ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች
ብ.ነጋሽ
ህዳር 20 እና 21 ቀን 2010 ዓ/ም በኮትዲቮዋር አቢጃን የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት 5ኛ የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በጉባኤው ላይ ተሳትፏል። በጉባኤው ላይ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ተሳተፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝም በጉባኤው ላይ ከተሳተፉት መሪዎች አንዱ ነበሩ። ጉባኤው በአፍሪካ እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች የአጠቃላይ የአህጉሪቱን ህዝብ 60 በመቶ የሚሸፍኑ መሆናቸውን መነሻ በማድረግ ለወጣቶች መልካም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ላይ ያተኮረ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ሰላምና ደህንነት፣ የህዝብ ዝውውርና ስደትም ላይ ተወያይቷል።
የአፍሪካና አውሮፓ ህብረቶች የመሪዎች ጉባኤ በቀዳሚነት በወጣቶች ላይ ያተኮረ ነበር። ጉባኤው የአፍሪካ ወጣቶች ህይወት የሚቀየርበት አሰራር እንዲዘረጋ ውሳኔ አሳልፏል። በህገ ወጥ ስደት፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በሰላምና ደህንነት፣ ሽብርተኝነትን በመከላከል፣ በንግድና ኢንቨስትመንትና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያም መክሯል። ጉባኤው የአፍሪካ ወጣቶች በስፋት ወደ አውሮፓ እየተሰደዱ የመሆኑ ጉዳይ በሰፊው የተነሳበት ነበር። ይህ ሁኔታ አህጉሪቷን ያመምረት አቅም ካለው ወጣት ሃይል እየነጠላት መሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ወጣቶች በገፍ ወደ አውሮፓ መጓዝ በአውሮፓ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑ ተነስቷል። አንዳንድ ወገኖች ይህን ሁኔታ ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ማጋበሻነት እየተጠቀሙበት መሆኑን የሚያመለክቱ እውነታዎች መኖራቸውም ተነስቷል። አፍሪካዊያን ስራችሁን እየቀሟችሁ ነው በሚል ፕሮፓጋንዳ የአውሮፓን ፖለቲካዊ ሁኔታ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ጎልቶ ወጥቶ ወደነበረው የዘረኝነት እንቅስቃሴ እየወሰደ መሆኑን የሚያመለክቱ ሁኔታዎች እየታዩ ነው። ይህ አካሄድ የዓለምን ፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት የፈጠረበት ደረጃ ላይ ደርሷል።ይህ ሁኔታ የወጣቶችን ስደት ጉዳዩ የአፍሪካና አውሮፓ የጋራ ችግር ከመሆን ዓለፎ ዓለም አቀፋዊ ችግር እንዲሆን አድርጓል።
በዚህ መነሻነት በአቢጃኑ ጉባኤ የተሳተፉት የአፍሪካና አውሮፓ አገራት መሪዎች በሁለቱም አህጉራት ወጣቶች ላይ አተኩረው ለመስራት፣ ህይወታቸውንም ለመቀየር ቃል ገብተዋል፤ የፖለቲካ አቋምም ይዘዋል። ጉባኤው የፖለቲካ አቋም የሚነገርበት ብቻ እንዳይሆንና ውሳኔው ወደ መሬት ወርዶ በተለይም የአፍሪካ ወጣቶች ህይወት የሚቀየርበት የክትትል ስርዓት እንዲዘረጋም ተወስኗል።
የአፍሪካ ወጣቶች ሃገራቸውን ለቀው ወደ አውሮፓ እንዲሰደዱ ያደረጋቸው ምክንያት መኖሩ፣ ይህም በዋናነት ኢኮኖሚያዊ መሆኑ ላይ ስምመነት ተይዟል። የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ ማስቆም ባይቻልም በተለይ ወጣቶች ወደ አውሮፓ የሚያደርጉትን ስደት በአይነትም ሆነ በመጠን ጤናማ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግም ታምኖበታል። ጉባኤው ስደተኛ ወጣቶች እንደ መሸጋገሪያ በሚጠቀሙባት ሊቢያ እየተካሄደ ያለውን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የባርያ ንግድ አውግዟል። ጉዳዩ ተጣርቶ እንዲቀርብለትም መመሪያ ሰጥቷል።
እንግዲህ ከላይ እንደተገለጸው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ከአፍሪካ ሃገራት አልፎ አሳሳቢ ዓለም አቀፋዊ የዘት ያለው ቀውስ መሆን ከጀመረ ከራርሟል። ኢትዮጵያም የኤርትራንና የምእራብ አፍሪካ ሃገራትን ያህል ባይሆንም በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ዜጎቿ ላይ በሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት ችግር ውስጥ ከገቡ ሃገራት አንዷ ነች። በተለይ በህገወጥ መንገድ ወደመካከለኛው ምስራቅ የሚሄዱና ለከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚጋለጡ ዜጎች ጉዳይ ለኢፌዴሪ መንግስት የራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል። ከዚሁ ከመካከለኛው ምስራቅ ኢትዮጵያውያን ህገወጥ ዝውውር ጋር ተያይዞ በ2006 ዓ/ም ከሳኡዲ አረቢያ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በህገወጥነት ይኖሩ የነበሩ ዜጎች መባረር ያስከተለው የሰብአዊ መብት ጥሰትና እንግልት ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ በ2007 ዓ/ም ወደ አወሮፓ ለመሻገር ሊቢያ ሰፍረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አይ ኤስ አይ ኤስ በተሰኘው አሸባሪ ቡድን የተፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ያስቻለ አጋጣሚን ፈጥሯል።
በዚህ መነሻነት የኢፌዴሪ መንግስት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ሃገር አቀፍ ንቅናቄ አውጇል። ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የክልል መንግስታትን፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስንና ሌሎች የፌደራልና የክልል መንግስታት አካላትን ያካተተ ምክር ቤት ተቋቁሟል።
በመሰረቱ፤ የሰዎችን እንቅሰቀሴ መገደብ አይቻልም። ሰዎች በተለያየ ምክንያት መኖሪያቸውን በቋሚነትም ይሁን ለተወሰነ ጊዜ ተወላጅ ከሆኑበት ሃገር የሚቀይሩበትን ሁኔታ መገደብ የማይቻል ነው። የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ሊገሰስ የማይችል ሰብአዊ መብት ነውና። በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስት ይህ ህገመንግስታዊ መብት እንደተከበረ፣ ዜጎች ለሰብአዊ መብት ጥሰትና እንግልት ሳይጋለጡ በውጭ ሃገር ለስራ ሊሰማሩ የሚችሉበትን አዋጅ አዘጋጅቷል። ይህ አዋጅ ዜጎች በውጭ ሃገራት ሰብአዊ መብቶቻቸውና ክብራቸው ሳይጣስ የሚሰሩበትን ሁኔታ ከማመቻቸት በተጨማሪ መንግስት ዜጎቹ ያሉበትን ሁኔታ መከታተል ያስችለዋል።
የኢፌዴሪ መንግስት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ህዝባዊ ንቅናቄ ባካሄደባቸው ያለፉ ሶስት አራት ዓመታት በተወሰ ደረጃ በችግሩ አስከፊነት ዙሪያ ግንዛቤ መፈጠር ቢቻልም፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የችግሩን ሰፋት ያህል መከላከል አልተቻለም። የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት አዋጁም እስካሁን ስራ ላይ አለመዋሉ ስራ ላይ ቢውል ሊያቃልላቸው ይችሉ የነበሩ ችግሮች አሁንም ጎልተው እየታዩ ይገኛኛሉ።
ያም ሆነ ይህ፤ በቅርቡ የአፍሪካና የአወሮፓ ህብረት 5ኛ የጋራ ጉባኤ ላይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ጉዳይ በኢትዮጵያ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከራርሟል።
ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት መንስኤ አለው። የኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካውያን ስደት ዋነኛ መንስኤ ኢኮኖሚያዊ ችግር ነው፤ ስራ አጥነት፣ የተሻለ ህይወት የመኖር ፍላጎት ወዘተ። በመሆኑም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደትን አሁን የሚገኝበትን አስከፊ ሁኔታ ለማቃለል የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ አተኩሮ መስራት ምትክ የሌለው አማራጭ ነው። በተለይ የህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰደት ተጋላጭ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ሰሞኑን በኮት ዲቮዋር አቢጃን የተካሄደው የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤም ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቷል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ፖሊሲ ነድፋ በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ ከጀመረች አስራ ሁለት ዓመታትን አስቆጥራለች። በ1998 ዓ/ም ተነድፎ ስራ ላይ በዋለው የወጣቶች ተጠቃሚነት ፓኬጅ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች በሰራ ፈጠራ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማደረግ ተችሏል። ይህም ቢሆን ግን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለም። በተለይ ከሞያና ቴክኒክ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ እየተመረቁ የሚወጡ ወጣቶችና ከገጠር ወደከተማ የሚፈልሱ የወጣቶች ሰራ አጥነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ሁኔታ የፈጠረው ተስፋ መቁረጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ተቃውሞ የቀሰቀሰበት ሁኔታ አጋጥሟል። ይህ ተቃውሞ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና ለሃገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች ጭምር ትርምስ መፍጠር የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር። በተለይ በ2008 ዓ/ም በሃገሪቱ አጋጥሞ የነበረው አውዳሚ ሁከት የዚህ ውጤት ነበር።
የኢፌዴሪ መንግስት በ2009 ዓ/ም ይህን ቀውስ መነሻ በማደረግ ልዩ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል፤ የ10 ቢሊየን ብር ተዘዋወሪ ፈንድ በመመደብ። ይህን ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል የወጣቶች የልማት ተሳተፎና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ላይ የማሻሻያ ክለሳ ተደርጓል። የፈንዱ አጠቃቀም መመሪያ ተዘጋጅቷል። በዚህ መሰረት ከባለፈው ዓመት ማገባደጃ ጀምሮ የፌደራል መንግስት የመደበው ተዘዋወሪ ፈንድና ክልሎች ለወጣጦች የስራ ፈጠራ የመደቡትን ፈንድ አጣምሮ በመጠቀም የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል። ይህ የስራ ፈጠራ ፕሮግራም እስካሁን በታሰበው ልክ ስኬታማ ባይሆንም ስራ አጥነትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ ድርሻ የኖረዋል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት በተለይ ከስደት ጋር አያይዘው ልዩ ትኩረት የሰጡት የወጣቶች የስራ ፈጠራ ጉዳይ በኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተገባራዊ እንቅስቃሴ ከተጀመረ መከራረሙን ያሳያሉ። ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረትና በአውሮፓ ህብረት ትኩረት ተሰጥቶተ አቋም የተያዘበት መሆኑ የኢትዮጵያን የስራ ፈጠራ ጥረት ይደግፈዋል ተብሎ ይታመናል።
በአጠቃላይ፤ የወጣቶች የስራ እጥነት ችግር ወጣቶቹ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር በአፍሪካም በአውሮፓም የሰላምና መረጋጋት፣ የፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት መሆኑ ተረጋግጧል። ወደአውሮፓ በገፍ በሚሰደዱ አፍሪካውያንና የመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት ስደተኞች ምክንያት በአውሮፓ የዘረኝነት ዓመለካካት እያንሰራራ መጥቷል። ይህ ደግሞ ካሀገራቱም አልፎ ለዓለም አቀፍ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ሊሆን ይችላል። እናም የወጣቶች የስራ አጥነትን መከላከል የዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋት ጉዳይ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ርብርብ ሊደረግበት ይገባል።