Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት

0 551

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት

                                                             ዮናስ

ኢትዮጵያን ለዘመናት የመሩት ገዥዎች በተከተሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ የአገዛዝ ስርዓት ዜጎችም ሆነ ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ተነፍገው በስቃይና እንግልት ይኖሩ የነበረ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በአገራችን ዴሞክራሲ በትግል እውን ከሆነ በኋላ የዜጎችና የማህበረሰቦች መብቶች ሳይነጣጠሉ ተከብረዋል፡፡ ከግለሰብ እስከ ቡድን መብት ድረስ ያሉ መብቶች እውቅና ተሰጥቷቸው የህግ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በህገ መንግስታችን ሃሳብን የመግለፅ፣ የመቃወምም ሆነ የመደገፍ፣ የመደራጀት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ በህይወት የመኖር፣ ከአካላዊ ጉዳት የመጠበቅ ወዘተ … ግለሰባዊ መብቶች ተከብረዋል፡፡ በቡድን መልክ የሚገለፁ ማህበረሰቦችም የተሟላ እኩልነት ተጎናፅፈዋል፡፡

ብሄር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ሴቶች፣ ሠራተኞች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና የመሳሰሉት ማህበረሰቦች  የቡድን መብቶቻቸውን የተጎናጸፉ መሆኑም እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣይነት ህልውናዋ ተረጋግጦ ልትቀጥል የምትችለው ዜጎቿንና ህዝቦቿን አክብራ ስትይዝ ብቻ እንደሆነ በማመን ተግባራዊ የተደረገው ዴሞክራሲ አገሪቱን ለፅኑ ህዝባዊ አንድነት አብቅቷታል፡፡ በሃይማኖትም ሆነ በብሔር፣ በፆታም ሆነ በሌላ መልክ የሚካሄዱ ጭቆናዎች የተወገዱበት ፅኑ መሰረት የተጣለውም ስለዚህ ነው፡፡

ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏና ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ስጋት ቀስ በቀስ አርግቦታል፡፡ መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል በተግባር ታይቷል፡፡ በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ መንገድ ከፍቷል። መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጣቸው እገዛዎች፣ በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ አዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመታት መከበር የጀመረውን መብት ተከትሎ በርከት ላሉ ዓመታት ጥቂት በማይባሉ የህብረተሰብ ልሂቃን ዘንድ ሰፍኖ የቆየውን “መበታተን አይቀሬ ይሆናል” የሚል ጥርጣሬ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማስወገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አሁንም መፍጨርጨሮች የቀጠሉ መሆኑና በፌደራላዊ ስርአቱ ላይ የሚወረወሩት ሟርቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

ሃገራችን የራሷ የሆነና ከራሷ ብሄሮች፣ ብሄረሠቦችና ህዝቦች ማህበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ እውነታዎች በመነሣት የምትከተለው ርዕዮተ አለማዊ ፍልስፍና ይዛ ከተነሣች ሠንብታለች፡፡ ፍልስፍናዋና መርኋም ከላይ የተመለከተውን ተጨባጭ ሁኔታ በሚገባ ያገናዘበና በዚህም ፈጣን የተባለ እድገትና ለማምጣት የተቻለበትን ተጨባጭ ውጤቶች ያሣየ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ነው፡፡

ይህ መስመር የማይዋጥላቸውና አለምን በአንድ እጃቸው ላይ ጥለው ጠቅለው ለመግዛት የሚሹ ሃይሎች ደግሞ በተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበትን መርሆ ካልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር አያይዘው የብሄር ታፔላ በመለጠፍ ለማጨንገፍ እየተጉ ነው። በተለይም በዚህ ልማታዊ መስመር ሃገሪቱ በመወንጨፍ ሂደት ላይ መሆኗን የተገነዘቡት እነዚህ ሃይሎች፤ ሂደቱ አስቀድሞ በጥርጣሬ ላይ የነበረውን ህዝብ በማሣመን ደረጃ ላይ ስለመሆኑና በተሣትፎውም በመረጋገጥ ላይ እንደሆነ ከተረዱበት ቅድመ ምርጫ 97 ጀምሮ ሚዲያ በተሠኘ እና ሠብአዊ መብት በተሠኙ ጥይቶቻቸው አክራሪውን እና ጠባብ ብሄርተኛ የሆነውን ስብስብ ከፊት በማሠለፍ መባተላቸውም የማይዘነጋ እና የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ እና በተደራጀ መልክ ፀጥታ ለማደፍረስ ቆርጠው አደባባይ በሚወጡ ሃይሎች ላይ በሚወሠዱ እርምጃዎች ሳቢያ ለከፋ ጉዳት የሚጋለጥ ዜጋ መኖሩ ባያጠራጥርም እነዚያ አለምን ጠቅለው ለመግዛት የሚሹቱ  እና ስለእድገታችን መሠረት የሆነውን መርሆ በእጅ አዙር ለማስቀየር ተኝተው የማያውቁት ስብስቦች ከሃገሬው የመለመሉትን አክራሪና ጠባብ ብሄርተኛ ከፊት አሠልፈው ሠብአዊ መብትና ሚዲያ በተሠኙ ጥይቶቻቸው ኢትዮጵያ አበቃላት ሲሉ መተኮሣቸውም የተለመደና አሁንም ሊወገድ ያልቻለ ጥቃት ነው፡፡

በአንድ አገር ውስጥ እየኖሩ ካሉበት ውሱን አካባቢ ውጭ መምጣትን የባዕድነት መለያ ማድረግ፣ በሌላ በኩል ራስንም ለቀሪዎቹ ወገኖች (ብሔሮች) ባዕድ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ዝንባሌ በረከተ ማለት አገራዊ ዝምድናው ስማዊ (የውሸት) ሆነ፣ ባይታወር የሆኑ ትናንሽ ምድሮች ተፈጠሩ ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ቅርብ አዳሪነት ከኋላ ቀርነት እና ከዝገት  የሚመጣና በዕድገት የሚበጣጠስ ቢሆንም የማደግ ትግላችንን ያሰናክላልና ከወዲሁ ማስተካከል ብልህነት ነው፡፡ 

የአንድ ብሔር/ብሔረሰብ አባል ሆኖ ማኅበረሰባዊ ማንነትንና መብትን ማወቅ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ የአገር ትስስር ዕውነታ እስካለ ድረስም የአካባቢ ልዩነቶችን አልፎ በአገር ልጅነት የመተሳሰብ ተዛምዶ ማበጀት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የእነዚህ የሁለቱ ዕውነታዎች መጣጣም ለዕድገታችን ወሳኝ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ካደበዘዘ ወይም ከተካ ግን ችግር ነው፡፡ በጠባብ ብሔርተኝነትና በብሔራዊ ንቃት፣ በአገራዊ ንቃትና በትምክህተኝነት መካከል ያለው ልዩነት ትልቅ ነው፡፡ የሕዝቦችን ብሔራዊ ማንነትንና የእኩልነት መብትን ማክበር የተሳናቸውና ዳፍንታም ንቀትን የሚረጩ ትምክህተኞች ሺሕ ጊዜ “ኢትዮጵያ” እያሉ ቢጮሁ የአገራዊ ተዛምዶው ቀበኛ ከመሆን የተሻለ አስተዋጽኦ አያበረክቱም፡፡ ኅብረ ብሔራዊ እኛነትን መቀበል ትምክህተኛ መሆን የሚመስላቸውና ሽብልቅነት የያዙ ብሔርተኞችም ዛሬ ስለጠቅላላ ምድሪቷ፣ ስለመላው የሰው ልጅ ደኅንነትና ስለዓለም አቀፋዊ ዜግነት ማሰብ ከያዘው ሥልጣኔ የቱን ያህል እንደራቁና እንደዛጉ  ልንነግራቸው ይገባል።  

ያልተፈቱ የህዝብ ጥያቄዎችን በፍጥነት ከመፍታት አንጻር የመንግስት መንቀራፈፍ ዋጋ እያስከፈለን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ያልተማከለው የፌዴራል ስርአቱ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ስርነቀል ለውጦችን ማስከተሉ በተግባር ተረጋግጧል።  

ከሁሉ በፊት የዘመናት የአገራችን ጭቁን ህዝብች ጥያቄዎች የነበሩት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን በተለያዩ መንገዶች የመግለፅ እንዲሁም የመደራጀትና የመዘዋወር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ ተደርገዋል።  

የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያላቸው መብት እንዳይሸራርፍ በፅናት የታገለው ኢህአዴግ  ህገመንግስታዊ መብታቸው በተከበረበት ሁኔታ በነፃ ፍላጎታቸውና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው ጥረት፤ ህዝቦች በየአካባቢያቸው ራሳቸውን የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመጠቀም መብታቸው በጥብቅ እንዲከበር ከማድረጉም በላይ ህዝቦች በአካባቢዊና በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸውም አድርጓል። ህዝቦች አካባቢያቸውን የማልማት እኩል መብት እንዲኖራቸው በመደረጉም በልማት ተሳታፊና በተሳተፉት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በልማት ወደኋላ የቀሩ አካባቢዎች እንኳን የማስፈፀም አቅማቸው ለማጎልበትና የመሰረተ-ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ በመደረጉ የተመጣጠነ የክልላዊ ልማት እንዲሰፍን ሆኗል። በዚህም አማካኝነት በህገመንግስታችን የተቀመጠው+ አንድ ጠንካራ ትስስር ያለው የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ራዕይ በህዝቦች እኩልነት፣ መከባበርና መፈቃቀድ ላይ ተመስርቶ እንዲገነባ ተደርጓል፡፡

በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት ነው። ኢህአዴግ  የዘመናት የብሄራዊና የመደብ ድርብ ጭቆና የህዝብ ጥያቄዎች ከመሰረቱ ለመለወጥ ከተከተላቸው ቁልፍ የፖለቲካ አቋሞችና ከወሰዳቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎች መካከል የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን፤ የመገንጠል መብቶችን ማረጋገጥ ቢሆንም ከዚሁ ባልተናነሰ አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የመጨረሻው ግብ ሆኖ ተቀምጧል። በዚህም አዲሲቷ ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተች፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ዴሞከራሲያዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት አገር የመገንባት ራእይ ተቀርፆ እየተሰራ  መሆኑን ታሳቢ ያደረገ መከላከል ከህዝቡ ይጠበቃል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy