Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን፤ ፌዴራሊዝም እና ትሩፋቶቹ

0 402

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን፤ ፌዴራሊዝም እና ትሩፋቶቹ

                                                             መዝገቡ ዋኘው

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት የጸደቀበት ሕዳር 29 ቀን “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን” ተብሎ መከበር ከጀመረበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ እያንዳንዱ ክልል በዓሉን የማስተናገድ እድል አግኝቶአል፡፡

ዘንድሮ በሕገ መንግስታችን የደመቀ ሕብረ ብሔራዊነታችን ለሕዳሴያችን በሚል መሪ ኃሳብ በአፋር ክልል፣ ሰመራ ከተማ የተከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እንደቀደሙት አመታት ሁሉ በታላቅ ድምቀት፣ በፍቅርና ሀገራዊ አንድነትን ይበልጥ ባጎለበተ መልኩ ተከብሯል።

ይህ አመታዊ በአል የየብሔር ብሔረሰቦቹ ተወካዮች የሚገናኙበት፣ ባሕላቸውን፣ እምነታቸውን በጋራ የሚጋሩበት ታላቅ መድረክ ነው፡፡ ጥንትም የነበረውን ሀገራዊ አንድነት ፍቅር መከባበርና መቻቻል በበለጠ መሰረት ላይ የገነባ፣ ያሳደገና ለዘመናት የነበረውን በረዥም የታሪክ ሂደት የተቆራኘ ሕብረትና አንድነት ዛሬ ላይ ሙሉ ነጻነቱ በተረጋገጠበት፤ መብቱ በተከበረበት መንፈስ በጋራ ሲያከብሩት በአሉን ልዩ ያደርገዋል፡፡

ይሄ ደማቅና ሁሉ-አቀፍ በአል በሂደት በአለም ቅርስነት እንደሚመዘገብ ተስፋ ይደረጋል፡፡ በአሉ ከፍተኛ የአለም አቀፍ ቱሪስት መስህብ በመሆንም በየዙሩ ለሚከበርበት ክልልም ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ አንፀቃር አዘጋጆቹ እለቱን በብሔራዊ ደረጃ ከመዘከርና ከማክበር ባሻገርም እንዴት ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል በጥንቃቄ ማስላት ይጠበቅባቸዋል፡፡

እለቱ በኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ዘንድ አንድነትና መፈቃቀርን በላቀ ደረጃ ከማጎልበት ባሻገር በእኩልነትና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት እንዲፈጠር፤ የበለጠ መቀራረብ እንዲኖር፤ መተዋወቁ እየጠነከረ እንዲሄድ የማይተካ ሚና ተጫውቶአል፤ እየተጫወተም ይገኛል፡፡

በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖራቸው ያለና የነበረ፣ ሕብርነቱም የውበትም መገለጫ ነው፡፡ ትልቁ ነገር የሁሉም የእኩልነት መብታቸው ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸው በተግባር ላይ መዋሉ ነው የበለጠ ሀገራዊ አንድነታቸውን የሚያጎለብተው፤ በዜግነታቸውም የሚኮሩና የሚመኩ የሚያደርጋቸው፡፡ ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ ነው እየተሰራ ያለው፡፡

ከእኛም በቁጥር ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ድረስ የሚደርሱና ከዛም በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏቸው ሀገሮች በአለማችን አሉ፡፡ ተከባብረው፣ ተቻችለው፣ በፍቅር፣ በሕብረትና በአንድነት ሁነው ሀገራቸውን ወደ ታላቅነት አሳድገዋል፡፡ ፌደራሊዝሙ የእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰቦች ባሕል፣ ቋንቋ፣ እምነት ነጻነት እንዲከበር በራሳቸው እንዲተዳደሩና እንዲዳኙ ያስቻለ ሲሆን በጋራ ደግሞ ለጋራ ሀገራቸው እንዲሰሩና አካባቢያቸውን እንዲያለሙ የሚያደርግ ነው፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ለሀገር ሰላምና ልማታዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በግልጽ በሕገ መንግስቱ የተከበረው መብትና ነጻነት በአግባቡ ሳይከበር ሲቀርና በተሳሳተ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚሞክሩ ክፍሎች ሲፈጠሩ ግጭቶች፣ ሁከቶችና አለመግባባቶች ይከሰታሉ፡፡ የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች መብቶች በተከበሩበት ሁኔታ ውስጥ ግን ሁሉም በጋራ ለብሔራዊ አንድነታቸው ያለለዩነት ይቆማሉ፤ ሀገራቸውን ያለማሉ፤ ይጠብቃሉ፡፡

በዘንድሮውም በአፋር ክልል የሰመራው የብሔር ብሔረሰቦች በአል ላይ ለመገኘት ከመላው ኢትዮጵያ ወደስፋራው ያቀኑት የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች የበለጠ ሌላውን የሀገራቸውን ክልልና ወገናቸውን ባሕሉን እምነቱን ኑሮውን ለማወቅ ትልቅ አጋጣሚ አግኝተዋል፡፡ ምክንያቱም ከጥንት ጀምሮ አንዱ ቦታ ላይ በአል ሲከበር ከሁሉም ክልል ተውጣጥቶ በመሄድ በጋራ በአል የሚያከብሩበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትም ለዚህ ነው፤ ሰፊ የመግባቢያና የመተዋወቂያ መድረክ ነውና፡፡

በሰመራው የብሔር ብሔረሰቦች በአል ከሁሉም ክልሎች ተውጣጥተው በበዓሉ  የተገኙት ተወካዮች የአገራችንን ሰላም ለመጠበቅ፤ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን ለማጠናከር ቃላቸውን አድሰዋል፡፡ በጋራ የሀገራቸውን ልማትና እድገት ለማስቀጠል የበለጠም በያሉበት ሁነው ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የበአሉ በተዘዋዋሪነት በየክልሎቹ መከበር አካባቢውን ከማልማትና ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

በአፋርዋ የሰመራ ከተማ ከተሰራው ዘመናዊ ስታዲየም በተጨማሪ አለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ተሰርቶ በይፋ ተመርቋል፡፡ ይህ ከዚህ በፊት ለዘመናት ያልነበረ እጅግ ከፍተኛ ለውጥና እድገት ነው፡፡

የዛኑም ያህል ከተማዋ አድጋለች፡፡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማፋጠንና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርም ረገድ የበአሉ በየአመቱ መከበር ዓይነተኛ ሚና ተጫውቶአል፡፡ በጋምቤላ፣ ቤንሻነጉል ጉሙዝ፣ ሶማሌ ክልሎች፤ እንዲሁም በድሬደዋ ራስ ገዝ ቀደም ሲሉ በመሰረተ ልማትና በከተሞች መስፋፋት ረገድ የተመዘገቡትን ከፍተኛ ውጤቶች ማየት ይቻላል፡፡

ከብሔር ብሔረሰቦች በአል መከበር ጎን ለጎን ሀገሪትዋ በልማት በኢኮኖሚ እድገት ከዚህ ቀደም ባልነበረ ሁኔታ ወደላቀ ምእራፍ እየሸጋገረች የምትገኝ በመሆኑ፤ ይህንን ልማትና እድገት ጠብቆ የማስቀጠሉ ዋነኛው ኃላፊነት የሁሉም ክልል ሕዝቦች፣ በአጠቃላይም የመላው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በውስጥ የሚነሱ ማንኛውም አይነት ችግሮችን ሕዝቡ ከመንግስት ጎን ሁኖ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርሕ በቀጥታ እንዲፈቱ በማድረግ የኢትዮጵያን ውድቀት ሌት ከቀን ለሚናፍቁ የውጭ ኃይሎች በር በመዝጋት ሊከፋፍሉት የሚጥሩትንም በማሳፈር ሀገሩን ሰላሙን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ኢትዮጵያ ባስመዘገበቻቸው ታላላቅ የኢኮኖሚ ድሎች የተበሳጩ ኃይሎች በተለያዩ የሀገሪቱ ማእዘኖች ሁከትና ግጭት ለመቀስቀስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድበው እንደሚሰሩ ይታወቃል፡፡ የዚህን ተጨባጭ ድርጊትም ውጤቶች ባለፉት ግዜያት ሕዝቡ ተመልክቶአል፡፡

በውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን ስርአት ባለው መንገድ መፍታት እየተቻለ ሆን ተብሎ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት የማጣላት ስራዎች በገሀድ ታይተዋል፡፡ ትናንሽ የግለሰቦች አለመግባባቶችን ጭምር ወደጎሳና ዘር ግጭት እንዲያመሩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የማሻከር አስከፊ ድርጊቶች በተጨባጭ ተከስተዋል፡፡ እንደዚህ አይነቱ ድርጊትና ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዚህ መጠንና ደረጃ ቀድሞ ታይቶ አይታወቅም፡፡

ሕዝብ ለሕዝብ ተከባብሮ፣ ተዋዶ፣ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፣ ተቻችሎ፣ በደጉም በሀዘኑም ግዜ በአብሮነቱ ጸንቶ የጋራ ሕይወት የሚኖር ሕዝብ ነው የኢትዮጵያ ሕዘብ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦችም የፍቅር የአብሮነት የመቻቻል ተምሳሌት እንጂ የጠብና የግጭት መንስኤ አይደሉም፡፡ የዚህ ስራ ባለቤቶችና መሀንዲሶች ከውጭ በሚዘራላቸው ገንዘብ ያበዱ የግብጽና የኤርትራ ተላላኪዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡

በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ሕዝቡ የችግሩን መንስኤና ምንነት ለይቶ ተረድቶታል፡፡ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ማጋጨት ማናቆር ቂም እንዲይዝ ማድረግና መስራት በትልቁ የሚጎዳው ሀገርንና ሕዝብን ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን እኩይ አስተሳሰብ ለመለወጥ መስራት በየደረጃውም የድርጊቱን ተዋናዮች ማጋለጥ ሊጭሩ የሚጥሩትን እሳት ማጥፋት ከሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ 12ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአልን በማስመልከት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመገንባት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ብለው ለጀመሩት የጋራ ፕሮጀክት ስኬታማ ተግባራትን በማከናወን ረጅም ርቀት ተጉዘናል ሲሉ መናገራቸው  የተጋረጡ መሰናክሎችን በጋራና በሕብረት በማለፍ የሀገሪቱን አንድነት ሰላምና ልማት ጠብቆ የተደረሰበትን የተሻለ ደረጃ አመላካች ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመገንባት የገቡት ቃል በድምር አፈጻጸም ሲታይ ስኬታማ ነው፡፡ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፎች የተመዘገቡት ለውጦችና የተገኙት ውጤቶች ለአገሪቷ ሕዳሴ የተደረገው የረዥም ርቀት ጉዞ ስኬታማ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይህም ሁኖ ችግሮች የሉም፤ አልነበሩም፤ መንገዱ ሁሉ ቀናና የተስተካከለ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡

ኢህአዴግ በአመራር ደረጃ የተከሰቱትን ችግሮች በተለይም ኪራይ ሰብሳቢው፣ ሙሰኛውና ጥገኛው በመንግስታዊ የኃላፊነት ቦታዎች የተቀመጡ ግለሰቦችን በመሳሪያነት በመጠቀም በመንግስትና በሕዝብ ሀብት ዘረፋ፤ በመልካም አስተዳደር በፍትሕ ላይ የተፈጸሙትን ችግሮች ሁሉ ነቅሶ በማውጣት በጥልቅ ተሀድሶው መሰረት ሰፊ ለውጦችን ለማስመዝገብና የሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ በየደረጃው ሰፊ እንስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ አይነቱ ሁኔታ ዳግም እንዳይከሰት የቁጥጥር ዘዴዎችን ማጠናከርና መዘርጋት አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በየደረጃው የሚደረጉት የማጣራትና ተጠያቂዎችን ለሕግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የሙስናና ፀረ ዲሞክራሲ አምባገነናዊ አካሄዶችን ለመግታት በዋናው የፖለቲካ  አመራር ይህ ቀረው የማይባል የውስጥ ጠንካራ ትግል መካሄድ በመጀመሩና በጥልቅ ተሐድሶው ሒደት የሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ በመኖሩ ለውጦች ተመዝገበዋል፡፡ የጸረ-ሙስና ትግሉ ጅምር ብዙ ቢቀረውም የተወሰነ ርቀት መራመድ ተችሎአል፡፡ ይህ የተጀመረው ሀገራዊ ልማትና እድገት በሕዝቡ ዋነኛ ተሳትፎ እንደሚቀጥል፤ ከድሕነት ለመውጣት የተጀመረውም ትግል በብሔር ብሔረሰቦች ወሳኝ ተሳትፎ ከዳር እንደሚደርስ ያረጋግጣል፡፡ ለዚህ ሁሉ በየአመቱ እየተከበረ ያለው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአል እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy