Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህዝብ ባለቤትነት ሰላማችንን ማረጋገጥ ይቻላል!

0 296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በህዝብ ባለቤትነት ሰላማችንን ማረጋገጥ ይቻላል!

 

ዮናስ

 

ማንኛውም ዜጋ ሀሳቡን በነፃነት የመጻፍና የመናገር መብቱ ከመከበር አልፎ ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል።ይህ ዋስትና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹም ሳይሸራረፉ መከበር ያለባቸው መሆኑንም ይጨምራል፡፡እነዚህ መብቶች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው በወጡ ህጎችም ጥበቃና ከለላ አግኝተዋል፡፡ በጥቅሉ ማንኛውም ዜጋ በገዛ አገሩ ባይተዋርነት ሳይሰማው በእኩልነት የመኖር መብቱ በተግባር ተረጋግጧል፡፡ በዚህም አገሪቱን ለችግር የዳረጉ ብሶቶች ረግበው መነጋገር የሚቻልበት እድል ተፈጥሯል፡፡

 

ያም ሆኖ ግን፤ አገርን ወደ ብጥብጥ ለመግፋት የሚደረጉ  ጥረቶች  አሁንም አልፎ አልፎ ይስተዋላሉ፡፡ መነሻቸውም መድረሻቸውም የሕዝብ አጀንዳ ያልሆኑ ጉዳዮችን በማራገብ  አገሪቱን በማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት እየተደረገ ያለው ሩጫ ፍጥነቱን ጨምሯል፡፡ ለመንግሥት ሥልጣን ከሚደረገው ሽኩቻ ጀምሮ የመንግስትን ስልጣን ተጠቅመው ህገ ወጥ ሃብት ያካበቱ ሃይሎች ብሔርተኝነትን በማራገብ፣ የሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመናድ ቀን ከሌት እየተራወጡ ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ በድብቅ የሚካሄደው መጠላለፍና ንቁሪያ ራሱን የቻለ የቀውስ መንገድ መሆኑን መንግስትና እራሱ መሪ ድርጅቱም ይፋ አድርገዋል። በሌላው ጎራ ደግሞ አገርን ለትርምስ በሚዳርግ መንገድ ስልጣን ለመጨበጥ የሚሹ ሃይሎች ሴራ እየጎነጎኑ ነው፡፡ በዚህም የሕዝብ ፍላጎት ወደ ጎን እየተገፋ ወደ ብጥብጥ በሚያመራ እንካ ሰላንቲያ አየሩ ተሞልቷል ፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል ከፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ተገፍቶ የወጣ ሲመስል፣ የጥፋት አታሞ የሚደልቁ ኃላፊነት የጎደላቸው ኃይሎችም ዘራፍ እያሉ ነው፡፡ ይህ አጥንትን ዘልቆ የሚሰማ ሥጋት በፍጥነት እንዲገታ ካልተደረገ፣ ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ቀውስ መፈጠሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡

 

ኢትዮጵያውያን በመረጡት ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራት፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብታቸው በሕግ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ፤ ይህንን መብት በመጣስ በተለያዩ አካባቢዎች በበርካታ ዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ በደል ተፈጽሟል፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው “መጤ” እየተባሉ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ሲፈናቀሉና ሲገደሉ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ለዘመናት አብሮ በሰላም ከኖረ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ በርካቶች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከኖሩበት ቀዬ ተሰድደዋል፡፡ የዜጎች በሰላም የመኖር መብት አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ታዲያ ይህ አደጋ አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡

 

እንጀራ ፍለጋ የተሰማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ይኖራሉ፡፡ የእነዚህን ወገኖች ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ደግሞ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ካቃታቸው ሕግ አይከበርም፡፡ ሕግ ካልተከበረ ደግሞ ዜጎች ያፈሩትን ሀብት የሚፈልግ ወይም በጠባብ ብሔርተኝነት የተለከፈ ኃይል ሕገወጥ ድርጊት ይፈጽማል፡፡ ብሔርን መነሻ ያደረጉ ጥቃቶች የሚፈጸሙት ከኋላ የሚቆሰቁሱ ኃይሎች ስላሉ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች አንድም ሥርዓቱን በዚህ መንገድ ለመጣል የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሆነው ለፖለቲካዊና ለኢኮኖሚያዊ የበላይነት ትንቅንቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ የሕግ የበላይነት እንዲጠፋ ተደርጎ ገለልተኛ ሆነው ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው የፀጥታ ኃይሎች ጭምር አውቀውም ይሁን ሳያውቁት የግጭቱ አሟሟቂ  እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

 

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገው ሰላምና ዴሞክራሲ ነው፡፡ ይህ በማስተዋል የሚታወቀው ጀግና ሕዝብ በታሪኩ የሚያውቀው ጦርነትም ሆነ ግጭት ለድህነትና ለኋላቀርነት እንደዳረገው ከማንም በላይ ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ ታሪኩ በግጭቶችና በጦርነቶች የተሞላ መሆኑን ስለሚገነዘብ፣ ለሰላምና መረጋጋት ትልቅ ግምት አለው፡፡ በእርስ በርስ ግንኙነቱም ችግሮችን የሚፈታባቸው በርካታ አኩሪ ሥርዓቶች አሉት፡፡ ይህንን የመሰለ ሰላማዊና አስተዋይ ሕዝብ በሚኖርባት አገር ውስጥ፣ ከራሳቸውና ከቡድናቸው ጥቅም በላይ የማይታያቸው ራስ ወዳዶች ግን በጭፍንነት ብሔርተኝነትን እያቀነቀኑ የጥፋት መልዕክቶችን እያሰራጩ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች፣ እንዲሁም ሌላ አጀንዳ የተሸከሙም ጭምር ማመን የሚገባቸው የአገሪቱ ባለቤት ሕዝቡና ሕዝቡ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ የአገሪቱ የሥልጣን የመጨረሻው ሉዓላዊ ባለቤትም ሕዝብ እንደሆነ ሳያንገራግሩ መቀበል አለባቸው፡፡

 

የተለየ አጀንዳ አለን የሚሉ ወገኖች ካሉ ደግሞ መጀመርያ የሕዝብን ፍላጎት፣ ቀጥሎ ደግሞ ዘመኑ የደረሰበትን የዕድገትና የሥልጣኔ ደረጃ ቢያጤኑ መልካም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚደረገው ሙከራ ትርፍ አይገኝበትም፡፡ ሃይማኖትን፣ ብሔርንና የመሳሰሉትን ልዩነቶች በማራገብ ኅብረ ብሔራዊውን አንድነት ለመናድ መሞከር ከጠላት ተላላኪነት ተለይቶ አይታይም፡፡ ኢትዮጵያ የአማራው፣ የትግሬው፣ የኦሮሞው፣ የደቡብ ሕዝቦች፣ የአፋሩ፣ የሶማሌው፣ የጋምቤላው፣ የቤኒሻንጉሉ፣ የሐረሪው፣ ወዘተ. አንጡራ ሀብት ናት፡፡ የመላው ኢትዮጵያውያን እናት ናት፡፡ አስተዋዩና ኩሩው ሕዝብ ደግሞ በክፉም በደጉም ጊዜ ተደጋግፎና ተጎዳኝቶ የኖረው በዚህ ተምሳሌታዊ እሳቤ ነው፡፡ ይህንን ጥልቅና ወሰን የሌለው መስተጋብር በመሸርሸር አገርን መቀመቅ ለመክተት መሞከር ሰይጣናዊ ድርጊት ነው፡፡ የብሔር ስም እየጠሩ በመሳደብና በማንቋሸሽ ግጭት ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የጠላት ሴራ ውጤት ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ከንቱ ፕሮፓጋንዳ ለወጣቱ በመጋት በየቦታው ግጭት ለመቀስቀሻነት መጠቀም መወገዝ አለበት፡፡ በግለሰቦች መካከል የተነሳን ጠብ ወደ ብሔር እየገፉ አገርን ለማተራመስ የሚደረገው እንቅስቃሴ መቆም አለበት፡፡  

 

እርስ በርሱ ተከባብሮና ተፋቅሮ የሚኖር ጨዋ ሕዝብ ባቆያት አገር ውስጥ የብሔር ግጭት በመቀስቀስ አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ለመክተት የሚዳክሩ እኩዮች ተፈልፍለዋል፡፡ እነዚህን በሕግ ማለት ይገባል፡፡ ከሕዝብና ከአገር በላይ ማንም የለምና ከናዳው ለማምለጥ ፈጣን እርምጃ ያስፈልጋል፡፡

 

በተቀውሞ ጎራም ያለው ሃይል ያለው ብቸኛ አማራጭ ጊዜ ያለበፈትን የትግል ሥልት አስወግዶ ለሕጋዊ፣ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ጉዞ ራሱን ብቁና ንቁ ማድረግ ብቻ እንደሆነም ሊገነዘብ ይገባል። እምቢኝ ካለ ደግሞ ማስገንዘብ እና አንቅሮ መትፋት የሰላም ወዳዱ ህብረተሰብ ድርሻ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በሕጋዊ መንገድ ብቻ በመሆኑ ራስን አሳምኖ ለተግባራዊነቱ መበርታት እንጂ አመጽን እንደአማራጩ ማድረግ ለማንም አይበጅም፡፡

 

ሰላማዊውና ዴሞክራሲያዊው ጎዳና በስፋት እንዲከፈት ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በቅንነት መሥራት አለባቸው፡፡ በጉልበት የሚሆን እንደሌለ ሁሉ፣ በአሻጥርም የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ይህችን የተከበረች፤ ጥንታዊና ታሪካዊ አገር ለማጥፋት የሚፈልጉ ወገኖች ወደ ቀልባቸው ይመለሱ ዘንዳ ሰላም ወዳዱ ህዝብ ሳይታክት ሊሰራ ይገባል፡፡ የግልና የቡድን ጥቅም አገርን አይወክልም፡፡   

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰጡት ምላሽ የሚጠቁመው ነገር አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው ችግር በገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል ሳይሆን፣ በአመራሩ የተፈጠረ መሆኑ የመጀመሪያው ነገር ነው፡፡ እርሳቸው በፓርቲ አመራሮች ዘንድ ሁሉንም ሕዝብ እንደ ራስ ሕዝብ ያለማሰብ አቋም መኖሩን፣ ይህም ችግር የሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና የአጋር ድርጅቶች መሆኑን በግልጽ አስረድተዋል፡፡ የፀጥታ አካላትም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት ማስከበር ሲገባቸው፣ በደምና በጎሳ የመለየት  የማየት አዝማሚያ እንደስተዋለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በግጭት ውስጥ የተሳተፉም መኖራቸውን  ነው ያወሱት፤ ይህ በመሠረቱ የሕግ የበላይነትን የሚፃረርና አብሮ መኖርን ወደችግር ውስጥ የሚከት የአገር ሕመም ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ፍላጎት የሚቃረንና የዘመናት መስተጋብሩን የሚደረምስ ሕገወጥ ድርጊት ነው፡፡

 

ስለሆነም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ትናንሽና ጊዜያዊ ቀውሶች አገርን የማፍረስ አቅም እንዳላቸው ተደርገው በጽንፈኛ ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚነዙትን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች በአስተማማኝ መልኩ ከመመከት ጀምሮ፤ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተሰገሰጉ ጥገኞችን እና ሌሎች የትርምስ አጀንዳ የሚፈበርኩ ሃይሎችን ግንባር ገጥሞ መታገል ከህዝብ የሚጠበቅ እና ወቅቱ የሚጠይቀው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህንን በተገነዘበና ባለቤት በሆነ ሕዝብም የአገርን ሰላም ማረጋገጥ ይቻላል!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy