Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች እየተሞሉ ነው!

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች እየተሞሉ ነው!

                                                          ታዬ ከበደ

ገዥው ፓርቲና መንግስት የጀመሩት የጥልቅ ተሃድሶ ስራ በተለይ በመልካም አስተዳደር በኩል ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን እየሞሉ ይገኛሉ። የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶችና አጋር ፓርቲዎች ከህዝቡ ጋር በመሆን በጥልቅ ተሃድሶው ራሳቸውን እየፈተሹ ለመልካም አስተዳደር ማነቆ የሆኑ ጉዳዩችን እየፈቱና ምላሽ እየሰጡ ናቸው።

በጥልቅ ተሃድሶው የመልካም አስተዳደር ችግሮች የመፈታታቸው ምስጢር ህዝቡ የያዘው አቋምና ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ፐብሊክ ሰርቫንቱም ይሁን ህዝቡ የሚሰማቸውንና ለመልካም አስተዳደር እመርታ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዩችን እየለዩ ፊት ለፊት ገልፀዋቸዋል። በዚህም የአገራችን ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ እየተካሄዱ ባሉት የውይይትና የግምገማ መድረኮች የመንግስትን ባለስልጣኖች ከሃላፊነታቸው አንስቷል።

ከዚህ አኳያ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ህዝቡ በግምገማው ያካሄደውን ሹም ሽር በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ይህም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመታደስ ያሳዩት ቁርጠኝነት ውጤት እያመጣ እንጂ፣ አንዳንድ ፅንፈኞች እንደሚሉት ውጤት አልባ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ጥልቅ ተሃድሶው ዋጋ ያለውና የሀገሪቱን ችግሮች በመግባባት እየፈታ ነው።

እርግጥ በየትኛውም ዴክራሲያዊ አገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። ምንም እንኳን በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ ቢሆንም፤ እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ አገር ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳንና ጉድለቶች የሉብንም ብሎ ለመናገር አይቻልም።

መንግስትና እርሱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው በሚወስዷቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች በመጠኑም ቢሆን እየቀረፉ ቢሆኑም፤ የሚፈለገው ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ ተገኝቷል ማለት አይቻልም። እንዲያውም አስተሳሰቦቹ እየገነገኑ ጫፍ ላይ እየወጡ ይመስላሉ።  

በአመዛኙ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ የመንግስት ስራ አስፈፃሚን ብሎም ህዝብን በተሟላ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም። በሰጪም ይሁን በተቀባይ መካከል ያለው አስተሳሰብ አንድና ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል።

ይህ የሆነውም ካለፉት ስርዓቶች ይዘናቸው የመጣናቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ቅሪት አስተሳሰቦች ብሎም ልማቱ የፈጠራቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አስተዋፅኦ ያደረጉ ይመስለኛል።

ሲቪል ሰርቪሱ ምንም እንኳን በሀገራችን ውስጥ ለተገኘው ልማት የበኩሉን ድርሻ ቢያበረክትም ከዚህ ነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ ውጪ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ስልጣን የህዝብ ማገልገያ ሳይሆን የራስ መገልገያ ሊሆን ችሏል።

ይህን አመለካከት ለመለወጥ ደግሞ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የአስፈፃሚነት ስራን የሚከውኑት የሲቪል ሰርቪሱ አካላት በአመለካከት ብሎም በአደረጃጀት ለውጦች ውስጥ ማለፍ የግድ ይላቸዋል። የእነርሱ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ በማለፋቸውም የተጠያቂነት መንፈስ ተፈጥሯል፤ እየተፈጠረም ነው። በዚህም ውጤቶች ተገኝተዋል።

በተሃድሶው ውጤትም መላው የአገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በበጎ ገፅታ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ ያደረጋት ይመስለኛል። የምትከተለው በሳል የዲፕሎማሲ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች የሰላም ጠባቂ፣ መጠጊያና መጠለያ ሆናለች።

በጥልቅ ተሃድሶው ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየቀረፈ ነው። በእኛ አገር ዕውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረት፤ ህዝቡ የፖለቲካ መሪዎቹንና ተወካዩቹን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማል፤ ይሽራል።

ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማኝነት በቀጥታ የስልጣን ባለቤት የሆነበት ይህ አሰራር በስርዓቱ ውሰጥ ወሳኝ ሚና ቢኖረውም፤ በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት ግን መኖራቸው አይቀርም። በዚህ የአሰራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ስራ አስፈፃሚው ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው።

እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅም፤ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ።

ይሁን እንጂ የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መረዳት ይገባል። በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ ስራ አስፈፃሚውና ሲቪል ሰርቪሱ ማንም እንዳሻው የሚዘውራቸው አካላት አለመሆናቸውን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል።

ይህ ደግሞ የአንድን አካል ፍላጎት ለማሟላት ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን፤ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታው አሁን ካለበት ጅምር መንገድ እየተጠናከረና ስር እንዲሰድ ካለ መሰረታዊ ፍላጎት የሚመነጭ ነው።

እናም ህዝቡና የህዝቡ ተወካዩች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ተቃዋሚዎች ነገሮችን በሰከነ መንገድ በማየት መቀበል ያለባቸው ይመስለኛል።

እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው የህዝቡ ሉዓላዊነት መሳሪያዎች፣ አገልጋዩችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች በመሆን ለዴሞክራሲው መጎልበት የነኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው የሲቪል ሰርቪስ ስርዓቱ የተጠቃሚው መብትና ጥቅም እንዳየሸራረፍ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በርካታ ተግባባራትን አከናውኗል። ይህ ተግባርም መንግስት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተኪያ የሌለው ድርጊት መሆኑን እንደሚያምንና በቁርጠኝነት ለመተግበርም በሃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሱን የሚያመላክት ይመስለኛል።

ከመልካም አስተዳደር አንፃር የዳኝነት ስርዓቱም ቢሆን ከዚህ በተለየ መንገድ የሚታይ አይመስለኝም። ህዝቡ በተወካዩቹ አማካኝነት ያፀደቀውን ህገ-መንግስትና ይወክሉኛል ባላቸው አካላት አማካኝነት የሚወጡ ህጎችን በትክክል መተርጎሙ፣ በዚህ መሰረትም አቅም በፈቀደ መጠን ለባለ ጉዳዩ ፈጣንና ትክክለኛ ፍትህን ያለ አንዳች አድልኦ ማስፈፀሙ ለዴሞክራሲው መጠናከር የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። እነዚህ ሃቆች በአሁኑ ወቅት በአገራችን የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች እየተሞሉ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy