Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቅራኔ ምንጮችን በመዝጋት ላይ ያለ ሥርዓት

0 336

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቅራኔ ምንጮችን በመዝጋት ላይ ያለ ሥርዓት

                                                     ታዬ ከበደ

ለረዥም ዘመናት በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የኖረችው ኢትዮጵያ በዋነኛነት ለሰላሟ መጥፋት ምክንያት የነበሩትን የቅራኔ ምንጮች መዝጋት ችላለች። በዚህም የብዙ ብሄረሰቦች መኖሪያ የሆነችው አገራችን ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ሥርዓት በመመስረቷ ህዝቦች የስልጣናቸው ባለቤት እንዲሆኑ አድርጋለች።

ዘላቂ ሰላም በማስፈንም ዋስትና ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባትና ድህነትንና ኋላቀርነት በማስወገድ ፈጣን ልማት ለማስመዝገብ የቻለች አገር ሆናለች። ያልተማከለ አስተዳደርን የምትከተል በመሆኗም ሕዝቦች እንዲበታተኑ ሳይሆን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዓላማ ይዘው ጠንካራ አገር የመገንባት አቅም በመፈጠር ረገድም ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ የሚችሉበትን ምቹ ምህዳር እውን አድርጋለች።

እነዚህ ሃቆች መተግበር የቻሉት ሥርዓተቱ የቅራኔ ምንጮችን በመዝጋቱ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ይሁን እንጂ፤ የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ አንዳንድ ወገኖች ሰላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም። አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ስራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኞችና ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ዕድገትና አንድነት ሰላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም። ይሁንና ሃቁን ይበልጥ ገላልጦ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ ገጥመው ውጤት እያስመዘገቡ ያሉት በዚሁ ሥርዓት ውስጥ ነው።

በስርዓቱ ውስጥ ዜጎች በመንግሥት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል። ከድህነት አዙሪት ተላቀው ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትም ተሸጋግረዋል። ውጤቱን ከማጣጣም ባለፈ የህዳሴያቸውን ፈር ቀዳጅ መንገድ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ስርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ፣ ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በነፃነት የመግለፅ መብቶቻቸን እንዲጎናፀፉ አድርጓቸዋል። ርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ በመሆኑ ይህ ውጤት ከተገኘ 26 ዓመታትን ተሻግረዋል።

በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አይመስለኝም—የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ ከሆኑት ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠው እንጂ። ያም ሆኖ ግን እነርሱ ያሻቸውን ቢሉም የሆነው ሃቅ አሁን ከ26 ዓመት በኋላ ያለው ዓለም ያደነቀው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ነው።

ለነገሩ የሀገራችን ህዘቦች የሚከተሉት የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን የመስኩ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

ከዚህ ዕውነታ የሚነሳው የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ- መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው።

ይህ የሀገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለዚህም ይመስለኛል— ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችብን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።

ይህ ውሳኔያቸውም ለዛሬው እነርሱነታቸው ያበቃቸው ከመሆኑም በላይ፤ የፌዴራል ስርዓቱ አንዳንድ ወገኖችና ፅንፈኞች ሃቁን ካለመገንዘብ አሊያም ለመረዳት ካለመፈለግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት እንደሚሉት ዓይነት በድንቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አለመሆኑንም አሳይተዋል። ምክንያቱም ሥርዓቱ በህዝቦች ፈቃድ ተረጋግጦ አንድነታቸው በጠንካራ መሰረት ላይ ስለተገነባ ነው።

ለነገሩ አንዳንዶቹ ይህን ሃቅ እያዩ እንኳን በማንኛው በማደግ ላይ በሚገኝ ሀገር ውሰጥ እንደሚፈጠረው በግጦሽ ቦታና በውኃ ምክንያት በአንዳንድ የሀገራችን ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ነባራዊ ክሰተቶችን እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪዎች ከአንዳንድ አካባቢዎች ተባረሩ በሚሉ የፌዴራል ሥርዓቱ በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት ከሽፏል እስከማለት መድረሳቸው የቅርብ ጊዜያችን ትውስታ ነው።

እርግጥ ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ እንዲሁም ነገ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ይመስለኛል። ዋነኛው ጉዳይ ግጭቱ የሀገርንና የህዝብን ሰላማዊ ህይወት የማይበርዝ መሆኑን መገንዘቡ ላይ ነው። በአፋጣኝም መፍትሔ መሰጠቱ ላይ ነው።

ከዚህ አኳያ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

ይሁንና ያለፉት ስርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሚቀየሩ አይደሉም። ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን የሚጠይቁ ናቸው። ታዲያ መንግስት ይህን ዕውን ለማድረግ የህዝቦች አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ ተመርኩዞ ተግባሩን በብቃት እየተወጣ ነው።

ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው ፌዴራላዊ ሥርዓት ከ26 ዓመታት በላይ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በአስተማማኝና በሰከነ ሁኔታ በመፍታት ተሞክሮን አዳብሯል። አንዱ ክልል ከሌላው ጋር በወሰን መካለል ሳቢያ የሚፈጥራቸውን ችግሮች እየፈታ መጥቷል። በቅርቡም በኦሮሚያና በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል፣ በአማራና በትግራይ…ወዘተ. ክልሎች መካከል የነበሩ የወሰን መካለል ችግሮችን መፍታት መቻሉን መጥቀስ ይቻላል። ሌሎች ያልተፈቱ ችግሮች ካሉም ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈቱ ናቸው። እነዚህ እውነታዎች የሚያረጋግጡልን ነገር ቢኖር ሥርዓቱ በሰከነ መንገድ የቅራኔ ምንጮችንና ቅራኔዎችን እየፈታ በመምጣት አገራችንን ወደ ህዳሴ መንገዷ እያንደረደራት መሆኑን ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy