Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የታገሰ ማር ይበላል”

0 981

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የታገሰ ማር ይበላል”

                                                   ቶሎሳ ኡርጌሳ

መንግስት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን በወሰዳቸው ተከታታይ ርምጃዎች የመኸር ምርት ሊጨምር ችሏል። ይሁንና አንዳንድ ወገኖች ‘ምርትና ምርታማነት ጨምሯል ከተባለ ለምን የዋጋ መናር ይፈጠራል?’ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ምርትና ምርታማነት ከጨመረ ገበያውም በዚያው ልክ መረጋጋት እንዳለበት እሙን ሆኖ፤ የመኸር ምርቱ ተሰብስቦ ወደ ገበያው እስኪገባ ድረስ የዋጋው ሁኔታ በነበረበት ሊቀጥል መቻሉን ግን ማንም የሚገነዘበው ይመስለኛል። እናም ጉዳዩ ኦሮሞ አባቶቻችን “obsaatu damma nyaattaa” (“የታገሰ ማር ይበላል”) እንደሚሉት ዓይነት ነው። ማንኛውም ሰው ከታገሰ ጥሩ ነገር ያጋጥመዋል። እናም የጨመረው የመኸር ምርት ወደ ገበያ እስኪወጣ መጠበቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ርግጥ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ግብርናው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ተስፋ ተጥሎበታል። ይህ መዋቅራዊ ለውጥ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ጭምር ያለመ ነው። እናም ከዚህ ይልቅ ግብርናው ለውጥ ባመጣ ቁጥር ዜጎች ሊያገኙ ስለሚችሉት ጠቀሜታ ማውጋት ጉዳዩን ጠቅልሎ ለመመልከት የሚያስችል ይመስለኛል።

በአሁኑ ወቅት ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚቻል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። ተገቢው ውጤትም ተገኝቶበታል።

የዋነኛ የሰብል ምርቶች ከጠቅላላው የግብርና ምርት ተጨማሪ እሴት ያላቸው ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ይህ የዕድገት ጭማሬ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው ግብረ መልስ ሳይካተት በግብርና ዕድገት ምክንያት ብቻ በያዝነው የዕቅድ ዘመን አማካይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ 12 ነጥብ ሁለት በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህን ለመከወንም መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የሀገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር እነሆ የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን ሀገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን የመጀመሪያው የልማት ዕቅድ አረጋግጧል።

እርግጥ በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም። ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል። በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል። ለገበሬው በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው። የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።

አርሶ አደሩን በማህበር የማደራጀት ሥራ በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች በጋራ እንዲፈታ አስችሎታል። መንግሥት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

መንግሥት ባስቀመጣቸው የግብርናው ዘርፍ የልማት ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂዎችና መርሀ ግብሮች በመጠቀም ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን በማበረታታትና በመሸለም በርካታ ውጤታማ አርሶ አደሮችን ለማፍራት ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮች በመፍጠርም ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም በሂደት የተጎናፀፍነው ድል ለላቀ ሁለተኛው ዕቅድ እንዳነሳሳን ግልፅ ነው።

ከዚህ አኳያ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በትክክል ውጤትማ እየሆኑ ነው። በአፈጻጸሙ ከተጠበቀው በላይ መጓዙን መረጃዎች ያመለክታሉ። የመኸር ምርት መጨመሩ የልማት ዕቅዱ ገቢራዊነት ትክክለኛ ማሳያ ነው። ሆኖም የሚመለከተ አካል ምርት መጨመሩን መረጃዎችና ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዞ ሲገልፅ  ላይ ምርት ጨምሯል ባለበት ከሰዓት በኋላ የዋጋ መረጋጋት ይኖራል ማለት አይደለም። አስቀድመው ወደ ገበያ ውስጥ የገቡ ምርቶች በነበረው ዋጋ የሚሸጡ ከመሆናቸውም በላይ፤ አዲሱ የመኸር ምርት ተሰብስቦ አርሶ አደሩ የሚያዋጣውን ዋጋ ቆርጦ ወደ ገበያው ውስጥ እስኪያስገባ ድረስ ጊዜ ያስፈልጋል። እናም ይህን የጊዜ ዑደት “ምርት ከጨመረ ለምን ዋጋ አይቀንስም?” የሚሉ ወገኖች ሊያውቁት ይገባል እላለሁ። ለዚህም ነው— መስከንንና አንድን ሁኔታ ተረጋግቶ መጠበቅ የኋላ ኋላ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ለማመላከት ኦሮሞ አባቶቻችን “obsaatu damma nyaattaa” (“የታገሰ ማር ይበላል”) በሚል አባባላቸው ወጣቶችን የሚያስተምሩት።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy