Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአባይ ላይ ማፍጠጥ የባለቤቱን መብት እየረገጡ አይደለም

1 467

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአባይ ላይ ማፍጠጥ የባለቤቱን መብት እየረገጡ አይደለም

                                                                                          ይልቃል ፍርዱ

የአባይ ወንዝ ግብጾች ባለቤትነቱ የእኛ ነው ማለት ነው የቀራቸው፡፡ ያልተረዱት ነገር ቢኖር የአባይ ወንዝ 86 በመቶ መገኛ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የሚመነጨውም ከኢትዮጵያ እንጂ ከግብጽ መሬት አይደለም፡፡ በሰው ሀብት ያን ያህል የሚያስጮህ፣ የሚያንጨረጭር ምንም ነገር የለም፡፡ እኛ በአባይ ወንዝ እንደአሻን እንጠቀም፤ ባለቤትዋ ኢትዮጵያ ደግሞ በችግርና በረሀብ ውስጥ ትኑር የሚል ከሰብአዊነትና ከሰውኛ የወጣ አስተሳሰባቸው ግብጾች ምን ያህል ራስ ወዳድ መሆናቸውን ያሳያል፡፡

ግብጽ በቅኝ ግዛት ውልና ስምምነት መሰረት አብዛኛው የአባይ ውሀ ድርሻና ድልድል ለእኔ ይገባኛል ባይ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ አልፈረመችና በቅኝ ግዛት ውል አትገዛም፡፡ እንድትቀበለውም የምትገደድበት ምንም ሕጋዊ መሰረት የለም፡፡ ቅኝ ግዛት ተገዝታም አታውቅም፡፡ ግብጾች በሰው ሀገርና ውሀ፤ በሰው ሀገርና መሬት የማዘዝ መብት የላቸውም፡፡ በመሆኑም ወደ ኢትዮጵያ መሬት ሊገቡም በእኛ ውሀም ሊያዙ አይችሉም፡፡

ቀደም ባሉት አመታት የግብጹ ፕሬዚደንት ማርሻል አብዱልፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥተው በነበረበት ሰአት የአባይን ውሀ በጋራ ለመጠቀም እንችላለን ብለው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንደተለመደው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ግብጽንም ሆነ የተፋሰሱን ሀገራትን እንደማይጎዳ ይልቁንም ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንደሚረጋግጥ የግብጽን ውሀ ድርሻ መጠን እንደማይነካ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

በሶስትዮሽ ሰምምነቱ መሰረት ግብጽ ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ መክረው የተስማሙበት ሁኔታ እንደነበረም ይታወቃል፡፡ የሱዳኑ ፕሬዚደንት በቅርቡ  በአፋር የብሔር ብሔረሰቦች በአል ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጎረቤት ሀገራትንም ጭምር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ይሕንን እውነት መስማትም ሆነ መቀበል የማይፈልጉት ግብጾች ለበርካታ ግዜ ሲደረግ ከነበረው የሶስትዮሽ ውይይትና ስምምነት በአፈነገጠ መልኩ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሀ ድርሻችንንና  የግብጽን ጥቅም ስለሚጎዳ አንቀበለውም፤ የአባይ ወንዝ ውሀ ጉዳይ ለግብጽ የሕይወትና የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፤ ስለዚህም እስከ ወታደራዊ አማራጭ ድረስ እናስባለን የሚል ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በሚዲያዎቻቸው አማካኝነት ከፍተዋል፡፡

የግብጽ መንግስት መገናኛ ብዙሀን ፕሬሱም ሆነ ኤሌክትሮኒኪስ ሚዲያው እንዲሁም ሶሻል ሚዲያው ይህንን ወቅት መርጦ በፊት ፕሬዚደንቱ የገቡትን ቃል አጥፈው ለምን በኢትዮጵያ ላይ ግዜ ለይተው ዘመቻ ከፈቱ ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ግብጽ በፊት ለፊት ጦርነት ለመግጠም የሚያስችላት የድንበርና ወሰን ተጋሪነት ከእኛ ጋር የላትም፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያን መውጋትና ማዳከም የምትችለው ከጀርባ በምትደግፋቸው በሚለዮኖች ዶላር አፍስሳ በምታሰማራቸው ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ እሱንም እየሞከረችው ነው፡፡

በዚህ ውስጥ በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግዱ ኃይሎችን በሀገርዋ ቢሮ በመስጠት በማሰልጠንና በማደራጀት በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት በሶሻል ሚዲያ ፌስቡክን ጨምሮ ከፍተኛ የስነልቦና ጦርነት በመክፈት ሕዝብን ከሕዝብ በመከፋፈል የእርስ በእርስ ግጭትና የሰላም መደፍረስ እንዲከሰት ዛሬ በተለያዩ የሀገራችን የተከሰተውን ችግር በማቀጣጠል ረገድ ሰፊ ስራ ሰርታለች፡፡

በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ከተከሰተው የሰላም መደፍረስ ጀርባ ከራሳችን የውስጥ ችግር ባለፈም ትርምሱ እንዲሰፋ ኢኮኖሚያችን እንዲሽመደመድ ግብጽና ኤርትራ በወኪሎቻቸው አማካኝነት እየተጫወቱት ያለው ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ የዚሁ ሁሉ ግብ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስቆም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግብጾች ቢያስቡትም  በምንም አይነት መልኩ እውን ሊሆን ሊሳካላቸው አይችልም፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፡፡

የግድቡ ግንባታ ለአንዲት ሰከንድ አይቆምም፡፡ አይቋረጥም፡፡ ግድቡን ሰርተን ከመጨረስ የሚያግደን ምድራዊ ኃይል መቸም አይኖርም፡፡ ግብጾች ከሚገባው በላይ እራስ ወዳዶች ናቸው፡፡ ከእኛው በሚያገኙት ውሀ እየኖሩ እየከበሩ ሀብት እያገኙበት ግድብ ሰርተው ሰው ሰራሽ ሀይቅም ጨምረው በሰው ንብረት የእነሱ ባልሆነ ውሀ ባለቤት ነን ብለው ሲደነፉ ሊያፍሩ ይገባቸው ነበር፤ ግን ስራቸው በተቃራኒ ሆነና አረፈው፡፡

የደፕሎማሲው ቋንቋ ሰላምና መካባበሩ፤ መደማመጡ፤ ከተሳናቸው የአባይ ውሀ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ መሆኑን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን፡፡ ከቻሉና ከፈለጉ ከቅኝ ገዢያቸው እንግሊዝ የቴምስ ወንዝን ውሀ መጥለፍና መውሰድ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላም እንጂ ለጦርነት ተንበርክካ የምታውቅ ሀገር ነች፡፡ እኛ እንኑር ሙሉ በሙሉ የአባይን የውሀ ድርሻ መጠን ይገባናል የሚለው ደካማ አስተሳሰብ በዚህ ዘመን ፈፅሞ አይሰራም፡

ከተፈለገም ራሱን የአባይን ወንዝ ውሀ ወደ ታላቅ ጦር መሳሪነያት ልንለውጠው እንችላለን፡፡ የሚገባቸው ከሆነ የተጀመረው የታላቁ ሕዳሴ ግንባታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኪሱ ገንዘቡን አዋጥቶ የጀመረው፤ የገነባው፤ ለፍጻሜም እያደረሰው ያለ በመሆኑ ግጭታቸው ከመላው ሕዝብ ጋር መሆኑን ሊያውቁት ይገባል፡፡ ይህ የግብጾች በድንቁርና የተሞላ እኛ በአባይ ውሀ እንደልብ ተጠቃሚ እንሁን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በራስዋ ውሀ አትጠቀም የሚለው የጅል እሳቤ ከእንግዲህ የማይሰራ መሆኑን አውቀው አደብ ሊይዙ ይገባቸዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የሕዝብ የሀገር ፕሮጀክት ነው፡፡ እስከ ፍጻሜው ይቀጥላል፡፡ አይታጠፍም፡፡ ይሕ ፕሮጀክት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ቀዳሚው በአለም ደረጃ ሰባተኛው ግዙፍ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ  ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በታላቅ የኢኮኖሚ እድገትና ግስጋሴ ወደላቀ ምእራፍ ትሸጋገራለች፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ  እድገትና ግስጋሴ በፈጣን ሁኔታ እያሻቀበ መምጣቱ በክፍለ አህጉሩም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነትና ተደማጭነት እያደገና እየገዘፈ መሄዱ ያሳሰባትና ያስጨነቃት ግብጽ የተለመደው ታሪካዊ ሴራ መዶለትዋን ቀጥላለች፡፡

ከጥንት አስከዛሬ ለኢትዮጵያ በጎ አስባ የማታውቅ ሀገር ስለሆነች ይህ ተግባሯ እጅግም አይገርመንም፡፡ የአባይ ወንዝ በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ 86 በመቶ ምንጩ የኢትዮጵያ መሬት ተራሮችና ሸለቆዎች ናቸው፡፡ ከግብጽ በረሀ የሚመነጭ እንኳን ወንዝ ጠብታ ውሀም  የለም፡፡ የውሀው የወንዞቹ ባለቤቶች ኢትዮጵያ ነች። የአባይ ወንዝ ምንጭ የሚገኘው ኢትዮጵያ መሬት ወስጥ እንጂ ግብጽ ውስጥ አይደለም፡፡ ውሀችንን ባሻን፣ በፈለገን መንገድ መጠቀም እንችላለን፡፡ ስለዚህም ነው ግብጽ አደብ መያዝ ይገባታል የምንለው፡፡

ግብጽ ዙሪያ ገባውን ከኢትዮጵያ አጎራባች ሀገራት መሬት በመለመን በመግዛት የጦር ካምፕ ለመመስረትና ኢትዮጵያን በከበባ ቀለበት ውስጥ ለማስገባት የምታደርገውን ጥረት ኢትዮጵያ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ምላሹም ማንም ሊገምተው ከሚችለው በላይ ምንአልባትም ለአለምም እስከሚደንቅ ድረስ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ግብጾች የተረዱት አይመስልም፡፡ ሲሆን ሲሆን ግብጾች ኢትዮጵያን በአከብሮት ነበር መያዝም ሆነ መመልከት  የነበረባቸው፡፡

ዝንተ አለም በማያባራ ሴራ የተጠመዱት ግብጾች ይሄንን ሁሉ ደባና ሴራቸውን ኢትዮጵያና ሕዝብዋ እንደሚያውቁ ሊያውቁትም ይገባል፡፡ ሲያደሙን ሲያቆስሉን ከጀርባ ሁነው ሲወጉን ብዙ ዘመናት ኖረዋል፡፡ ዛሬም ከዚህ ድርጊታቸው አልታቀቡም፡፡ አሁንም በዚህ መሰሪ ሴራቸው ገፍተውበታል፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ የግብጾችን ሴራና ደባ ደግማ ደጋግማ ታፈርሰዋለች፡፡ ትበትነዋለች፡፡ አንድም ምንም የሚሳካላቸው ነገር አይኖርም፡፡ ግብጾች ጠላትነታቸውን  እያሳዩ ያሉት 103 ሚሊዮን ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህም ጦርነታቸው በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት 2 ከሆነችው በጦርነት ውስጥ እድሜ ዘመንዋን ካሳለፈችው ኢትዮጵያ ጋር መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ውሀ ለሁላችንም ይበቃል፤ በጋራ ልንጠቀምበት እንችላለን ነው ያለቸው፡፡ እንደ ግብጾች ፍጹም ራስ ወዳድ የሆነ እኛ እንጠቀም ሌላው በረሀብና በችግር ይለቅ የሚል በአለም ላይ ታይቶና ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግደብ ግንባታ የአገራችንን የመልማት በአህጉርም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን መብት ተከትሎ እየተሰራ ያለ በመሆኑ የኢትዮጵያን ፍጹም ሕጋዊ የተጠቃሚነት መብትና ሕጋዊነት ያረጋገጠ ነው፡፡

በዚህ ደረጃ ግብጽ የምታነሳቸው ጥያቄዎች አንድም አይነት ሕጋዊ መሰረት የላቸውም፡፡ ግብጽ የአባይ ባለቤት ኢትዮጵያ እያለች በአባይ ወንዝ ውሀ ላይ ምንም አይነት ታሪካዊ መብት የላትም፡፡ ሊኖራትም አይችልም፡፡ እንዲህ አይነቱን ተረት ተረት ለጥንት ቅኝ ገዢ ጌቶችዋ ለእንግሊዝ ብታቀርብላት የተሻለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትንና የደረሰበትን ደረጃ ቀን ከለሊት እየተከታተለው ይገኛል፡፡ የግድቡ ባለቤት ሕዝቡ ስለሆነ፡፡

ሕዝቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሎአል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሌሎች ግድቦችንም ገና ደግሞ ደጋግሞ ይገነባል፤ ምክንያቱም ይህ ገና የመልማትና ማልማት ጅምራችን እንጂ ፍፃሜያችን አይደለምና፡፡ ለዚህም ነው የግብፅ በአባይ ላይ ማፍጠጥ የኛን፤ የባለቤቱን መብት እየረገጡ መሆን የለበትም የምንለው። የባለቤትነት መብታችን ይከበራል፤ ልማታችንም ይቀጥላል።

 

  1. ተኽለሃይማኖት says

    በመጀመሪያ ለፅሑፉ ብስለት እና አቀራረብ ከስሜት የፀዳ ምክንያታዊ ኣቀራረብ እናመሰግናለሁ ፨ ኢትዮዽያ ምትጠበቅበት ሓይል ከእግዚኣብሔር ተራዳኢነት ነዉ ፨ እነሱ /ጠላቶቻችን/ የእድሜ ልክ ጠላቶቻችን ሆነው እስከ ኣሁኗ ሰዓት እየተዋጉን ነዉ ፨ ሰለዚ ማገዶ መፍጀቱ ለማይቀር በደንብ ማብሰል ኣለባቹ ፨ ማለቴ ዉሃዉ ሰስንሰጣቸዉ መጀመርያ 100% መቆጣጠር ከዛ እንደየተግባሩ መስጠት (share) ፨ ከንግዲህ ወዲህ በፈቃዱ የሚሄድ ኣባይ መኖር የለበትም እያልንኩ ነዉዉዉ ፨

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy