Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌዴራል ስርአቱ አበይት ስኬቶች

0 297

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴራል ስርአቱ አበይት ስኬቶች

                                                                                    መዝገቡ ዋኘው

የዜጎች የዘመናት ጥያቄ የነበረው ብዝኃነትን የማስተናገድ ችግር ሕዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም በጸደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አስተማማኝ ምላሽ አግኝቶአል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ለረዥም ዘመናት የዘለቀውና ለተማሪዎች ንቅናቄም አንዱና መነሻ የትግል አቅጣጫ የነበረው የብሔር ጭቆና ሲሆን ይህን መብት በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር ለማድረግ በርካታ የትውልዱ ወጣቶች ታላቅ መስዋእትነት ከፍለው አልፈዋል፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ ሰፍኖ ከኖረው ፊውዳላዊ አገዛዝ ጋር ተያይዞ የከፋ ጭቆናና እንግልት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጭቆና ባለበት ሀገር ደግሞ የተወሰኑ የገዢው መደብ አባላትና አምሳያዎቻቸው ካልሆኑ በስተቀር የአብዛኛው ብሔ፣ እንግልት፣ ድብደባ፣ ሞት . . . ሲዘንብባቸው፤ ብዝሀነት ተደፍጥጦ የግድ የገዢውን መደብ አባላት ፍላጎትና አስተሳሰብ ብቻ ለማስረጽ በሰፊው ሲሰራበት ኖሮአል፡፡ የትላንትናዋ ኢትዮጵያ የዚህ ታሪክ ሕያው ምስክር ነች። ይህንን የጭቆና ቀንበር ለመስበር ነበር ወጣቶች ወደ ጫካ ትግል የገቡት።

አለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ተብለው የሚጠቀሱት የመናገር፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ የፕሬስና የመናገር ነጻነት የተባሉት ሁሉ አይከበሩም ብቻ ሳይሆን የሚታሰቡ አልነበሩም፡፡

የዜጎች የተፈጠሩበትን ብሔርና ብሔረሰብ የማናናቅ፣ የማጥላላት፣ እንዲሸማቀቁ፣ ይልቁንም ራሳቸውን እንዲጠሉ፣ በባሕላቸው፣ በቋንቋቸው፣ በማንነታቸው፣ በእምነታቸው እንዳይኮሩ ሲደረግ ኖሯል፡፡ ወላጆች ከተለያዩ ብሔረሰቦች በመወለዳቸው የልጆቻቸውን ስም በግዴታ እንዲቀይሩ አስከመገደድ የደረሱበትን ሁኔታ ሁሉ ያሳለፈች ሀገር ነች፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች መብት በሕገመንግስቱ ጸድቆ መከበሩ ዜጎች በተወለዱበት ብሔረሰባቸው እንዲኮሩ በነጻነት ባሕላቸውን፣ እምነታቸውን፣ ቋንቋቸውን እንዲያበለፅጉ፣ በነጻነት አካባቢያቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳደሩ ያስቻለ፤ መብታቸውንና ሕልውናቸውን ያስከበረ ታላቅ እርምጃ ነው፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች መብት በፌደራል ስርአቱ መከበሩ ይሄንንም ተከትሎ በተገኘው ሰፊ እድል ክልላቸውን አካባቢያቸውን እንዲያለሙ መደረጉና መቻላቸው የመብታቸውም ተጠቃሚ ለመሆን መብቃታቸው ቀድሞ ከነበረው የብሔር ብሔረሰቦች የጭቆና ቀንበር እንዲላቀቁ በሙሉ ነጻነት የመብታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጎአል፡፡ የጭቆና ዘመን እንዲያከትም በመላ አገሪቱ እኩልነት እንዲሰፍን መደረጉ በኢትዮጰያ ታሪክ ውስጥ የተመዘገበ አንድ ግዙፍ ለውጥና እርምጃ ነው፡፡

በሀገራችን ለረዥም ዘመናት ለዘለቀው የውስጥ ግጭትና ትርምስ ለሰላም እጦት አንዱና ዋነኛው መነሻ የብሔር ብሔረሰቦች መብት አለመከበር የነበረ ሲሆን፤ የነበሩትን የቅራኔ ምንጮችና አለመግባባቶች በማጥበብና በመዝጋት ረገድ የተጨበጡ ውጤቶችን ለማስመዝገብ  ተችሎአል፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፋ የያዘች፤ ሰፊ ባሕሎችና እምነቶች ያሉዋት፤ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፤ የሚደመጡባት ሀገር ነች፡፡ በሀገራችን ሕብረ-ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓት በመመስረቱ ሕዝቦች የስልጣን ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይህም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ የዴሞክራሲ ስርዓት መሰረት ለመጣልና ለመገንባት፤ ድሕነትንና ኋላቀርነት ለማስወገድ ይቻል ዘንድ ፈጣን ልማትና ሀገራዊ አድገት ለማስመዝገብ አስችሏል፡፡

በአገሪቱ ያልተማከለ አስተዳደር መኖሩ  ሕዝቦች እንዲበታተኑ ሳይሆን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አላማ አንግበው ጠንካራ ኃገር የመገንባት አቅም ለመፍጠር አስችሎአቸዋል፤ በጋራ ዘርፈ-ብዙ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ችለዋል፡፡

ፌደራሊዝም እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም ሰፊ የግዛት ወሰን ባላቸው  ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመተግበር ተመራጭ ስርዓተ መንግሥት ሲሆን የትክክለኛው ፌደራሊዝም መነሻ ዴሞክራሲ እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ የክልሎችና የፌደራል መንግስቱ የስልጣን ክፍፍል በሕገ መንግሥቱና በሕግ የበላይነት የተረጋገጠ ነው፡፡

ቀደም ሲል ጀምሮ በአብዛኛው የሀገር ውስጥና ዲያስፖራ ነዋሪ ዜጎች አስተሳሰብ ውስጥ የነበረው የፌደራሊዝም ስርዓት ኢትዮጵያን ይበታትናታል የሚለው ስጋትና ፍርሀት ሰፍኖ ይታይ የነበረ ቢሆንም በተጨባጭ የተደረሰበት ውጤትና የተገኘው ድል የመበታተን አደጋውን ስጋት ቀርፎታል፡፡ ስርዓቱ ከመበታተን ይልቅ ለዜጎች የአንድነታቸው ማሰሪያ፤ የአብሮነታቸው ማጎልበቻና ማሳደጊያ ጽኑ መሰረት ሆኖአል፡፡

የሀገሪቱ ሰላምና ደሕንነት ይበልጥ የተረጋገጠው ኢኮኖሚያዊ እድገቷ የተፋጠነው የዜጎች ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት የተሻሻለው ዴሞክራሲና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማበብ የጀመረው ሀገራችን አለም አቀፍ ተሰሚነቷና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እያደገ የመጣው ከፌደራል ስርአቱ እውን መሆን በኋላ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲውም ሆነ በአህጉራዊና አለም አቀፉዊ የፖለቲካ መድረኮች ውስጥ ከፍ ያለ ተሰሚነትና ተደማጭነት ማግኘት ችላለች፡፡ ለዚህም በአለም አቀፍ ደረጃ ከኒውዮርክና ከብራሰልስ ቀጥሎ ሶስተኛዋ  የዲፕሎማቲክ ከተማ ለመሆን የበቃቸው አዲስ አበባ ነች፡፡ ይህን እድል ሌሎች ሀገራት አላገኙትም፡፡

ኢትዮጵያ የምትከተለው ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ስልጣንን ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት የሚያከፋፍል በመሆኑ ያልተማከለ አስተዳደርን አስፍኖአል፡፡ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እድሉ ስለተፈጠረላቸው በሀገሪቱ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸውን ባሕልና ታሪካቸውን በስፋት የማሳደግ የመጠበቅና የመንከባከብ እድሉን አግኝተዋል፡፡

የፌደራላዊ ስርአቱ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ በሀገሪቱ እድገት ላይ ሁሉም እኩል ተረባርበው እንዲንቀሳቀሱ በማድረጉ እየተመዘገበ ላለው ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ስኬታማ መሆን መሰረት ሆኖአል፡፡

በሀገሪቱ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጣቱን በእውቀት ከማነጽ ጎን ለጎን የፌደራል ስርአቱን ምንንትና ሀገራዊ ፋይዳ የማሳወቅና የማስረዳት፣ የመቅረጽ፣  ሕገ- መንግስቱን በአግባቡ ተገንዝቦ ለለውጥ የሚተጋ ትውልድ መፍጠር አቢይ ትኩረታቸው ሊሆን ይገባል፤ ፌደራል ስርአቱን ሊጠብቀውና ሊንከባከበው የሚችለው ተተኪው ትውልድ ነውና፡፡

ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለውን የፌዴራል ስርዓት በአለማች የሚገኙ  በርካታ ሀገሮች የሚከተሉትና ብዝሀነትን በአግባቡ የሚቀበልና የሚያስተናግድ በመሆኑ  እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ለሆኑ ሀገራት ሕብረ-ብሔራዊ የፌደራል ስርዓት አማራጭ የሌለው የአስተዳደር ስርዓት ነው፡፡

ሥርዓቱ የተለያየ ማንነት ባሕልና ታሪክ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ብዝሐነታቸውን እንደጠበቁ ለአንድ ዓላማና ለአንድ ሀገር እንዲሰሩ እድል የፈጠረ በመሆኑ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሎአል፡፡ በፌደራሊዝም ስርአቱ ውስጥ የተገኘው ሌላው ግዙፉ ድል በእርግጥ ታዳጊ ዲሞክራሲ ከመሆናችን አንጻር ወደፊት እያደገና ጥራቱን የጠበቀ ሁኖ እንደሚያድግ ቢታመንም ዜጎች የፈቀዱትን፤ ማንኛውንም አመለካከት የመያዝ፣ የመደራጀትና ኃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የፕሬስና የመናገር ሰብአዊ መብት በሕገ መንግሥቱ መረጋገጡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለዲሞክራሲ ማበብና ማደግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የፌደራል ስርአቱ አንዱና ትልቁ ድልና ስኬትም ይሄው ነው፡፡

በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ሳንሱር በሕግ የታገደበት፣ ግለሰብ ዜጎች ሕግን አክብረውና አሟልተው የራሳቸውን የግል ፕሬስም ሆነ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ለመክፈት ለመስራት የበቁበት፣ ቀድሞ በሀገሪቱ ያልነበረ ነጻነት ሲሆን  የፌደራሊዝም ስርአቱ ውጤት ነው፡፡ ይህንን ነጻነት በአግባቡ መጠቀምና ማሳደግ ደግሞ የዜጎች ኃላፊነትና ግዴታ ነው የሚሆነው፡፡

ሀገራችን አለምን ያስደመመ ፈጣን እድገት ባለቤት ለመሆን የበቃች ሲሆን ድሕነትን ከ54 ከመቶ ወደ 22 ከመቶ የቀነሰች፤ የምእተ ዓመቱን የልማት ግቦች በማሳካት ላይ ያለች፤ የአፍሪካ የኃይል ምንጭ እየሆነች የመጣችው፤ በመላው ሀገሪትዋ  ወደ 30ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ያደረገች ነች። ይህም ሊሆን የቻለው በአገራችን በተፈጠረው ሰላምና ለልማት በተሰጠው ትኩረት ሲሆን ይህም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያስገኘው  ውጤት በመሆኑ ሊመሰገን የሚገባው ነው፡፡

በሀገሪቱ ቀድመው የተሰሩና የተጠናቀቁት እንዲሁም የተጀመሩት ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለደረስንበት የኢኮኖሚ እድገት ማሳያ ሲሆኑ ሀገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ስኬታማ ጉዞ በማድረግ ላይ መሆኗን በተጨባጭ ያሳያሉ፡፡ ይህም የፌደራሊዝም ስርአቱ ያስገኘው ውጤትና ትሩፋት መሆኑ ለሰመርበት የግድ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy