Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝብና ቤት ቆጠራ ለየኢኮኖሚ ሽግግር

0 840

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብና ቤት ቆጠራ ለየኢኮኖሚ ሽግግር

 

ስሜነህ

 

በየካቲት ወር መጀመሪያ ለሚካሄደው አራተኛ ዙር አገር አቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች ሁሉ ስለመጠናቀቃቸው መረጃዎች እያመለከቱ ነው። ለቆጠራው 150ሺ የቆጠራ ቦታ ካርታ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ 180ሺ ታብሌት ኮምፒዩተሮች ተገዝተው ስለመግባታቸው የሚያወሱና የማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣንን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች ከየካቲት 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አስር ቀናት ለሚካሄደው ቆጠራ የተለያዩ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅት በቆጠራው የሚሳተፉ 190ሺ ሰዎች ምልመላ የተከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይ በአምስት ቋንቋ የተዘጋጁ መጠይቆችን ፅንሰ ሃሳብ በአግባቡ እንዲገነዘቡ ተደርጓል። የዘንድሮው ቆጠራ ከዚህ ቀደም ባልነበረ መልኩ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ እገዛ የሚደረግ ሲሆን፤ 180ሺ ታብሌት ኮምፒዩተሮችና 126ሺ የኃይል ማጠራቀሚያ (ፓዎር ባንክ) ግዥ ተፈፅሟል። ለዚህም የተግባር ስልጠና እንደሚሰጥ የጠቆሙት የኤጀንሲው መረጃዎች ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ የሚሰጠውን የተግባር ፈተና ያለፉት ቆጠራ ስለሚመደቡ በስልጠናው ላይ ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ ባለሙያዎች ሊካተቱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

 

በአሁኑ ሰአት የቆጠራ ቦታ ካርታ ተዘጋጅቷል፤ የቆጠራ ቦታው ግልጽ እንዲሆን የማድረጉን ሥራ በአግባቡ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የመቀየር ሥራ ተከናውኗል። በተጨማሪም በቆጠራ ወቅት መሰብሰብ የሚገባቸውን መረጃዎችም በጥንቃቄ መወሰዳቸው ተጠቁሟል።  እንደመግቢያ ስለአራተኛው ዙር የህዝብና ቤት ቆጠራ ይህን እናንሳ እንጂ የዚህ ተረክ ዋነኛ አጀንዳ የህዝብና ቤት ቆጠራን ፋይዳ መመልከት ነው።

 

በ1986 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት የከተሞች ቁጥር ከ925 በላይ (2000 ነዋሪዎች ያላቸውን ከተሞች ጨምሮ) የደረሱ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች የከተሞቹ እድገት ያልተመጣጠነ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ ከ925ቱ ከተሞች ከ100ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሏቸው 12 ከተሞች ብቻ መሆናቸው እና የዋና ከተማዋ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር በህዝብ ብዛት ቀጥላ ከምትገኘው ከድሬደዋ ከተማ በ14 እጅ የሚበልጥ መሆኑ ልዩነቱ እጅግ የጎላ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ያልተመጣጠነ የከተሞች እድገት በአንዳዶቹ ከተሞች በተለይም የመሠረተ ልማት እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ሽፋን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የተደረገውን የቆጠራ ውጤት መነሻ በማድረግ የተለያዩ የከተማ ለከተማ እና የከተማ ገጠር ትስስር ስትራቴጂዎችን በማውጣት ያለውን ያልተመጣጠነ አከታተም በማሻሻል በከተሞች መልካም አስተዳደር ፓኬጅ ዉስጥ ራሱን የቻለ የከተማ ለከተማ እና የከተማ ገጠር ትስስር ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

 

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአከታተም ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆኑ አገሮች የከተማ ነዋሪው ሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የክትመት ምጣኔአቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም /2007 እ.ኤ.አ/  በኢትዮጵያ ማዕከላዊ  ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የተደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት እንደሚያመለክተው ደግሞ በአገራችን የከተማ ነዋሪው ሕዝብ ብዛት 11.9 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከጠቅላላው የሃገሪቱ ህዝብ 16.1 በመቶውን ብቻ የያዘ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ድርሻ አሁን ካለው ከአፍሪካ አማካኝ 37 በመቶ እንዲሁም ከታዳጊ ሃገራት አማካኝ 41 በመቶ ጋር ስናነጻጽረው ምን ያህል ዝቅተኛ እንደሆነና የክትመት ሂደቱም ምን ያህል ዘገምተኛና ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ከ1958 ጀምሮ ያለውን የሃገራችን የከተማ ህዝብ አማካይ የዕድገት ምጣኔ  ስንመለከት ወደ 4.49% የሚደርስ (ከ3.54 እስከ 6.11) ሲሆን ይህም የዕድገት ምጣኔ አሐዝም ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገሮች አማካይ የከተሞች የዕድገት ምጣኔ (ማለትም 4.58%) ጋር የተቀራረበ ሲሆን ይህም በዓለም ከፍተኛውን የከተማ ነዋሪ እድገት ምጣኔ የሚይዝ መሆኑን እንረዳለን፡፡

 

በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር በሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ በአራት እጥፍ በማደግ በ1958 ከነበረበት 1.5 ሚሊዮን በ1986 ወደ 7.3 ሚሊዮን አድጐ ነበር፡፡ ከዚያም በአስራ ሦስት ዓመታት 63 በመቶ በማደግ በ1999 ዓ.ም 11.9 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በዚህ ሂደትም የከተማ ነዋሪው አማካይ የእድገት ምጣኔ ከ4 በመቶ በዓመት የማያንስ እንደሆነ ያሳያል፡፡ የሀገራችን ከተሞች የክትመት ደረጃቸዉ ዝቅተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ለየት ያሉ ገጽታዎች የሚታወቁ  እንደነበር ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡  

 

አንደኛው የከተሞቻችን ገጽታ በተፈጥሮ እድገት የሚያድገውን ህዝባቸውን መሸከም ሳይችሉ ባሉበት በዚህ የክትመት ሂደታቸው ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፈጣንና የማያቋርጥ ፍልሰት ደግሞ በከፋ ሁኔታ ችግሮች እንዲበራከቱና የባሰውን እንዲወሳሰቡ እያደረገው ይገኛል፡፡ ለዚህ ፍልሰት ዋነኞቹ ምክንያቶችም የገጠሩ ግፊት ማለትም የገጠሩ መሬት ተጨማሪ ህዝብ የመሸከም አቅሙ ፈተና ውስጥ በመግባቱና የከተሞች ስበት ማለትም በአንጻራዊነት በከተማ ጥሩና የተሻለ ኑሮ ይኖራል የሚሉ እሳቤዎችን (ምንም እንኳን እውነታው ሌላ ቢሆንም) መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ገጽታ ደግሞ አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ የለውጥ ሂደትን (Globalization) እና የዘመናዊ መረጃ መስፋፋትን (ICT) መሠረት በማድረግ የገጠር አካባቢዎች ወደ አዳዲስ ከተማነት የመለወጣቸው ዕድል ሰፊ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡

 

ከዚህም በተጨማሪ ያለው የተፈጥሮ የከተማ ህዝብ ዕድገትና የገጠር ከተማ ፍልሰቱም ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል መሆኑ (ምንም እንኳን ሀገራችን በዋናነት ግብርና መር ስትራቴጂን የምትከተል ብትሆንም ይህንን ክስተት በአጭር ጊዜ መቀልበስ ስለማይቻል) እና የዓለምአቀፍ የለውጥ ሂደት ተወዳዳሪነትም እንዲሁም ቀጣይ በመሆኑ ከተሞቻችን በፍጥነት የሚያድጉና ፈተናዎችም እንዲሁ የሚበራከቱና የሚወሳሰቡ መሆናቸው ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡  

 

በዚህ ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከተሞቻችን አሁን እየተገመተ ባለው አማካኝ ዓመታዊ ምጣኔ ዕድገት እ.ኤ.አ በ2020  የሃገራችን የክትመት ደረጃ 30 በመቶ የሚደርስ ሲሆን አሁን ያለው የከተሞች ተጨባጭ የዕድገት እንቅስቃሴ  (አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ)  ይህንን መሸከም የሚያስችል ስለማይሆን ወደ ባሰ ውስብስብ ችግርና  ከፍተኛ ወደ ሆነ ቀውስ የሚወስድ መሆኑን አስቀድሞ በመገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ፣ ለዚህም አሁን በከተሞች የሚታዩትንና ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ችግሮች ለመቅረፍና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሃገራዊ የገጠርና  የከተማ ልማት ዘርፍ መሪ የመካከለኛ ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝብና ቤት ቆጠራ መሰረታዊና የነገሮች ሁሉ መነሻ ይሆናል።

 

መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና አስትራቴጅዎች ተግባራዊ በማድረግ ልማታዊ መንግስት ለመገንባትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም ተጠያቂነትና ግልፅነት ያለው የመንግስት አሰራር ለመፍጠር ጥራቱ የተጠበቀ ትምህርት አግኝቶ ያደገና ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል እቅድና ፖሊሲ ማውጣት የሚችለው የህዝብና ቤት ቆጠራን ውጤት ተንተርሶ ብቻ ነው።

 

በንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት፤ በንግድ፤ በመሰረተ ልማት፤ በትራንስፖርት፤ በስራ እድል ፈጠራ፤ በብድር አገልግሎት ወዘተ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ የሚያስችለውም ፕሮግራምና እቅድ የሚተለመው የህዝብና ቤት ቆጠራን ውጤት ተንተርሶ ነው።   

 

የከተማ ገጠር እና የከተማ ለከተማ ትስስሩን በማጎልበት የርስ በርስ መመጋገብ እንዲኖር በማድረግ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የኢኮኖሚውን እድገት እውን ለማድረግ የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ግድ የሚል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የከተማ ገጠር ትስስር አጠንክሮ ከማስኬድ በተጨማሪ  የከተሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት የፈጠራና የምርምር ማዕከል እንዲሆኑ ለማድረግ የሚቻለው የከተሞች ሁለንተናዊ እድገት በከተማ ፕላን እንዲመራ ማድረግ  ሲቻል ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መሰረታዊ መነሻ ነው።   

 

በከተሞች መልሶ ማልማትና ማሻሻል ስራ በማካሔድ ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ብቃት ያለው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት መፍጠርና ከተሞች የተደራጀ ዘመናዊ ወይም ባህላዊ የመሬትና መሬት ነክ ሃብቶች መረጃ ሥርዓት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚቻለውም በዚሁ መንገድ ብቻ ነው።   

 

ከብዙ በጥቂቱ እነዚህን እና ከላይ የተመለከቱ አብነቶች አነሳን እንጂ ጉዳዩ ብዙ ነው። ለማናቸውም ግን ባሳለፍናቸው 26 አመታት ለተመዘገቡ ውጤቶች መንገዱ የህዝብና ቤት ቆጠራን መነሻ ያደረጉት ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች እንደሆኑት ሁሉ በየትኛውም ዘርፍ ውጤታማ ሆነን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣት የምንችለው በዚሁ እና የህዝብና ቤት ቆጠራን መነሻ ባደረጉ እቅዶች እና ፕሮግራሞች መሆኑን በመገንዘብ ለቆጠራው ስኬታማነት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ልናደርግ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy