Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢህአዴግ ሰሞነኛ ውሎ

0 633

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢህአዴግ ሰሞነኛ ውሎ

ዳዊት ምትኩ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እያካሄደ ያለውን ግምገማ ከጥልቅ ተሃድሶው ጋር የሚያያዝ ነው። ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ካነሳቸው ነጥቦች ውስጥ ከምንም ነገር በላይ በአገሪቱ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመፍታትና የፌዴራል ስርዓቱን ከአደጋ ከመታደግ አኳያ የጋራ አቋም በመያዝ ያስቀመጣቸውን ጉዳዩች ተስፋ ሰጪዎች ናቸው። ድርጅቱ በሰሞነኛ ውሎው የያዘው የጋራ አቋም የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ ነው።

ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ጊዜያዊ ተግዳሮቶች እየፈታ የመጣ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ ከአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል።

በኢህአዴግ መሪነት የሀገሪቱ ህዝቦች ወደውና ፈቅደው አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመመስረት የሚያስችለውን የተመቻቸ ሰላማዊ ምህዳርም ተፈጥሯል። ይህ ሁኔታም ህገ- መንግስታቸውን በጋራ መክረው ዘክረው እንዲሁም አምነውበት እንዲያፅድቁት ከማድረጉም ባሻገር፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እንዲመሰረት አስተማማኝ መሰረት ጥሏል።

ይህም በደርግ ውድቀት ማግስት ‘ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው’ በማለት ሲያሟርቱ የነበሩ ተንታኝ ተብዬዎች ጥንቆላ መና እንዲቀር ያደረገ የሰላም መስመር ነው። እናም ኢህአዴግ ያኔ የተከተለው ትክክለኛ መስመር ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ያደረገ ብቻ ሳይሆን፤ ከብተናም እንድንድን ያደረገን ነው ማለት ይቻላል።

በደርግ ውድቀት ማግስት ከብተና እንዴት መዳን እንደሚቻል ትምህርት የቀሰመው ኢህአዴግ በተሃድሶው ወቅትም ይህን ፈተና ከተሞክሮው ማለፍ ችሏል። እንዲያውም የኪራይ ሰብሳቢነትንን የጥገኝነትን አደጋ መስቀረት በመቻሉ አሁን ላለንበት ሁለንተናዊ ዕድገት ልንበቃ የቻልንበት ምስጢር ይኸው ይመስለኛል።

በዚህ ሁኔታ እየተማረ የመጣው ኢህአዴግ፤ በሀገራችን ውስጥ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት በተሃድሶው መስመር የተቀመጠውንና በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ካለው ፅኑ ፍላጎት ተነስቶ በህገ መንግስቱ መሰረት ምርጫ 97ትን አካሂዶ በጎዳና ላይ ነውጠኞች የተፈጠረውን ችግርንም መፍታት የቻለ ህዝባዊ ድርጅት ነው።

በአጭሩ ከፈተናዎች የተማረ ድርጅት ነው ማለት ይቻላል። እናም ዛሬ ከፊቱ የተጋረጡበትን አደጋዎች ለመፍታት ግምገማ ላይ ተቀምጧል። ግምገማውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በፈጠረው ተስፋና የተከመሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ፊቱ ላይ በደቀኑት ሥጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ እንዳለ በትክክል ተገንዝቧል።

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተጀመረውን ፈጣን ዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እስካሁን የመጣበትን ርቀት ለማሳካትም ሆነ ወደፊትም ለማስቀጠል በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ካሁን በፊት የነበረው አኩሪ በመተጋገል ላይ የተመሠረተ አንድነት በቦታው ላይ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንመ አምኗል።

ኮሚቴው እስካሁን ባደረገው ግምገማ በአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእርስ በርስ መጠራጠር ያመዘነበት፣ አለመተማመን ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣበት መሆኑን በጥብቅ በመገንዘቡ ለመፍትሔውም ቅርብ የሆነ ይመስለኛል።

በመሆኑም ባደረገው ሰፊና ጥልቅ ውይይት በዚህ ረገድ የታዩ ችግሮችን በስፋት መርምሮ የቆየውን የሐሳብና የተግባር አንድነት ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መድረሱ የሚያስመሰግነው ነው።

እንዲሁም ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቱ ኢሕአዴግ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በርካታ አበረታች ውጤቶች የተገኙበት ቢሆንም፣ በሚፈለገው ደረጃ ጥልቀት ያልነበረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተመልሰን ወደ አዘቅቱ የመመለስ ጉዳይ ሊኖር እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅቱ አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን በሚገባ በመገንዘቡም በግምገማው ማጠቃለያ ላይ ገዥ የሚሆን ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ለምትገኝበት አስጊ ሁኔታ ድክመቱ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ይህን በአስተማማኝ ሁኔታ መቀልስ ስለሚኖርበት ነው።

በድርጅቱ ውስጥ በየደረጃው ያለው አመራር ከሞላ ጎደል የዚሁ ድክመት ተጋሪ ቢሆንም፣ ሥራ አስፈጻሚው የዚህ ችግር ዋነኛ ባለቤት መሆኑንና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ችግሮችን በቁጭት መንፈስ ከመፍታት ይልቅ የእርስ በርስ ንትርክ ላይ ማተኮሩ የችግሩ ገዥ ጉዳይ አድርጎ መውሰዱ ፓርቲው የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ምን ያህል ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ድርጅቱ የውሰጠ ድርጅት ጉዳዩችን በተመለከተበት ሁኔታ ደረጃው ከፍተኛ ድክመት የሚስተዋልበት መሆኑንና በህዝቡም ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሕይወት በመፍጠር ረገድ ያደረሰውን አሉታዊ ተፅዕኖን አንጥሮ በማወቁ ወደፊት ለሚወስዳቸው የመፍትሔ እርምጃዎች በር የሚከፍቱ ይመስሉኛል።

ድርጅቱ አሁን በሚገኝበት የጥልቅ ግምገማ ሂደት ከላይ የተጠቀሱትት ጉዳዩች የህዝቡን የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ፣ የልማትና የሰላም ጥያቄዎችን በሚገባ ባለመመለስ ከስኬት ጎዳና የሚያርቁ መሆናቸውን በመዳቱ በመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ መግባባት መፈጠሩ ስር ነቀል ለውጥ ለማድግ የሚያስችለው ይመስለኛል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገሪቱ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመፍታትና የፌዴራል ሥርዓቱን ከአደጋ ከመታደግ አንፃር የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መንገድ የተጠናከረ ሥራ ማከናወን የሚያስችለው ነው።

ስራ አስፈጻሚው ለአገሪቱ ሕዝቦች ጥያቄ በተሟላ መንገድ መመለስና ለፌዴራል ሥርዓቱ በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና ለዚህ ግብ ዝግጅት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችለውን የተሳካ ውይይትና መተጋገል በፅናት ቀጥሎበት በቅርብ ጊዜ በድል እንደሚጠናቀቅ ገልጿል። ህዝቡ የሚጠብቀውም ይህንኑ ይመስለኛል። እርግጥ ድርጅቱ ቀደም ሲል ካለው ችግሮችን ፈትቶ ወደ ተሻለ መንገድ የመጓዝ ባህል በመነሳት የአገሪቱን ወቅታዊ ችግሮች ስር እንዳይሰዱ ማድረግ የሚያስችል ቁመና ያለው መሆኑ አይታበይም። እናም በሰሞነኛው የግምገማ ውሎው ላይ የገለፃቸውን ቁርጠኝነት በማጠቃለያው ላይ ለአገሪቱ የሚበጅ ዘላቂ መፍትሔ በማጀብ እንደሚያረጋግጥ ከወዲሁ ለማወቅ የግድ ነብይ መሆንን የሚጠይቅ አይመስለኝም።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy