Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የእንቦጭ አረምን ከማስወገድ አንፃር የምሁራኖቻችን ቁልፍ ሚና

0 277

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የእንቦጭ አረምን ከማስወገድ አንፃር የምሁራኖቻችን ቁልፍ ሚና

                                                                                   ዋኘው መዝገቡ  

የእንቦጭን አረም ከጣና ሀይቅ ላይ ነቅሎ ለማጥፋት የተደረገው ሕዝባዊ ርብርብ ክልል ሳይወስነው የሀገራችን ዜጎች ከተለያዩ ማእዘናት ያንቀሳቀሰና ያሳተፈ በመሆኑ የነበረውንና ያለውን ሕዝባዊ አንድነት የበለጠ ያረጋገጠ፤ ሁሉን በጋራ ያሰለፈ መሆኑ ሲታይ በእጅጉ የሚያኮራ ተግባር ነው፡፡ እምቦጭ አረሙን ለማረምና ለማጥፋት በሌላም መልኩ የእኛው ዜጎች በፈጠራና ምርምር ስራ የሰሩት ማሽን በአይነቱ የመጀመሪያ ሆኖ ዜጎችንም ሀገርንም ያስደሰተ ተግባር ነው፡፡ ጎንደርና ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ለየራሳቸው የሰሩትን ማሽን አቅርበዋል፡፡ ወደስራም ገብቶአል፡፡ እሰየው፣ ይበሉ፣ ይበርቱ ያሰኛል፡፡

በሀገራችን በሳይንሳዊ ዘዴዎች ላይ የተመሰረቱ የጥናትና ምርምር ስራዎችን መስራትና በስፋት ማካሄድ በወጣቱ ዘንድ የተለመደ ስራ ሁኖ  እንዲቀጥል ማድረግ ከድሕነትና ከችግር መውጪያ ብቸኛ መገዳችን ነው፡፡ ሳይንሳዊ የጥናትና የምርምር ስራዎችን በአልተገደበ መልኩ በማካሄድ በብዙ መስኮች መስራት ስንችል ዘርፈ ብዙ ለሆኑት ችግሮቻችን መፍትሔ ለማግኘት ያስችለናል፡፡

በጥንት ዘመን የነበሩት ወጣቶች የሰሩት የፈጠራ ስራ መጀመሪያ መነሻ ስራውን “ሀ” ብሎ በአንድ ሞዴል ከጀመረ በኋላ ደረጃ በደረጃ እያደገ ከመጀመሪያው መነሻ የሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ የበለጠ እያሻሻለው እያሳመረው አቅሙን እየገነባ ደረጃውን በበለጠ ብቃትና አገልግሎት ሰጪነት እየለወጠው ይሄዳል፡፡

ከሽጉጥና ጠብመንጃ እስከ ሮኬት፣ ሚሳኤል፣ ታንክና መድፍ ከተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት ጭራሹንም አሕጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ድረስ መስራት የቻለው የሰው ልጅ የራሱን የምርምርና የፈጠራ ስራ ተጠቅሞ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስልክ፣ ሬድዮ፣ አውሮፕላን፣ መርከብ፣ ሄሊኮፕተር፣ ኮምፒዩተር ወዘተ የፈጠራ ስራዎችና የምርምር ውጤቶች ሁሉ የሰው ልጅ ፈጣን አእምሮውን፣ የፈጠራና የምርምር አቅሙን ተጠቅሞ ያስመዘገባቸው ድንቅ ስራዎቹ ናቸው፡፡

ዛሬ ላይ የሰው ልጅ  ጭርሱንም ከመሬት አልፎ  በመሄድ ሕዋን ለመቆጣጠር እየተራወጠ በፉክክር ላይ የሚገኝበት ዘመን ነው፡፡ በሰራቸው ዘመናዊ ሳተላይቶችና መንኮራኩሮች  በመታገዝ አለምንና ታሪክዋን እየለወጠ ይገኛል፡፡ በአለፉት አመታት በአውሮፓ በአንድ ወጣት ፈጠራ የተሰራው በምድር መኪና በሰማይ ትንሽ አውሮፕላን በባሕርና ውቅያኖስ ደግሞ ትንሽ በውሀ ላይ እንደልብዋ የምትሄድ መርከብ ሁሉንም በአንድ አቅፋ ያያዘች፤ ምጥን አካል የፈጠራ ስራ ሆና ወደ እውነትነት የተለወጠች ነች፡፡

በእርግጥ የውጭዎቹ ከእኛ የሚለዩት ለወጣቶቻቸው የፈጠራ ስራዎች ሳይዘገዩ ፈጥነው  ግዜ ሳይወስዱ እርዳታና እገዛ በማድረግ ውጤቱን ለማየት መቸኮላቸው ነው፡፡ የእኛዎቹ  ከዚህ መማር ቢሮክራሲና ምልልስ ሳያበዙ ማንኛውንም የፈጠራ ስራ ያቀረቡ ወጣቶች ስራቸውን ፈጥነው እንዲያስረዱ ጉዳዩን ለአጥኚ ኮሚቴዎች መምራት፣ ሲጸድቅ ጅምር ስራቸውን ሰርተው ሊያሳዩ የሚችሉበትን ገንዘብ ፈጥኖ መስጠት በሀገራችን የተጀመረው የአዳዲስ መሳሪያዎች የስራ ፈጠራ ችሎታና ተነሳሽነት እያበበና እያደገ፤ ወጣቶቹም ሞራላቸው እየተጠበቀ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡

መታወቅ ያለበት ትልቁ ነጥብ የእነዚህ ወጣቶች የስራና የፈጠራ ችሎታ በተለያየ መስክ  ሲሰራ ከሀገር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃም ትልቅ የውጭ ገበያ ሊስብና ሊያመጣ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና ገቢ ለሀገራችን ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ሀገራችንን በአለም አቀፍ መድረክ የበለጠ በወጣቶችዋ የፈጠራ ስራ እንድትታወቅ ያደርጋታል፡፡

በቅርቡ የሀገራችን ትልቁ የጣና ሀይቅ የተጋረጠበትን የእምቦጭ አረም ለማስወገድና ኃይቃችንን ከጥፋት ለመታደግ አረሙን የመንቀል ብሔራዊ ዘመቻ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይሄው የተጋረጠብን አደጋ ለግዜው በጣና ሀይቅ ላይ ቢታይም ችግሩ በሌሎች ሐይቆቻችንም ላይ ሊከሰት እንደሚችል የሚገልጹ ምሁራን አሉ፡፡ አረሙን ማስወገድ፣ በሕልውናችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ መክላት ኃላፊነቱ የእኛና የእኛ ብቻ ነው፡፡ ግዜ የሚሰጠው ጉዳይም አይደለም፡፡

በዚህ ረገድ እምቦጭ አረሙን ነቅሎና አጭዶ ለማስወገድ የሚችል ሀገር በቀል መሳሪያ በጎንደርና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ተሰርቶአል፡፡ ምስጋና ለምሁሮቻችን ይድረሳቸው፡፡ በአሁኑ ሰአት የጎንደሩ ማሽን በኃይቁ ላይ እንዲሰማራ ተደርጎ ስራውን እየሰራ ይገኛል፡፡ መጀመሪያ ላይ ማሽኑ ግዙፍ ስለሆነ ለማጓጓዝም የሚከብድ የነበረ ሲሆን በስፍራው ላይ ተጭኖ እንዲደርስ ተደርጎ ስራውን ጀምሮአል፡፡

ይሄ በሀገር ልጆች የተሰራ የፈጠራና የምርምር ስራ እንደ ዜጋ እንደ ሀገር በእጅጉ የሚያኮራን ነው፡፡ በቀጣይ የሚኖረው ሂደት ማሽኑ ከመጀመሪያው ልምድና ተሞክሮ በመነሳት የበለጠ እየተሻሻለ ስራዎችን በፍጥነትና በቅልጥፍና የሚሰራበት መንገድ እየታየ ሊሻሻል የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ይሄ በስራው ሂደት ውስጥ የሚፈተሸ ይሆናል፡፡ አንድ የፈጠራ ስራ መነሻና በሂደት እየተሻሻለ የሚሄድበት ደረጃ አለው፡፡ በዚህ መልኩ ቀጣይ የመለወጥና የማዘመን ስራዎቹ የሚቀጥሉ ሆኖ፤ ስራ በእጅጉ ሊወደስ ሊበረታታ ሊደነቅ የሚገባው ድንቅ ተግባር ነው፡፡

አሁንም በተለያየ መልኩ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶቻችን በብዙ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ በመመርኮዝ በመደገፍ አዳዲስ ማሽኖችን መሳሪያዎችን የመፍጠር የመስራት አቅም ያላቸው መሆኑ ይታመናል፡፡ ለዚህ ስራ የሚሆነውን እንደ ሙያው አይነት ሰፊ ምርምርና ተግባራዊ ፍተሻ ሊያደርጉ የሚችሉባቸውን ጋራዦች ሰፋፊ ምርምር ሊያደርጉባቸው የሚችሉ ቦታዎችን ከልሎ መስጠት፤ ላብራቶሪዎችን በየክልሉ በስፋት ማዘጋጀት፤ የፈጠራ ስራ ችሎታና ፍላጎቱ ያላቸውን ወጣቶች በየፍላጎታቸው አደራጅቶ ባለሙያም መድቦ እንዲሰሩ፣ እንዲመራመሩ፣ ሙከራዎችን እንዲያደርጉ ማስቻል ተገቢ ነው፡፡ በቦታና በማቴርያል እጥረት ምርምርና የፈጠራ ስራ ለማድረግ የሚፈልጉ ወጣቶቻችን ተሰናክለው እንዳይቀሩ እንደልባቸው ሳይጨናነቁ እንዲሰሩ እንዳይቸገሩ የፌደራሉ መንግስትና የየክልሎቹን መንግስታት በማእከል ሁኖ የሚያስተባብር፤ ጉዳዮችን በመዋቅራዊ መልኩ የሚመራ፣ የሚከታተል፣ ፈጥኖ ውሳኔ የሚሰጥ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለቴክኒዮኒሎጂ ሚኒስትር የሆነ ማእከል መፈጠር አለበት፡፡

በርካታ አንጋፋ የሳይንስ ምሁራንና የምርምር ሰዎች በተለይ በጡረታ ላይ ያሉትን፣ በስራው ብዙ ተሞክሮ ያላቸውንና ያሳለፉትን የሚያቅፍ የሚሰራ አካል ነው መሆን ያለበት፡፡ ወጣቱ በምርምርና የፈጠራ ስራዎቹ ሊታገዝ ሊበረታታ ይገባል፡፡ ከጥቅም ውጭ የሆኑና አገልግሎት የማይሰጡ በተለያየ መስክ የሚገኙ የሚወገዱ ማቴርያሎችን ተብለው የሚጣሉትን በማእከል አደራጅቶ ለምርምርና ለአዳዲስ ስራ ፈጠራ እንዲያግዙ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለክልሎችም ማከፋፈል ይቻላል፡፡

የሕክምና መሳሪያዎችን፤ መኪናዎችን፤ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን)፤ መለስተኛና ከፍተኛ የሆኑትን የጭነት መኪናዎችን፤ አውቶቡሶችን፤ ኃይል አመንጪ ጀነሬተሮችን፤ የተለያዩ የጦር መሳሪያ ሞዴሎችን፤ አነስተኛና ፈጣን መርከቦችን፤ የአርሶ አደሩን አድካሚ ስራ የሚቀንሱ ሀገር በቀል የቴክኒዮሎጂ ስራዎችን መዝራትን፣ ማረምን፣ ማጨድና መውቃትን የሚያቀሉ ቀለል ያሉ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሁም ሌሎች በብዙ መስኩ በሀገራችን ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሰፊ የፈጠራ ስራዎችን ወጣቶቻችን ሰርተው እንደሚያሳዩን ምንም ጥርጥር የለውም፤ አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገላቸው፡፡ ወጣቶች የበለጠ ተነሳሽነት አግኝተው በስራው ላይ ሊተጉ የሚችሉት የሞራልና የማቴርል ድጋፍ ሲያገኙ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ባጠቃላይ፣ በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋትና ለማስወገድ የእራሳችን ዜጎች ሰርተው ወደስራ ያስገቡት ማሽን ለሀገራዊ ችግር ሀገራዊ መፍትሔ የበለጠና የተሻለ አማራጭ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡ ሌሎች ችግሮቻችንን የሚፈቱ የራሳችን ምሁራን የፈጠራ ስራ የሆኑ ማሽኖችም በተለያየ ዘርፍ ተሰርተው የምናይበት ግዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ምርምሩና የፈጠራ ስራው ለሀገር መድሕንና ትንሳኤ ሆኖ ሀገራችን በሳይንስና ምርምሩም መስክ ከፍተኛ ድሎችን በወጣቶችዋ እንደምታስመዘግብ ጠንካራ እምነት አለ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy