Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላት የመሪነት ሚና

0 413

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላት የመሪነት ሚና

አባ መላኩ

የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመከተል በግንባር ቀደምትነት ዓለም አቀፋዊ  ኃላፊነቷን እየተወጣች ያለች አገር ናት – ኢትዮጵያ። ኢትዮጵያ በዚህ የኃላፊነት መንፈስ ውስጥ ሆና በመንቀሳቀስ ያተረፈችው ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ከራሷ አልፎ አፍሪካን ጭምር አኩርቷል።

በተደጋጋሚ ጊዜያት በድርቅ አደጋ የምትጠቃው አፍሪካ ያለ አንዳች አስተዋፅኦዋ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ መሆኗን በመከራከር የምዕራባውያንን አገሮች ጭምር ማስደመም የቻለች አገር ሆናለች – ኢትዮጵያ። ምን ይህ ብቻ! የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ አገራትን ድምጽ በማሰማትና ዘመቻውን በማስተባበር ጭምር በዓለም መድረኮች ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች። በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ አገሮችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ድርድር በማስተባበርና ሂደቱን በመምራት በአሸናፊነት ለመዝለቅ ጥረቷን ቀጥላበታለች።

በቅርቡ በጀርመን ቦን በተካሄደው የኮፕ 23 የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ  ኢትዮጵያ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ 47 አገራት ቡድንን በሊቀመንበርነት መርታለች። በዚህም የመሪነት ኃላፊነቷን በሚገባ ተወጥታለች። የኢትዮጵያ ተሳትፎ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድንም አባል ተሳታፊ ናት።

ለአየር ንብረት ለውጥ የሚደረገው የማጣጣሚያ ድጋፍ አስገዳጅነት፣ የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ ድጋፍ፣ ያደጉ አገራት የሙቀት አማቂ ጋዞችን የማስተካከያ እቅድ ማስገባት፣ የፓሪስ ስምምነት የማስፈፀሚያ ህጎችበፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባት፣ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ ራሱን ችሎ የመወያያ አጀንዳ መሆንና ሌሎች ጉዳዮች ኢትዮጵያ በድርድሩ ሊቀመንበርነትና በአባልነት የምትሳተፍባቸው ቡድኖች የያዙት የጋራ አቋም ነው። እነዚህ አጀንዳዎችም በተደረገው ብርቱ ጥረት ተቀባይነት ማግኘቱን ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመንደፍ ለታዳሽ ኃይል ትኩረት የሰጠች አገር ነች። የኃይል ልማት ፖሊሲው ከነባሩ ወይም ባህላዊ መንገድን ተከትሎ ከሚደረገው የኃይል ማመንጨት ሥራ ቀስ በቀስ ዘመናዊ የኃይል አጠቃቀም መከተልንና መሸጋገርን ማዕከል ያደረገ ነው።

አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም የማዳረስና ለምጣኔ ሀብቱም ዕድገት በቂ ኃይል የማቅረብ ሃሳብንም ይዟል። ፖሊሲው ለአገር ውስጥ የኃይል ምንጭ ቅድሚያ በመስጠት ራስን መቻልን ያልማል። እንዲሁም ንፁህ ኃይልን ቆጥቦ በብቃት በመጠቀም የአካባቢ የአየር ሁኔታ ጤናማነትን በማስቀጠል የበኩሉን ሚና ይጫወታል።  

ኢትዮጵያ ባልተራዘመ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የመሰለፍ ራዕይ ሰንቃለች። የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አገሪቱ በተከታታይ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ያላት የምጣኔ ሀብት ባለቤት አገር ሆኖ እንደምትቀጥል መተንበይ ከያዙ ሰነባብተዋል።  

ይህን ስኬታማ ለማድረግ የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ልማቱ መሠረት ማድረግና የኤክስፖርት ደረጃን ለማሳደግ ታስቦም እየተሰራ ነው። ውጤትም ተገኝቶበታል። አገሪቱ ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ ራዕይዋን እውን ማድረግ የምትችለውም  ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ፈተና ሆኖ የተጋረጠውን የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት መዋጋትና ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ሲቻል ብቻ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ሃብት እጥረት ነዳጅን በማስገባት በሚወጣ የውጭ ምንዛሪ ምክንያት የሚመጣ የተፈጥሮ ክስተት ነው። ይህ ክስተት በተለይ ልማታቸውን በተፈጥሮ ዝናብ ላይ ጥገኛ ያደረጉ አገሮችን ይጎዳል። ይህን ችግር ለማስወገድ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ጭምር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።

በዚህ ስትራቴጂ የሚወሰዱ ርምጃዎች ሁሉ ለኢንቨስትመንት አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጡና የምጣኔ ሀብት ዕድገትን በቀጥታ ከሚያፋጥኑ ከተጨማሪ እሴቶች ጋር የሥራ ፈጠራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስትራቴጂው የዓለም የሙቀት መጠንን በመቀነስ ረገድ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቷን እንድትወጣ የሚያስችል ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል።   

የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ኢትዮጵያ በቀጣዩቹ ዓመታት 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋታል። ታዲያ ይህን ግብ ለመድረስ በሁለትዮሽ ግንኙነት አማካይነት ከሚካሄዱ የዲፕሎማሲ ሥራዎች፣ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ እንዲሁም የግሉ ሴክተር ከሚጫወተው ሚና ጋር ተገናዝቦ ገቢራዊ እየሆነ ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያና አፍሪካ ለዓለም አየር ንብረት ለሚያደርጉት የታዳሽ ኃይል ሥራዎች በጎ አስተዋጽኦ ማካካሻ የገንዘብ ድጋፎች ታሳቢ ሆነው ይቀርባሉ።

በጀርመኑ ቦን በተካሄደው ድርድር ላይ ያደጉ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ 90 ሚሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ተጋላጭ ለሆኑ ታዳጊ አገራት 100 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ይህም ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ውጤት ማሣያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ ካደረገችው ንቁ ተሳትፎ ባሻገር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልትን ነድፋ በመተግበሯ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ አድናቆትን አትርፎላታል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በሃያ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ 150 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል። ከአገር ውስጥ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከሁለትዮሽ ትብብርና ከሌሎች ምንጮች ይገኛል ተብሎ የሚታሰብ ነው።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በዕቅዷ ውስጥበማስገባት መተግበር ጀምራለች። ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣ የገጠሩ ኅብረተሰብ የአርባ ቀናት ነጻ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች ሥራዎችና የአረንጓዴ ልማትን መሠረት በማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ዓለም አቀፍ እውቅናን አስገኝተዋል። አርአያ የሆኑ ተግባሮች ተብለው ተሞካሽተዋል። እስካሁን በተካሄደው ድርድር መልካም ሊባሉ የሚችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል። በቀጣይ በጠንካራ ትብብር መሥራትን ይጠይቃል። ይህ ተግባር ተጠናክሮ ከቀጠለ ዓለም አቀፍ ድጋፉ እንደሚጨምር ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልቷን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ካደረገች የምትፈልገውን ድጋፍና ውጤት እንደምታገኝ የብዙዎች እምነት ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy