳብም ላይ ልንስማማ ግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ምሁራንና አክቲቪስቶች መደማመጥ አለባቸው፡፡ ሕዝብ የግል ታሪኩን እየመዘገበ፣ አገራዊ ታሪክን እየሸረሸረና እያዛባ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ግንዛቤ መፍጠር ከነዚሁ አካላት ይጠበቃል። በማለት ያሳስባል።

 

ጥያቄው ብዝኃነትንና አንድነትን አንዱ አንዱን ሳይጨፈልቅ እንዴት እንሥራ? የሚል ነው።ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ድርጊቶች አፍጥጠው እየመጡ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችን መቻቻል በሚለው መርህ ላይ ልዩነቶች ሰፍተዋል የሚለው የምርምር ውጤት ፤አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎለብቱ እሴቶች ላይ መስራት የምሁራን ሃገራዊ ሃላፊነትና ግዴታ አጽንኦት ይሰጣል።ዩኒቨርሲቲዎች የዩኒቨርሳል እውቀት ማዕከል ቢሆኑም እየሠሩ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር የተቋማቱ አሠራርና አመለካከት ለዚህ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ በቋንቋ መግባባት አልተቻለም፡፡ ሀብትን ለመቀራመት ሩጫ በዝቷል፡፡ ተቋማት ውስጥ የወንድማማችነት መንፈስ ባለመፍጠር ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ምሁራኑ ተቋማትን መፈተሽ ካልቻሉ መጪው ጊዜ አስፈሪ መሆኑንም ጥናቱ በስጋት መልክ አስቀምጧል።

 

ስለሆነም በሕዝቦች መካከል ያለውን መስተጋብር በማዛባትና በማምታታት የተፈጠረውን ክፍተት ምሁራን በመሙላት የድርሻቸውን ሊውጡ ይገባል። ጊዜው ከማይፈቅደው መርህና አሠራር በመውጣት አንድነትንና ተባብሮ መሥራትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮች በምሁራን በኩል በትክክለኛ መንገድ ተጠንተውና ተለይተው መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy