የግብርናውን ዘርፍ ማበልፀግ
ይልቃል ፍርዱ
የሀገራችን የኢኮኖሚ መሰረት ሁኖ የኖረው ግብርና ነው፡፡ ግብርናውን ወደ ዘመናዊ ደረጃ ለመለወጥ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን የዘመናዊ እውቀት ባለቤት ለማድረግ በግብርና ሚኒስቴርና በግብርና ባለሙያዎች በየደረጃው ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ረዥም ርቀት በመሄድ አርሶአደሩን ስለአፈር አጠቃቀም፤ የተበሉ መሬቶችን ስለማከም፤ የአፈር መሸርሸርን ስለመከላከል፤ የተጋለጡ መሬቶችን በደን ስለመሸፈን፤ የዝናብ ውሀን በማቆር ለመስኖ ስራ አገልግሎት ስለሚውልበት በተጓዳኝም ስለቤት እንስሳት እርባታና ከብት ማድለብ፤ ስለንብ እርባታና ስለመሳሰሉት ሰፊ እውቀት እንዲገበይ ለማድረግ ተችሎአል፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋነኛ መሰረት የሆነውን ግብርናን በዘመናዊ መንገድ የማስፋቱና የማሳደጉ ስራ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ይህንን ስራ ስኬታማ ለማድረግ አርሶ አደሮቻችንን የዘመናዊ ግብርና እውቀት ባለቤት ማድረግ ለችግሩ መፍቻ ቁልፍ መፍትሄ መሆኑ ከታመነበት ውሎ አድሮአል፡፡ ለዚህም ነው በማስተማርና በማሳወቅ ስራ ላይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው፡፡
ባለፈው የመኽር ወቅት የተሰበሰበው የመኽር ምርት እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ በዘንድሮው አመት የበለጠ ምርት ለማግኘት የተዘራውን ምርት በአግባቡ የመሰብሰብ፤ እንዳይባከን የማድረግ ሰፊ ስራዎች ሊሰሩ ይገባቸዋል፡፡ በምርት አሰባሰብ ወቅት የሚከሰተውን ብክነት መከላከል አንዱ ቀዳሚ ስራና ትኩረት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በሀገራችን የተከሰተውን ድርቅ ለመመከትና ለመቋቋም በተደረገው ሰፊ ብሔራዊ ርብርብ ችግሩን በራስ አቅም ለመመከት የቻልነው በሀገሪቱ በተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ነው፡፡
ድርቁ የተወሰኑ የሀገራችንን አካባቢዎች ቢያጠቃም የዛኑም ያህል በቂ የዝናብ መጠን በማግኘት ሰፊና የተትረፈረፈ ምርት ለማምረት የበቁ የሀገራችን አካባቢዎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ደረጃ የተገኘውን ተረፈ ምርት ከአርሶአደሩ በመግዛት ከብሔራዊ ክምችትም በመጠቀም ለችግሩ ለመድረስ ተችሎአል፡፡
በየአመቱ እያደገ ለመጣው የግብርና ምርታችን ዋነኛው ምክንያት ሀገራችን የምትከተለው የግብርና ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ውጤታማ በመሆናቸው ሲሆን ይህም ሂደት ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ በ2017 ዓ.ም ሊደረስበት የታሰበው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የታቀደው ብሔራዊ ራእይ ተግተን ከሰራን ሙሉ በሙሉ እውን እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
በአምናው ተሞክሮ ከፍተኛ ምርት ለማግኘት የበቃን ቢሆንም በጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ አመት ሙሉ የተለፋበት የአርሶ አደሩ ምርት ለብክነት የሚዳረግበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ዝግ አልነበረም፡፡ በተለይም ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት ለብልሽት እንዳይዳረግ፤ ምርትን ከማሳ ወደ ውቅያ ቦታ፤ ከውቅያ ቦታ ወደ ጎተራ በማጓጓዝ፤ እንዲሁም በውቅያ ቦታ ዝግጅት የጥንቃቄ ጉድለት የተነሳና በጎተራ ውስጥ ከገባም በኋላ በአይጦችና በነቀዝ እንዳይወድም የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ለማሳደግ የልማት ሰራተኞችና የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ወቅታዊ መረጃ ምክርና ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ቀደም ባሉት ግዜያት በተገኙት ልምዶችና ተሞክሮዎች አርሶ አደሩን ማስተማርና ማሳወቅ በብዙ መልኩ ውጤታማ እንድንሆን ያስችለናል፡፡ አሁንም አርሶ አደሩን የማሳወቅና የማስተማሩ ስራ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል፡፡ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ አንዱ የተሰራው ትልቅ ስራ የመስኖ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡
የመስኖ አገልግሎት በሀገራችን ብዙም ያልተሰራበት ሁኖ ቢቆይም በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ አርሶአደሩንና አርብቶአደሩን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ መስኖን በተለይ በረሀማነት በሚያጠቃቸውና በረሀ ቀመስ በሆኑ ዝናብ አጠር አካባቢዎች በተጠና መንገድ መጠቀም የጓሮ አትክልትንና ሌሎችንም ምርቶች ለማልማት ከመዋሉም በላይ የሚቀያየር የአየር ንብረት ባለበት ሁኔታ የውሀ እጥረት ሳይኖር ለመጠቀም ያስችላል፡፡
ያልተጠበቀ ከባድ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ውሀው ያለአግባብ እንዳይባክን፣ ያለጥቅምም እንዳይፈስ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ማቆር ወደመሬት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባና እርጥበት እንዲፈጥር ማድረግ የአካባቢውን የተፈጥሮ አየር ንብረት ሚዛን ለመጠበቅ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ዝናብ በሌለበት ሰአት የታቆረውን ውሀ በመጠቀም የመስኖ ልማቶችን በተወሰነ ደረጃ ለማስኬድ ያግዛል፡፡
በአሁኑ ሰአት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ሰፋፊ የመስኖ ግድቦችን የመስራት ስራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የዚህ ጥቅም የገዘፈ በመሆኑ ስራው ተጠናክሮ በመቀጠል ላይ ሲሆን ተመሳሳይ ግድቦች በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ውሀን ከወንዝ በመጥለፍ እንዲሁም ከተፈጥሮ ዝናብ በስፋት ትነትን ተቆጣጥሮ በማከማቸት ለመስኖ ስራ እንዲውል የማድረጉ ስራ አዋጪ መሆኑ ታይቶአል፡፡ ለምርትና ምርታማነት እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡
የበጋ ወቅት የመስኖ ዝግጅት ከሁሉም በላይ በስፋት ሊሰራበት የሚገባው ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ለአርሶ አደሩና ለቤተሰቡ እንዲሁም ለእንሰሳቱ ሕይወት መድህን በመሆኑ ሲሆን አጠናክረን ልንገፋበት ይገባል፡፡ መንግስት በተለይ የአርሶአደሩንና የአርብቶአደሩን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ግብርናውን በተለያየ መልኩ ለማዘመን የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ በእርሻ ስራዎቻቸውና በሕይወታቸው ላይ የሚያስከትለውን ፈተናዎች ድርቅንና የውኃ እጥረት የመሳሰሉትን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
የመስኖ ግድብን ማስፋፋት፤ አርሶአደሩን የዘመናዊ ግብርና እውቀት ባለቤትና ውጤታማ ተጠቃሚ ማድረግ በስፋት እየተሰራባቸው ያሉ ስራዎች ናቸው፡፡ ምርታማ አዝእርቶች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ፤ በተደራጀ መልኩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ በስራ ላይ ማዋል፤ በተለይም የአርብቶ አደሩን ተንከራታች ሕይወት ለመለወጥ በሰፈራ እንዲሰባሰብ የትምሕርት፣ የጤና ወዘተ አገልግሎት እንዲያገኝ፤ የንጹህ ውኃ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የተሰሩት ስራዎች ውጤታማ ሆነዋል፡፡
ጉልበትን መሰረት ያደረገውን የሀገራችንን የእርሻ አሰራር ለማዘመን የተያዘው እቅድ ከግዜ ወደ ግዜ ከፍተኛ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ በግል ዘርፍ በእርሻና ግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎችም ዘመናዊ ግብርናን በመጠቀም ከፍተኛ ምርት በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ ግብርናችንን ወደ ሜካናይዝድ እርሻ ማሳደግ የግብርና መሳሪያዎችን መጠቀም አርሶ አደሮቻችን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑ ታምኖበት ደረጃ በደረጃ ወደስራው ለመግባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
አነስተኛና ዘመናዊ በሆነ የግብርና መሳሪያዎች አርሶ አደሩ ቴክኒዮሎጂን ተጠቅሞ እንዲያርስ ማድረግ የጉልበት ድካሙን እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ የማጨድ፤ የመሰብሰብ፤ የመውቃት፤ ምርት የመሰብሰብ ስራዎቹን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያካሄድ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማሕበር ዩኒየኖች ከፍተኛ የሆነ ድርሻን ይወጣሉ፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች ግብርናን ከማዘመን አኳያ በቀጥታ በስራው ተሳታፊ በመሆን የራሳቸውን ከፍተና ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ የግብርናው በዘመናዊ ደረጃ መደራጀትና መመራት አርሶ አደሩንና ሀገራችንን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በሀገር ደረጃ ውጤታማ በሆነ የግብርና ዘዴ የሚመረተው የተለያየ ምርት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ ለውጭ ንግድ በስፋት በመዋል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ያስገኛል፡፡ ምርቶቹ ለገበያ በሚሆን መልኩ ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲመረቱ ማድረጉም ራሱን የቻለ እውቀትና ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ለዚህም የግብርና ባለሙያዎች አርሶአደሩን የማስተማር ከፍተኛ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
ከግብርናው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ አርሶ አደሩን እያጠቃ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥና ድርቅ በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቋቋም ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ሰፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ በእርጥበት አዘል አካባቢዎች በዘንድሮ የበጋ ወራት እየተከናወነ ያለውን የበጋ እርሻ ሥራና የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከመሰራቱም በላይ በርካታ የመስኖ ግድቦች ተገንብተው ስራ ላይ ውለዋል፡፡ በመገንባት ላይ ያሉም አሉ፡፡
እነዚህ የተቀናጁና በእቅድ የተመሩ ስራዎች አርሶ አደሩን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ አስመዝግበዋል፡፡ የመስኖ ልማት ስራ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጠቀሜታው በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ከአስተራረስ ጀምሮ የአዘራር የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አጠቃቀም የፀረ-ተባይና ፀረ-አረም እንዲሁም ምርትን ከብክነት የመታደግ፤ እስከ የአሰባሰብ ዘዴ ድረስ ያሉ የምርታማነት ማበልጸጊያ አሰራሮችን የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችለዋል፡፡
ይሄን ልምድ ማስፋትና ማሳደግ ሌላውም አርሶአደር በምሳሌነት እንዲጠቀምበት ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትን መድረክ መፍጠር ከባለሙያዎች ይጠበቃል፡፡ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ የሚቻለው የአፈር ለምነትን ለማሻሻል ትኩረት በመስጠት አሲዳማ አፈርን በማከም ምርትና ምርታማነትን ዘላቂ በሆነ መንገድ በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የግብርና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው በገበሬው ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡
ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች የመሬት መሸርሸርን ብሎም የአፈሩን በውሀ መታጠብ ለመክላት በደን ተከላ እጸዋት እንዲለሙበት በማድረግ ቀድሞ የነበረውን የተፈጥሮ ቅርጽና የአየር ንብረት እንዲይዝ የማድረግ ሰፊ ስራ በተለያ ክልሎች ተሰርቶአል፡፡ ይህም የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ከማድረግ አልፎ ከማበልፀግ አንፃር ሊበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ተግባር ነው።