Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጣቱ ከኪራይ ሰብሳቢዎች ተጽዕኖ ይጠበቅ!

0 426

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጣቱ ከኪራይ ሰብሳቢዎች ተጽዕኖ ይጠበቅ!

 

ስሜነህ

 

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ወጣቶች ዴሞክራሲያዊ አመለካከት፣ የሙያ ብቃት፣ ክህሎትና መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸው ዜጎች ሆነው ሀገሪቱ በተያያዘችው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የልማት እንቅስቃሴዎች በብቃት፣ በንቃትና በስፋት ተሳትፈው ከውጤቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ተልዕኮም ዕውን መሆን የነበሩትን የፖሊሲና ተቋማዊ ክፍተቶች በቅድሚያ መሙላት የግድ ይላልና በፌዴራል ደረጃ የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተል፣ የሚመራና የሚያስተባብር የወጣቶች እና የስፖርት ሚኒስቴር እንዲደራጅ ተደርጓል።  

 

ሚኒስቴሩ የሚመራበትና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሎ የተቀረጸው የወጣቶች ፖሊሲም በዋናነት ወጣቶች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና በመልካም አስተዳደር፤ እንዲሁም በልማት ግንባታ ሂደቶች ውስጥ በተደራጀ አኳኋን ተሳትፎ አድርገው ከልማቱ  በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያለመ ነው። የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጋገጥ ወጣቶች ራሳቸውን በማደራጀትና በማብቃት የመሪነት ሚና ወጫወት የሚገባቸው መሆኑ ባያጠያይቅም፣ ይህን ጥረታቸውን በመደገፍ ረገድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በተቀናጀ አኳኋን ተንቀሳቅሰው አቅማቸውን የመገንባትና የማብቃት ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባም።

ለአንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ባህላዊ ልማት የሁሉም ኀብረተሰብ ክፍል ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው።  ወጣቶች ደግሞ አዳዲስ ሀሳቦችን ለመቀበል እንዲሁም የፈጠራና የማምረት እምቅ አቅም ያላቸው በመሆኑ በሁሉም የልማት ዘርፎች ውስጥ የላቀ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ መሆኑ አያከራክርም።ይህ የሚሆነው ግን እምቅ ሀይላቸውንና ችሎታቸውን በተግባር ለማዋል የሚያስችል ምቹ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ሲፈጠርላቸው ነው። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ፈጥነው  ተስፋ በመቁረጥ እና ሁሉንም ነገር በመተው የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ በገለልተኛነት ከርቀት ሊመለከቱ የሚችሉበት እድል የሰፋ ይሆናል። አልፈውም ለማኀበራዊ ጠንቆች ተጋላጭ ስለመሆናቸው በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችም ያረጋግጣሉ ።

በአገራችን የወጣቶች ጉዳይና አደረጃጀት ተገቢው ትኩረት ካለማግኘቱ የተነሳ በወጣቶች፣ በቤተሰብ፣ በህበረተሰብ፣ በሌሎች ተባባሪ አካላት እና በመንግስት መካከል የጋራ ትብብርና ቅንጅት ተፈጥሮ በተፈለገው መጠን ሲሰራበት ያልነበረ በመሆኑ በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስርአቱ በፈጠረው እድል ተጠቅመው እራሳቸውን በእውቀት ባበቁ ወጣቶች ልክ የስራ እድል አለመፈጠሩ ለተለያዩ አሉባልታዎች እና የግጭት አጀንዳዎች ተጋላጭ እየሆኑ ነው። በጥቅሉ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በብቃት ተሳትፈው፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ልማትን በማፋጠን የራሳቸውንና የኀብረተሰባቸውን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፈርጀ-ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ሁኔታዎች ያልተመቻቹላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የወጣቶቻችን ተጋላጭነት በመጠንም ሆነ በጥልቀት እየጨመረ ነው።

 

ስለሆነም ዛሬ በአገራችን የተፈጠሩትን ምቹ የፖለቲካ ሁኔታዎች፣ ለልማት የሚበጁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈው ተግባር ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውና ፖሊሲዎቹንም በብቃት ለማስፈፀም የአቅም ግንባታ ስራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረትና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ተግባራዊ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ወስዷል። በተለይም ወጣቶች በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ ራዕይና አመለካከት ይዘው፣ በራሳቸውና በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ኖሯቸው በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ባህላዊ ልማቶች የበኩላቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሏቸውን ፕሮግራሞች በመንደፍ እና ፓኬጆችን በመቅረጽ በየደረጃው ርብርብ እየተደረገ ነው።

 

የኢትዮጰያን ወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በተመለከተ በተለያዩ የፖለቲካ ስርዓቶች እንዲሁም ታሪካዊ ወቅቶች ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ይከናወኑ እንደነበር ይታወቃል። ሀገርን የሚመለከቱ የጋራ ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በአንድነት መንቀሳቀሳቸው የነበረና ያለ ህያው ታሪካቸው ነው። ዘመናዊ ትምህርት የማግኘት ዕድል ባልነበረበት ዘመን በግብርናና በዕደ-ጥበብ በመሠማራት አገራቸውን ከመገንባት ጐን ለጐን የውጭ ወራሪን ይከላከሉ እንደነበር የሚያወሱ የታሪክ ድርሳናት፤ ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ ሁለንተናዊ ጭቆናን በመቃወም ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለተሻለ አስተዳደር በጽናት የታገሉ ስለመሆናቸውም በድርሳናት ተከትበዋል።ወጣት ተማሪዎች በተለይ ከ1953 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት ዓመታት ውስጥ ኀብረተሰቡን በንቃትና በስፋት በማንቀሳቀስ የትግል ፋና ወጊ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ወጣት ተማሪዎች፣ ወጣት ሠራተኞችና ወጣት አርሶ አደሮች፤ በአንድ በኩል በራሳቸው ተነሳሽነት ከመንግስት ዕውቅና ውጪ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስት ድጋፍ በቅርጽና በይዘት የተለያዩ ዓላማዎች በነበሯቸው ማኀበራት፣ ድርጅቶችና ስብስቦች በመታቀፍ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል። የመሬት ላራሹን፣ ብልሹ የአገዛዝ ሥርዓትን ለማስወገድ እና መሰል የሕዝቦችን ጥያቄዎች በማንገብ ለውጥ ለማምጣት ትግል አካሂደዋል። የሕይወት መስዋዕትነትም ከፍለዋል። ይህም ሲሆን ከ1966-1983 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የወጣቶች አደረጃጀትና እንቅስቃሴዎች ሁሉ በወቅቱ ከነበረው የፖለቲካ አመለካከትና ፍላጐት ጋር እንዲጣመሩና የነበረውን ስርዓት በቅርብ ሊያገግሉ በሚችሉበት መንገድ በመቃኘታቸው ወጣቶች ከዴሞክራሲያዊ አሠራር ተገልለው የታዩበት ወቅት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በዚህ ፈታኝ ወቅትም ሥርዓቱን በመቃወም አያሌ ወጣቶች ለሕዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሕይወት መስዋዕትነት እስከመክፈል ድረስ ታግለዋል። ይህም ረጅም የትግል ጉዟቸውና መስዋዕትነታቸው አገራችንን አሁን ለምትገኝበት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያደረሳት መሆኑን ስለአጀንዳችን መገንዘብ ይገባል።

 

በገጠርም ሆነ በከተማ መደበኛ ባልሆነው የሥራ ዘርፍ ውስጥ ተሰማርተው ያሉትን ወጣቶች ሁኔታ በሚመለከት የተሟላ መረጃ ማግኘት ባይቻልም በአሁኑ ወቅት በገጠር የሚገኙ ወጣቶች ከግብርና ሥራ ውጪ ሊሰማሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ ከሆነው የገጠር ወጣቶች መካከልም በድህነት ምክንያትና የተሻለ ሕይወት እናገኛለን በሚል ተስፋ ወደ ከተማ እየፈለሱ ስለመናቸውም በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ የተሰጡ ማብራሪያዎች ያረጋግጣሉ። በከተማም ሥራ የማግኘት እድላቸው የተጣበበ በመሆኑና እንደተመኙትም ሆኖ ስለማያገኙት እጣ ፈንታቸው ለልዩ ልዩ ማህበራዊ ጠንቆች መጋለጥ ከመሆኑ ባለፈም ሌላ ተልእኮ ላነገቡ እና ሀገርን ለትርምስ እያመቻመቹ ለሚገኙ ሃይሎች ሰለባና መጠቀሚያ መሆናቸው በተግባር እየተስተዋለ ነው።

 

በአሁኑ ጊዜ ግን ችግሮችን ሊቀርፍ የሚችል የትምህርትና የሥልጠና ፖሊሲ እንዲሁም ሥርዓተ-ትምህርት ተቀርጾ በሥራ ላይ ውሏል። በርግጥ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ የተጓዳኝ ትምህርት ኘሮግራሞች ተሟልተው ባለመገኘታቸው ወጣቶች ያላቸውን የተፈጥሮ ዝንባሌ አውቀውና ተገንዝበው ልዩ ችሎታቸውን የበለጠ በማዳበር ሁለገብ የሆነ ዕውቀት እንዲያገኙ ምክንያት ሆነዋል። እናም ትምህርትና ሥልጠናው በአፈፃፀም ችግሮችና በአቅም ማነስ ምክንያት ሁሉንም ወጣቶች ተጠቃሚ ሊያደርግ እንዳልቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚሁም ላይ ወጣቶች ባህላዊ እሴቶችን ከሚቀስሙባቸው አያሌ ተቋማት ውስጥ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ት/ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የባህል ተቋማትና የሃይማኖት ድርጅቶች ዋነኞቹ ቢሆኑም በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ ተቋማት ማግኘት የሚገባቸውን ያህል አገልግሎቶች ባግባቡ እያገኙ እንዳልሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎች ያሳያሉ። ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወጣቶች ባህላዊ ዕሴቶቻቸውን ጠንቅቀው የማያውቁ፣ ይልቁንም በውጪ ባህሎች ተፅዕኖ ስር የወደቁ፣ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጠቂ፣ ላልተፈለገ የሥነ-ምግባራዊ ድርጊቶች እና ለልዩ ልዩ ማህበራዊ ጠንቆች ከመጋለጥ አልፈው ውድ የሆነውን የህይወት ዋጋ በሚያስከፍሉ ግጭቶች ሰለባ በመሆን ላይ ናቸው።

 

ሰለባ የመሆናቸው ጥግጋት ደግሞ ስፖርትና መዝናኛ ለወጣቶች የጤና፣ የአካልና የአዕምሮ መገንቢያና የዕረፍት ጊዜን ማሳለፊያ ብቻ ሳይሆኑ ማህበራዊ ኑሮን የሚማሩበትና ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት የማድረግ የሕይወት ክህሎት የሚያዳብሩበት መድረክ መሆኑን እስከመዘንጋት ባደረጉ ክስተቶች ተገልጧል።በእርግጥ የስፖርት ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዮት ያለመኖር ወጣቶችን በሥነ-ምግባር በማነጽ፣ ጤናማና አምራች ዜጐችን በመፍጠር ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።  

 

ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ መረዳት የሚቻለውም አገሪቱን ከድህነት በማላቀቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚጠበቅበት ዋነኛው የልማት ኃይል በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ ባለመመራቱ ምክንያት በሚፈልገው አቅጣጫ ለማንቀሳቀስ ያልተቻለ መሆኑን ነው።  ስለዚህ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመለወጥ በዋናነት ጥቅም ላይ መዋል የሚገባውን የሰው ኃይል አገሪቱ ለምታካሂደው የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ኃይል በሚሆንበት መልኩ አደራጅቶና አቅሙን አሟጦ በአግባቡ እንዲንቀሳቀስ ማስቻል ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከላይ ከተመለከቱት ባለድርሻ አካላት ሁሉ ይጠበቃል።

 

ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ያለው፣ በዕውቀትና ሙያዊ ክህሎት የጐለበተ፣ የተደራጀና በሥነ-ምግባር የታነፀ ወጣት ትውልድ እንዲፈጠር ማድረግ የእነዚህ ባለድርሻ አካሎች ሁሉ ግዴታና ወቅቱ የሚጠይቃቸው ቁልፍ ተግባር ነው። ወጣቶች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀ አኳኋን የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ማብቃት ከነዚሁ አካላት ይጠበቃል።

 

ስለሆነም ወጣቶች በሚያደርጓቸው እንቅስቅሴዎች፣ ግንኙነቶችና ተሳትፎዎች ሁሉ በመካከላቸው ላሉት የብሔረሰብ፣ የጾታና የእምነት ልዩነቶች ዕውቅና በመስጠትና በማክበር አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኀበረሰብ የመፍጠር ዓላማ መሰረት ያደረገ መርሆ መሆኑን መሰረት ያደረገ የግንዛቤ ስራ መስራት ከነዚሁ ከላይ የተመለከቱ ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ። ወጣቶች በመካከላቸው ያሉትን ልዩነቶች በእኩል ዓይን የማየት፣ የመቻቻልና የመከባበር ባህልን አዳብረው በኀብረት በመንቀሳቀስ ለጋራ ዓላማ በአንድነት መንፈስ መነቃነቅ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታዎችም መፍጠር ያስፈልጋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ  የማኀበረሰቡንም የባህልና ያኗኗር ልዩነቶች ባግባቡ አውቀውና ተረድተው ላጠቃላዩ የጋራ ራዕይና ዓላማ ስኬት የድርሻቸውን ሊያበረክቱ የሚያስችላቸውን ጥርጊያ መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

 

በወጣቶቻችን በኩልም መብትንና ጥቅምን ለማስከበር በነፃ ተደራጅቶ በተቀናጀ አኳኋን መንቀሳቀስ፤ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ በመልካም አስተዳደርና የልማት ግንባታ ጥረቶች ውስጥ በንቃት በመሳተፍ መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር በተናጠልና በተበታተነ ሁኔታ ከመንቀሳቀስ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን መንቀሳቀስ የሚያስገኝላቸውን ከፍተኛ ፋይዳ ተረድተው ይበጀናል በሚሉት የጋራ ዓለማ ዙሪያ በመደራጀት የተሳትፏቸውንና የተጠቃሚነት ሚናቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል።

 

ወጣቶች በሕገ-መንግስቱ ዓላማዎችና መርሆዎች እንዲሁም በሀገሪቱ ዋና ዋና ፖሊሲዎች ዙሪያ ግንዛቤ ጨብጠው በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አመለካከትና እምነት እንዲፈጥሩ፣ እንዲሁም በነፃ ፍላጎትና በፈቃዳቸው ተደራጅተው በዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር ግንባታ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቅሴ ውስጥ በንቃት ተሳትፈው መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን እንዲያስከብሩ አመቺ ሁኔታዎች መፍጠር ደግሞ የመንግስት ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል።

 

በሀገሪቱ ዲሞክራሲንና ፍትሕን እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ወጣቶች በንቃት በመሳተፍ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማስፋፋት ወይም ማበልጸግ (Promote) ፣ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የሚዋጉ ዜጎች እንዲሆኑ ማብቃትም ተያያዥ የመንግስት ተግባር ነው።

 

ወጣቶች የመቻቻል፣ አብሮ የመኖር፣ የመከባበር፣ የመወያየትና ለሰላም የመቆም ዴሞክራሲያዊ ባህሉችን አዳብረው በአተገባበራቸው ላይ በንቃት እንዲሳተፉና ከመጨረሻ ፍሬውም በአግባቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር ደግሞ መሰረታዊው እና ሃገራችንን ሊያተራምሱ ካሰፈሰፉ ሃይሎች የመፋቻው መንገድ ይሆናል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy