Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዓሉና ፌዴራሊዝም

0 825

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዓሉና ፌዴራሊዝም

                                                  ዘአማን በላይ

በየትኛውም አካባቢ ለሚከሰቱ ጊዜያዊ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ ከማበጀት አኳያ ፌዴራላዊ ስርዓቱ የራሱ አሰራሮች አሉት። በተለይም የህዝቦችን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር በአማራና በትግራይ እንዲሁም በኦሮሚያና በአማራ ህዝቦች መካከል የተካሄዱት ህዝባዊ ኮንፈረንሶች ማሳያዎች ናቸው።

ሰሞኑን በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝቦች “አብሮነታችን ለዘላቂ ልማትና ሰላም” በሚል መሪ ቃል ያካሄዱት የአንድነት፣ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስን ከፌዴራሊዝም የዚሁ የስርዓቱ የችግር አፈታት ሂደት አመላካች ነው። እነዚህ ሁነቶች በህዝቦች አንድነት፣ አብሮነትና ዘላቂ ሰላም ላይ በቅንጅት ለመስራት አስፈላጊ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ናቸው። ኮንፈረንሶቹ የህዝቦችን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክሩና የሀገርን ልማትና ብልፅግና ከማፋጠን አኳያም ያላቸው ሚና የላቀ ነው።

በእኔ እምነት እንዲህ ዓይነት ኮንፈረንሶች በተለይ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዋዜማ ላይ መከናወናቸው በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ የህዝቦች ግጭት የሚባል ነገር አለመኖሩን የሚያመላክት ነው። ዕለቱ የህዝቦች አንድነትና አብሮ በመኖር አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት ቃል የሚታሰስበት ስለሆነ ነው።

ርግጥ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሌላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ምናልባትም በውስጣቸው የመከሰት ችግር ካለ እየፈቱ አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እንደሚገነቡ የሚያሳዩበት ነው። በበዓሉ ላይ የተንፀባረቀውም ይኸው ነው። ይህን እውነታ ሁሉም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ በዕለቱ እንደተገነዘበው ተስፋ አደርጋለሁ።

በዓሉ የህዝቦችን ማንነት ብቻ ማሳያ አይደለም። በክልሎች መካከል የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንዲሁም ጎልተው እንዲካሄዱ በማስቻል ዴሞክራሲያዊ አንድነት ይበልጥ እየጎለበተ ብሎም የህዝቦች ቅርርብ እየደረጀ መሄዱን ያየንበት ነው ማለትም ይቻላል። በበዓሉ ላይ ለአንድ ዓመት በደቡብ ክልል የቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ለቀጣይ ተረኛ ክልል ተላልፎ መሰጠቱ የሚያሳየው ነገር አለ። ይኸውም የሀገራችን ህዳሴ መገለጫ የሆነው ዋንጫው በኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ የዴሞክራሲያዊ አንድነት መገለጫ በመሆኑ ነው። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሀገራቸውን ልማት በጋራ ለማልማት ያላውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ይህም አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ከሚደረገው ህገ መንግስታዊ ዓላማ የሚቀዳ ነው።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለት፣ አካላቸውን ያጡለትና ለተግባራዊነቱም የተረባረቡለት ነው። ይህ እውነታም በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተስማምተው ያፀደቁትና የሉዓላዊ ሥልጣናቸው ምንጭ ነው። በህገ መንግስቱ መሰረት ይሰበሰባሉ፤ በህገ መንግስቱም አብረው ይኖራሉ።

የሀገራችን ህዝቦች በሙሉ ፈቃደኝነታቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን እየፈቱበት የሀገራችንን አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በመፍትሔነት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ሆኗል።

ህገ መንግስቱ ላለፉት 23 ዓመታት ያጎናፀፈን ድሎች በርካታ ናቸው። የሀገራችን ህዝቦች አንደኛው የሌላኛውን መብት የማክበርና የመቻቻል ተግባሮች ከድሎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተጎናፀፉት ህገ መንግስታዊ መብት ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን ማሳለጥ ችለዋል። ይህ ተግባራቸውም የሀገራቸውን መፃዒ ዕድል የሚወስን ነው። ለዚህም ነው የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መዲና በሆነችው ሰመራ ላይ ተገናኝተው ይህን የወደፊት ዕድላቸውን ለማሳካት ቋጠሮው አብሮነታቸው መሆኑን ያሳዩት።

እናም ሰመራ ላይ እንዳደረጉት ሁሌም በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚሰባሰቡት ይህን ህገ መንግስታዊ ፈቃዳቸውን ለማሳየት ነው። በህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ “….እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” በማለት የእምነታቸው ማሰሪያ እንዲሆናቸው ቃል ኪዳን መግባታቸውን አረጋግጠዋል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማይገሰስ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን በህገ መንግስቱ አንቀፅ 8 ላይ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውንም አውጀዋል።

የፌዴራላዊ ስርዓቱ መነሻ የሆነው ህገ መንግስት የእነርሱና የእነርሱ ብቻ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ የሚገባ ይመስለኛል። በህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን ለማድረግ በነፃ ፍላጎታቸው በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ አላቸው።

መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት የተቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋፊነት በፍትሐዊና ፈጣን ልማት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ በህገ መንግስቱ ገልፀዋል።

በህገ መንግስቱ ለዚህ ዓላማቸው መሳካት የግለሰብና የቡድን መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ሃይማኖቶችና ባህሎች ያለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ ፈቅደዋል።

ኢትዮጵያ የየራሳቸው አኩሪ ባህል ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገር መሆኗን፣ የየራሳቸው መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበራቸውና ያላቸውን በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረው አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት ሀገር በመሆኗ ያፈሩት የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለው የሚያምኑ መሆናቸውንም በህገ መንግስታቸው ላይ በማያሻማ ሁኔታ ደንግገዋል። እነዚህን እውነታዎች ለማሳየትም በየዓመቱ ህገ መንግስቱ የፀደቀበትን ቀን በዙር በሁሉም ክልሎች ውስጥ እየተገኙ ያረጋግጣሉ።

በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የተመሰረተው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም በመሆኑ በግዛት ላይ የሰፈሩ ብሔራዊ ማህበረሰቦች የራሳቸውን ጉዳይ በሚመለከት የራስ አስተዳደርና የጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አስተዳደር ስልጣን እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው። የህገ መንግስቱ የተለየ ባህሪ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ የፖለቲካ ስርዓትን ስላጎናፀፋቸውም በዓሉን ያከብሩታል።

ዕለቱን ህዝቦች በየዓመቱ የሚያከብሩት የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የተከበሩበት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት፣ ራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የነፃ ገበያ መርህና በዚሁ ማዕቀፍ የመሬት አስተዳደር በመንግስትና በህዝብ ስር እንዲሆኑ መወሰናቸውን ለማሰብም ጭምር ነው።

ባለፉት 23 ዓመታት የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን በሚገባ ማጣጣማቸው፣ የጀመሩት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያድግላቸውና እንዲመነደግላቸው ለመስራት፣ ዳግም ተመልሰው በኢ-ሰብዓዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ እንዳይዳክሩ፣ በርካታ መስዕዋትነቶችን የከፈሉበትንና የቃል ኪዳን ሰነዳቸው የሆነውን ህገ መንግስት እንደ ዓይናቸው ብሌን እንደሚጠብቁት ዳግም ቃላቸውን ለማደስ በየዓመቱ ይገናኛሉ።

ርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ፀረ ዴሞክራሲያዊና ኢ-ልማታዊ እሳቤዎችን አምርሮ የሚጠላቸውና ከጫንቃው ላይም እንዲወገዱ በፅናት የታገሏቸው ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ዛሬ ላይ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመመልከትም በአንድነት ይሰባሰባሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ህገ መንግስቱ በራሳቸው የደም ጠብታ የፃፉት የጋራ ሰምምነት ሰነዳቸው በመሆኑ በዕለቱ ተገናኝተው አንዱ ከሌላው እንዲማርና የጋራ ዕድገትን በማምጣት ህዳሴያቸውን ለማረጋገጥ መሰባሰባቸው ተገቢነቱ አያጠያይቅም። ምክንያቱም በዚህ ዓመት “በህገ መንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን” የሚል የጋራ ራዕይን ሰንቀው በመንቀሳቀስ የራሳቸውንም ይሁን የሀገራቸውን ተጠቃሚነት ከፍ…ከፍ እያደረጉ ስለሆነ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy