Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እነ ግብፅ ትናንት እና ዛሬ

0 439

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እነ ግብፅ ትናንት እና ዛሬ

                                                          ደስታ ኃይሉ

እነ ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግድቡ ገና በተጀመረበት ወቅትና በአሁኑ ሰዓት እያራመዷቸው ያሉትን አቋሞች ሲነፃፀሩ የአቋም ለውጥ የሚታይባቸው ናቸው። በተለይም ግብፆች ትናንት “አንድም ጠብታ ውሃ አይነካብንም” በማለት ፍትሐዊ ያልሆነውን የቅኝ ግዛት ውል ለማስፈፀም ደፋ ቀና ይሉ እንደነበር ይታወቃል።

እንደሚታወቀው የአባይ ውኃን የመጠቀም መብት ቅኝ ገዥዎቹ ባዘጋጁትና በቀይ ካርድነት ሲያገለግል በቆየው እ.ኤ.አ የ1929 እና 1959 “የናይል ውኃ አጠቃቀም ስምምነት” ተገድቦ ቆይቷል፡፡ “የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ” እንዲሉ የተፋሰሱ ሀገራት በመብታቸው እንኳንስ ሊጠቀሙ ቀርቶ ሃሳብ እንዳላቸው እንኳን ቢሰማ ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግር ቀድመው የሚያውቁት ስለሆነ “አይነኬ” ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡

ምንም እንኳን ግብጾች የውሃው “የታሪካዊ መብት” ተጠቃሚዎች እንደሆኑና ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ወንዙን እንዳይጠቀሙ መብታቸውን ገድበው በመኖራቸው ሳቢያ ዓባይን እንደ ግል ሀብታቸው ቢቆጥሩትም፤ በእኩልነት፣ በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት ውኃውን የመጠቀም መብት ከላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት በኩል መነሳቱ ግድ ሆኗል—ሁሉም ነገር ባለበት አይቆምምና።

ሀገራችን የናይል ወንዝ አጠቃቀምን አስመልክቶ በእንግሊዝና በግብጽ የተካሄደው የ1929ኙ ስምምነትንም ይሁን በግብጽና በሱዳን መካከል የተፈረመው የ1959ኙ ስምምነት ተቀባይነት እንደሌለው ስታሳውቅና አቋሟን ስታንጸባርቅ መቆየቷ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ የስምምነቱን ኢ-ፍትሃዊነትንም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መንግስታት ሁሉ በአባይ ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል፡፡ እርግጥም “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንደማይታሰብ ሁሉ፤ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ያላከተተውና በሁለቱ የታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት መካከል የተካሄደ ስምምነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑ አይካድም፡፡ ሆኖም የላይኛው ተፋፈስ ሀገራት አቋም ሰሚ ጆሮ ማግኘት አልቻለም፡፡

በተለይም በግብጾች በኩል ይህ “የቅኝ ገዥዎች” ስምምነት የማይጣስ መሆኑን ከመግለፅ ባለፈ፣ ከዛቻ አዘል ማስፈራሪያዎች ጋር ሲሰነዘር ቆይቶ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያን ዋነኛዋ የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ዓለም ያወቀው ሃቅ ነው፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ግብጾች ሊያውቁት የሚገባው ነገር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ የምትሰጥበት ጊዜ ያከተመ መሆኑን እንዲሁም በእኩልነትና ምክንያታዊነት በጋራ የመጠቀም መርህ ጽኑ አቋሟ ሊቀለበስ እንደማይችል ነው፡፡

ለነገሩ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንደሚባለው እነዚህ በሙባረክ ዘመን እሳቤ የሚዳክሩ አሮጌ ፍራሽ አዳሽ የግብፅ ሚዲያዎችና አንዳንድ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ አቋም በሚገባ ስለሚያውቁት እዚህ ላይ ብዙ ማለት አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡

ሆኖም ግብፆች በዘመነ መሐመድ ሙርሲ ዘመን የያኔውን የቅኝ ግዛት ውል በማስታወስ “በጦር ሃይል እንጠቀማለን፣ አገሪቱ እንዳትረጋጋ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች እንጠቀማለን…ወዘተ” ሲሉ ማድመጣችንን እናስታውሳለን። ጉዳዩ አዲስ ባይሆንም ነገርዬው ማስፈራራት ነበር። ግና እነርሱ ያሻቸውን ቢሉም የኢትዮጰያ አቋም የማይለወጥ ነበር—ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና በጋራ የማደግ መርህ።

መሐመድ ርሲን አስወግዶ በእግሩ የተተካው የፕሬዳንት ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለጋራ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ ግልፅ መልዕክት እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህም በወቅቱ የግብፅ መንግስት በዓባይ ጉዳይ ላይ ለያዘው አቋም ቀደም ሲል የነበሩት ገዥ መደቦች እንዲሁም የመሐመድ ሙርሲ ማስፈራሪያ እንደማይሰራ የተገነዘበ መሆኑን አንዳንድ ተንታኞች ሲገልፁ ነበር።

እርግጥም ዓለም በግሎባላይዜሽን የትስስር ድር እንደ አንድ መንደር በምትታይበት በዘመነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ተግባብቶ መፍታት አንዱ የስልጣኔ መገለጫ ነው። ማናቸውም አለመግባባቶች ባህሪያዊና በሰው ልጅ መስተጋብሮች ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ክስተቶች በመሆናቸው መፍትሔያቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መሆን እንደሌለበትም ይታመናል።

እናም በማናቸውም ቦታ የሚከሰቱ አለመግባባቶች ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ አካላት መካከል የሚከሰት በመሆኑ የመፍትሔ አማራጮች ሊሆኑ የሚችሉት ሁሉም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበት መንገድ እንጂ፤ ባለፉት አሮጌ ዘመናት አሳፋሪ ማንነት እየቆዘሙና ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብን እያቀነቀኑ አንደኛው በሌላኛው ላይ ቀረርቶና ፉከራ በማሰማት የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም አሊያም እኩይ ሴራዎችን በመጎንጎን ተፈፃሚ የሚሆን አይደለም።

ይህን መሰሉ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ምልከታም የትኛውንም ወገን ቢሆን አሸናፊ የማያደርግና የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ፤ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ በአላዋቂ ተጓዥነት መገለልን በማስከተል የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው። “በትናንት በሬ ያረሰ የለም” እንዲል የሀገራችን አርሶ አደር፤ የትናንቱ አሮጌ አስተሳሰብ እንዳለቀ ሸማ ወልቆ መጣል ያለበት ትናንት ነው—ዛሬ ላይ እንኳንስ ቦታ ሊኖረው ቀርቶ አዳማጭም የለውምና።

በተለይም ለዘመናት የአፍሪካንና የልጆችዋን ማንነት ሲያዋርድ፣ ልጆችዋን በባርነት ሲሸጥና ሲለውጥ እንዲሁም አንጡራ ሃብቶቿን ሲቦጠቡጥና ለራሱ ጥቅም ሲል መርዛማ ውሎችን ሲከትብ የኖረው የቅኝ አገዛዝ ኢ-ሰብዓዊ አስተሳሰብ በፀያፍነቱ ሳቢያ ዛሬ ላይ ከታሪክነት በዘለለ ሰሚ ጆሮ የለውም።

ይህን ፀረ-ሰውዓዊ እሳቤን ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው ለመጣልም አፍሪካውያን በተናጠልም ይሁን በቅንጅት ታግለዋል፤ ህይወታቸውንም ቤዛ አድርገዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ቤት ንብረታቸውንም አጥተዋል— “ሰውነታቸውን” ከሰው በታች አውርዶ በመፈጥፈጥ እንዳሻው ሲያደርጋቸው የነበረውን አስከፊ ተግባር ከነ ግሳንግስ አስተሳሰቦቹ ለማስወገድ።

እናም ይህ ዘረኛ ተግባር ዛሬ በአፍሪካ ልሳነ-ምድር እንኳንስ አስተሳሰቡ ገቢራዊ ሊሆን ቀርቶ የሚታሰብ አይደለም። ምንያቱም አርጅቶ የተቀበረው የቅኝ አገዛዝ እሳቤ በያኔው የአህጉሪቱ ድርጅትም ይሁን በአሁኑ ህብረት ውስጥ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ነው።

ግብፆች በአል ሲሲ የስልጣን ዘመን ይህን ተገንዝበው ወደ ሰላማዊ የጠረጴዛ ውይይቶች መምጣታቸው እሰየው ነው። ሆኖም አሁንም የሚታየው ነገር “የቅኝ ግዛት ውሎች ሊከበሩልኝ ይገባል” የሚለው አስተሳሰብ ቀደም ሲል ባነሳኋቸው እውነታዎች ሳቢያ ፈፅሞ ተቀባይነት የላቸውም።

በመሆኑም ዘላቂው መፍትሔ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ላይ ተመልሶ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኘውን ጥቅም በጋራ መቋደስ ብቻ ይመስለኛል። ይህ ካልሆነ ግብፅ ከትናንት ዛሬ የተሻለ የመነጋገርና የመመካከር አቋም ላይ በመሆኗ ጥሩ ነው ሊባል ቢችልም፤ አሁንም ድንገት ትዝ እያላት የምትገባበት የቅኝ ግዛት ውሎች አባዜ በአፍሪካዊያንም ይሁን ለአህጉሪቱ ነፃነት ፋና ወጊ በሆነችው ኢትዮጵያ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው አስተሳሰብ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል።  

 

   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy