Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የድርደሩ ስኬት ያሰጋቸው ቡድኖች ሴራ እንዳይሆን?

0 407

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የድርደሩ ስኬት ያሰጋቸው ቡድኖች ሴራ እንዳይሆን?

ብ. ነጋሽ

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 17 ፓርቲዎች ኢህአዴግን ጨምሮ የአገሪቱን ዴሞክራሲ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ማጎልበትን ዓላማ ያደረገ ድርድር ማካሄድ ከጀመሩ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ነው የቀሩት። ይህ ድርድር ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር የሚደረግ ይሁን እንጂ በኢህአዴግ ችሮታ የተሰጠ አይደለም። ከዚያ ይልቅ አገሪቱ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ባለፈችበት ሁለት ተኩል አሥርት ዓመታት ሂደት ዴሞክራሲውን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ እንዲጎለብት የግድ ባለ ነባራዊ ሁኔታ ግፊት የመጣ ነው።

በ1987 ዓ/ም የጸደቀው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ስራ ላይ በዋለባቸው ዓመታት አምስት ሃገራዊ፣ አራት አካባቢያዊ (አዲስ አበባና ደሬደዋን ጨምሮ፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች) ምርጫዎች ተካሂደዋል። 5ኛው የአዲስ አበባና ድሬደዋ እንዲሁ የአካባቢ ምርጫ በያዝነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይካሄዳል። እስከአሁን በተካሄዱ ምርጫዎች አሸናፊ የሆኑ ፓርቲዎች የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የክልልና ከዚያ በታች ያሉ መዋቅሮች ምክር ቤቶች መቀመጫዎችን ሲይዙ የነበረው ህገመንግስቱ በሚያዘው የአብላጫ ድምጽ አሸናፊ ስርአት ነበር።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 54 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሚል ርዕስ ስር፤

 

  • የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጢር በሚሰጥበት ሥርአት በየአምስት ዓመቱ በህዝብ ይመረጣሉ።
  • የምክር ቤቱ አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መሃከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርአት ይመረጣሉ። የተለየ ውክልና ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የታመነባቸው አናሳ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በምርጫ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ይሆናሉ። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል።
  • የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር የህዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ቁጥር መሰረት በማደረግ ከ550 የማይበልጥ ሆኖ ከዚህ ውስጥ አናሳ ብሄረሰቦች ከ20 የማያንስ መቀመጫ ይኖራቸዋል።

 

ተብሎ ተደንግጓል።

በዚህ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ላይ በመመሰረት በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የምርጫ ህግ ቁጥር 532/1999፣ የምርጫ ሥርአት በሚል ርዕስ ስር፣

 

  • የምርጫ ሥርአት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሚወዳደሩ ዕጩዎች መሃከል አብላጫ ድምጽ ያገኘ ዕጩ በምርጫ አሸናፊ የሚሆኑበት የምርጫ ሥርአት ነው።

 

ይላል።

እንግዲህ ያለፉት ምርጫዎች በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት ሲካሄዱ የቆዩ ናቸው።

በዚህ ሂደት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዙር በተካሄዱ ምርጫዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፌደራልንም ሆነ የክልል ምክር ቤቶችን መቀመጫዎች መጋራት የቻሉበት ሁኔታ ነበር። ይሁን እንጂ ከአራተኛው ዙር በኋላ በተካሄዱ ምርጫዎች ኢህአዴግ በሚወዳደርባቸው አራት ክልሎች (ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ) በአብላጫ ድምጽ ሁሉንም የምክር ቤት መቀመጫዎች ያሸነፈበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በአራተኛው ዙር ምርጫ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መደረክ (መድረክ) የተሰኘው ፓርቲ አግኝቶት ከነበረው አንድ መቀመጫ በስተቀር። ኢህአዴግ በማይወዳደርባቸው አምስት ክልሎችም ቢሆን ከፊል ሃራሪ፣ አፋር፣ የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል አሸናፊ የሆኑት የኢህአዴግ የዓላማ አጋር ድርጅቶች ናቸው።

ይሁን እንጂ ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች ሁሉንም የምክር ቤት መቀመጫዎች አሸነፉ ማለት ሌሎች ተቃዋሚዎች ምንም ድምጽ አላገኙም ማለት አይደለም። ቀላል የማይባል የህዝብ ድምጽ አግኝተዋል። መቀመጫ እንዳያገኙ ያደረጋቸው እጩዎች ባቀረቡባቸው የምርጫ ክልሎች በ50 + 1 አብላጫ ድምጽ መሸነፋቸው ነው። ይህ ሁኔታ በመንግስት ውስጥ የማይሰሙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጾች እንዳይኖሩ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም የምርጫ ስርአቱን ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ይህም ዴሞክራሲውን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ የማስፋት እርምጃ  ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በዚህ መነሻነት የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማሰፋት መንግስና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የአነሳሽነቱን ሃላፊነት ወሰዱ። እናም በ2009 በጀት ዓመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባስተላለፉት የዓመቱ የስራ ክንውን መግለጫ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር እንደሚደረግ አሳወቁ። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፤

. . . ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ከማበልፀግ አኳያ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ በሃገራችን የፍላጐት ብዙህነት እንዳለ ተገንዝቦ፣ እነዚህን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመግለፅ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የምክር ቤቶቻችንን ተዋፅኦ የማጐልበት ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ሃገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርዓት በመመራት ባለፉት ሀያ አምስት ዓመታት በድምሩ  ለአስር ጊዜ ሃገራዊ፣ ክልላዊና ከባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ  የህዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም፣ በሃገራችን ወሳኙ የስልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል። በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጐት ያላቸው ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች በምክር ቤቶቻችን ውስጥ የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል። ስለሆነም ይህን የመሰለው ሁኔታ ስርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በህግ ማእቀፍ በተደገፈ አኳኋን የህዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል።

ማለታቸው ይታወሳል። ይህን ተግባራዊ የሚደረግበትን ሁኔታም አስመልክተው ሲናገሩ፤

የሃገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ አንዱ ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ ይሆናል። ሃገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ ሃገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል። ስለሆነም የምርጫ ህጋችን የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል። ይህም በፓርቲዎች መካከል በሚካሄድ የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛና ሃገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ ግልፅነትን የተላበሰ የድርድር ሂደት የሚፈፀም ይሆናል።

ብለዋል።

እንግዲህ በኢህአዴግና በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል በመደረግ ላይ ያለው ድርድር ከላይ የተገለጸውን ዓላማ መነሻ ያዳረገ ነው። ኢህአዴግን ጨምሮ በድርድር ላይ የሚገኙት 17 ፓርቲዎች 12 ያህል አጀንዳዎች ላይ ለመደራደር መስማማታቸው ይታወሳል። እስካሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ በምርጫ አዋጅና በምርጫ ሰነምግባር ደንብ ላይ ድርድር አካሂደዋል። በዚህ ድርድር በርካታ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ተስማምተዋል። ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መሃከል ከላይ የተጠቀሰውን ህገመንግስታዊ የምርጫ ስርአት ማሻሻልን የሚመለከት ሁሉ ይገኝበታል። ይህ በድርድር የተደረሰበት የማሻሻያ ሃሳብ በፓርቲዎች የሚወከል ሁለም የህዝብ ድምጽ እንዲሰማ ማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

በዚህ መሰረት የምርጫ ስርአቱ የአብላጫና የተመጣጣኝ ውክልና ቅይጥ እንዲሆን ተስማምተዋል። በቅይጥ የምርጫ ስርዓት 80 በመቶ የአብላጫ ምርጫ ድምፅ 20 በመቶ ደግሞ በተመጣጣኝ ድምፅ የፓርላማው ወንበር እንዲያዝ ነው ከስምምነት የደረሱት። የአብላጫ እና ተመጣጣኝ ድምጽ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ስርዓት በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ የሚደረግ እንዲሆንም ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ፓርቲዎቹ በተስማሙበት የአብላጫና ተመጣጣኝ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና ስርአት አሁን ካለው የምክር ቤት መቀመጫ 110 ተጨማሪ መቀመጫዎች በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲኖር ያደርጋል። ይህ የሃገሪቱን የዴሞክራሲ እድገት ከፍታ የሚያሳይ ትልቅ አመርታዊ ለውጥ ነው።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረግ ሃሳብ የቀረበበት ታሪካዊ ድርድር ላይ በንቃት በመሳተፍ ህዝባዊ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ የቆዩ አንዳንድ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ችግሮች እየታዩ ነው። በተለይ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ውስጥ የታየው የአመራር ውዝግብ ፓርቲውን ከድርድሩ እንዳያሰናክለው ስጋት አሳድሯል፤ በህዝቡ ዘንድ። የፓርቲውን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደን ጨምሮ በድርድሩ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ሶስት የድርጅቱ አመራሮች ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ መውጣቱን ሰምተናል። የተነሱበት ምክንያት በድርድሩ ላይ ፓርቲውን የማይወክል አቋም ይዘዋል የሚል መሆኑም ተነግሯል። አዲስ ተመረጥኩ ያለው አመራር ኢዴፓ ከድርድሩ መውጣቱንም አሳውቋል። ይህ በድርጅቱ ማህተም የወጣ ደብዳቤ በፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት በፕሬዝዳንትነት ተመርጫለሁ በሚሉ ግለሰብ የተጻፈና የድርጅቱ ማህተም ያረፈበት ነው።

በሌላ በኩል ከሃላፊነታችሁ ተነስታቹሃል የተባሉት እነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ብሄራዊ ምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚዎችን የመምረጥ ስልጣን ቢኖረውም ምክር ቤቱን ስብሰባ የመጥራት ስልጣን ያለው የፓርቲው ፕሬዝዳንት በመሆኑና አዲስ አመራር ተመረጠበት የተባለው ስብሰባ ከዚህ ውጭ በመሆኑ ምርጫው ህገወጥ ነው፣ ፓርቲው ከድርድር ወጥቷል በሚል የተጻፈው ደብዳቤም ሀገወጥ ነው ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት እወስዳለሁ በሏል።

ልብ በሉ፤ ጉዳዩ የፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ቢሆንም መከፋፈሉ ፓርቲውን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ከድርድሩ ሊያርቀው ይችላል። ጉዳዩ የህግ እልባት አግኝቶ ህግ የፈቀደለት አመራር ወደድርድሩ ቢመለስ እንኳን፣ ይህን እድል ያጣው የአመራር ወገን ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ተቃዋሚዎች ዘንድ እንደ ወግ የተያዘውን አካሄድ ተከትሎ፣ በፓርቲው ስም መግለጫ እያወጣና ተደራዳሪውን ወገን የመንግስት ተለጣፊ፣ የኢህአዴግ ምንትስ እያለ ውዥንብር የመፍጠር እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ የሚቀር አይመስልም። በተቃዋሚው ጎራ የዚህ አይነት አካሄድ የተለመደ ነው።

ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ የድርድሩን ሂደት መለወጥ ወይም ድርድሩን ማሰናከል ባይችልም አንጋፋ ተቃዋሚ ከሆነው ኢዴፓ ጋር ተያይዞ የሚነዛው ውዥንብር ህዝብን ሊያደናግር ይችላል። በአጠቃላይ ይህ አካሄድ ምናልባት ከፓርቲው የመነጨ ሳይሆን የድርድሩ ውጤት የሚፈጥረው አስተማማኝ ዴሞክራሲ ሁከት ለመቀስቀስ እንደማያመች የተረዱ በውጭ ሃገራት ያሸመቁ ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች እጅ እንዳይኖርበት ያሰጋል። ኢዴፓ በውስጡ የተፈጠረውን ችግር ፈትቶ የድርድሩን ሂደት ለመቀጠል በቅንነት የመስራት የህግም የሞራልም ሃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ፓርቲው የውስጥ ችግሩን ፈትቶ ወደድርድሩ እንዲመለስ ጫና ማሳደር ይጠበቅባቸዋል። የውስጥ ጉዳዩን መፍታት አቅቶት ውዥንብር መንዛት ቢሄደም ጆሮ ሊነፍጉት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy