Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ይህ ወቅት የሀይማኖት አባቶቻችንን እና የሃገር ሽማግሌዎቻችንን ይሻል

0 922

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ይህ ወቅት የሀይማኖት አባቶቻችንን እና የሃገር ሽማግሌዎቻችንን ይሻል

 

ዮናስ

 

የዛሬ  ሁለት አመት ግድም ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተከትሎ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በዜጎች መካከል የተፈጠረው መጠነኛ ግጭት ወደ ባሰ ብጥብጥና ግርግር በማምራት፣ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል፤ አሁንም እያስከተለ ነው። የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ደግሞ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች መሆናቸው እና በሕዝቡ ላይ ውጥረት ማንገሳቸው ነው። ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን እንቅስቃሴ በማወክ ተገልጧል።

 

እየተስተዋለ ያለው ግጭት በአብዛኛው በብሔር ስሜት ላይ የተቀናበረ ነው። ከአማራው፣ ከኦሮሞው የገዳ ሥርዓትና ከተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦቹ ቱባ ሕይወት መማር የተቻለ አይመስልም። የአገሪቱን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ግለሰቦች ግን ባሉት ችግሮች ስፋትና መጠን፣ በችግሮቹ መነሻና መፍትሔዎች ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን በማራመድ ላይ ናቸው። ይህ ተረክ ደግሞ ከካፌ በዘለለ ውይይት እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥም የሃገር ሽማግሌዎች ሚና ምን ሊሆን ይገባው እንደነበር እና የሃይማኖት አባቶችን ድርሻ የሚመለከት ነው።

 

መንግስት ልማቱን በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ነጋዴዎች ማፅዳት አለመቻሉ ዋነኛው የችግራችን ምንጭ ነው። በመሆኑም ያላግባብ መበልፀግ (ሙስና) ባህል ሆኗል። የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሰፍኗል፤ የውሸት ባህል ነግሷል፤ ለሆዱ ብቻ ያደረ ትውልድ ተፈጥሯል። አድሏዊነት፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነትና ጨቋኝነት ተንሰራፍቷል። ብሔርተኝነት ከመጠን በላይ ተለጥጧል። በሰላምና በፍቅር አንድ ላይ መኖር አልተቻለም። ሕዝብና መንግሥት የጥይት ጨዋታ ውስጥ ገብተዋል፤ ወጣቱ ተስፋ ቆርጧል። መግባባት፣ መደማመጥና መነጋገር ጠፍቶ መናናቅ መለያችን ሆኗል። የአብሮነት መንፈስ የሚባል ነገር ጠፍቷል። መንግሥት በሕዝብ ብሶትና እንባ ማትረፍ የሚሹትን ሰዎች አያውቅም ማለት አይቻልም። ስለዚህ በሕዝብ ስም የራሳቸውን ኑሮ ያመቻቹና የሕዝብን ገንዘብ በጆንያ የሚዘርፉ ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ለምን እንደማያመጣቸው ፈጽሞ ግልጽ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ በሥርዓቱ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ አብዛኞቹ ግለሰቦች (ሁሉም አይደሉም) ስለሆዳቸው እንጂ ስለሕዝቡ አሰቃቂ ሁኔታ የሚያስቡበት ሰዓትም ያላቸው አይመስልም። ይህ ደሞ በህዝብ ዘንድ አልተወደደም።

 

በሌላ በኩል ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያ ዓለም ያፈጠጠባት አገር መሆኗ ይታወቃል። ያፈጠጠባትም ምክንያት በእምነቷ የፀናች፣ ሕዝቦቿ ደግሞ ፈሪኃ እግዚአብሔር ያደረባቸውና በቀላሉ ሊፋቱ ወይም ሊበረግጉ የማይችሉ መሆናቸውን በመገንዘብ ነው። በዚህም የተነሳ ይህ ዓይነቱን ሕዝብ ከአሁኑ ካልቀየርነውና አንገቱን እንዲደፋ ካላደረግነው በስተቀር፣ ዋል አደር ካለ ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ የበላይነትን መንፈስ ሊላበስ ይችላል የሚል እምነት ያላቸው ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች እንዳሉና ዓላማቸውንም የሚያስፈጽሙ ቡድኖች መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ካለፈው ዓመት ጀምሮ እዚህም እዚያም የሚታዩት ግጭቶች የእነዚህ ኃይሎች ነፀብራቅ የሆኑ የውስጥና የውጭ እጆች እንዳሉበት መገመት አይከብድም። በዚህ ጊዜ ደግሞ የሃገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን ሚና ሊተካ የሚችል ሃይል የለም። በርግጥ የተጀማመሩ ነገሮች ያሉ ይመስላል። ግን በጣም የቀረ ምናልባትም የሌሎች መጠቀሚያ እንጂ የሃገር ሽማግሌነትን እና የሃይማኖት አባትነትን መርህና እሴት መሰረት ያላደረገም ይመስላል የሚሉ ወገኖች በርካታዎች ናቸው። ያም ሆኖ ግን የተጀማመሩ ነገሮች ስለመኖራቸው መካድ አይቻልም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነን ደግሞ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ነው።

 

በመከባበር የጎለበተው የኢትዮጵያውያን የወንድማማችነት እሴቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሰሞኑ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። ጉባኤው በመግለጫው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ከሀገሪቱ ውስን ሀብት፣ ከማስፈጸም አቅም ማነስና ከአሰራር ጉድለት ጋር የተያያዙ ችግሮች የተማረው ወጣት እንዳይረካ ማድረጉን አንስቷል። በዚህ እና ነባር ያልተፈቱ ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት እና አለመረጋጋት እንዲፈጠር መነሻ እንደሆኑም አስታውቋል። የሀይማኖት ተቋማቱ ከወጣቶች ጀርባ ሀገሪቱ ወደማያባራ ግጭት እንድትገባ የሚፈልጉ ሀይሎችም አጋጣሚዎችን በመጠቀም አለመረጋጋቱን በማባባስ ላይ እንዳሉ እና ህዝቡ ግንዛቤ ሊወስድ እንደሚገባም አሳስበዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወንድም በወንድሙ ላይ የፈፀመውን ኢሰብአዊ ድርጊትንም የሀይማኖት አባቶቹ በጋራ መግለጫቸዉ አውግዘውታል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የተስተዋለው ግጭት እና አለመረጋጋት በወቅቱ እልባት ካልተሰጠው በሀገር አንድነት ላይ የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ነው የሚለው መግለጫቸው፤ በመሆኑም ሁሉም በሚመለከተው ዘርፍ ሰላሙን ወደነበረበት ለመመለስ ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

 

ወጣቶችም ግጭትን ከሚያባብሱ ነገሮች በመቆጠብ ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጉባዔው ጥሪ ያቀረበው ጉባኤ፤ የፌደራል እና የክልል መንግስታትም ህዝቡን በማሳተፍ እና ለአስተዳደራዊ ጥያቄዎች በጊዜው እና በተገቢው መንገድ ምላሽ በመስጠት ችግሩን በአፋጣኝ እንዲፈቱ እና ህጋዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ነው የጠየቁት።

 

ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ወጣት ተማሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የመገናኛ ብዙሃን በሀገሪቱ የአንድነት ጉዳይ ላይ የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡም ጭምር የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂዎች ያሳሰቡ ሲሆን፤ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በየአጥቢያቸው በተለይ ለወጣቶች ስለ ሰላም እንዲያስተምሩም መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ከዚህ በላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል የሚለው የምእመናን ድምፅም ቀላል አይደለም።

 

ፈጣሪ ሁሉንም ሰው እኩል አድርጎ ፈጠረ እንጂ ብሄር መርጦ እንዲፈጠር አለማድረጉን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ይመሰክራሉ። ዘረኝነት በነብዩ መሀመድም በጣም የተወገዘ ከመሆኑም በላይ ሁሉም ሰው የየትኛውም ብሔር እና ቦታ ተወላጅ ይሁን በአላህ ዘንድ አንድ መሆኑም የእስልምና አስተምህሮ በደማቁ ያሰመረበት ጉዳይ ነው።  

 

ስለሆነም የሃይማኖት ተቋማትም ሆኑ አባቶች ከመግለጫ በዘለለ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ተማሪዎችን ለማረጋጋትና በእርስ በራሳቸው ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ሃላፊነት ወስደውና ወርደው ሊሰሩ ይገባል። ተማሪዎች  በስሜት ከመጓዝ ይልቅ በትዕግስትና ተቻችሎ በመማር ነገ በአንድ መስሪያ ቤት ተቀጥረውም ሆነ በሌሎች አማራጮች ሃገራቸውን የመገንባት ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑንም መምከርና መዝከር የነዚሁ አባቶችና ተቋማት ሃላፊነት መሆኑን አውቀው ወርደው  ቤት ለቤት ሊሰሩ ይገባል።

 

የሃገር ሽማግሌዎችም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ከእነርሱ በላይ ሃይልና አቅም ያለው አካል የሌለ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። በዚህም በተለያዩ  አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭትን ተከትሎ በወገኖቻቸው ላይ በደረሰው ሞትና መፈናቀል የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ከመግለጽ የዘለለ ስራም ሊሰሩ ይገባል። ለዘመናት ከኖሩበት ቤት-ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚኖሩ ዜጎች መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስቀምጥ ጫና ከመፍጠር ባሻገር፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና አካባቢዎች ተማሪዎችና ነዋሪዎች እያነሱ ያሉትን ጥያቄዎች በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ማቅረብና ምላሹ በትዕግስት መጠበቅ እንዳለባቸውም ሊመክሩና ሊገስጹ ይገባል። እየተፈጠረ ላለው የጸጥታ ችግርና የሰላም መደፍረስ እንዲሁም የብሔርተኝነት አስተሳሰብ በየደረጃው የሚገኘው አመራር አካላት ድርሻ ያላቸው መሆኑን መንግስት ገልጿልና እነርሱም በእነርሱ ጉያ እስከሆኑ ድረስ በቃችሁ ሲሉ ሊያወግዟቸው ግድ ይላል። ችግሩ የአንድ ወይም የሁለት ብሔር ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም የኢትዮጵያዊያን ችግር ነው፤ ለመፍትሄው ሁላችንም በጋራ መስራት ያለብን ቢሆንም የሃገር ሽማግሌዎቹ ድርሻ ደግሞ ከላይ በተመለከተው አግባብ የተለየ ነውና ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

 

ህብረተሰቡ ልጆቹን  የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አውቆ  የቤተሰቡን አስተሳሰብ በመግራት የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ ያለበት መሆኑን መምከርና መዘከር ከሃይማኖት አባቶችና ከሃገር ሽማግሌዎች በላይ የማንም ስራ ሊሆን አይችልም። በምንም ምክንያት ይሁን በተጋጩ ወገኖች መካከል እርቅ ማውረድ የእነዚህ አካላት ስራ ነው። ልዩነት ምንግዜም በመካከላችን ይኖራል። ነገር ግን ሁላችንም የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች ስለመሆናችን ማስተማር የነዚሁ አካላት ስራ ነው።  

 

ግጭቶቹ ሊፈቱ የሚችሉት ግጭቶችን በፈጠሩ ወይም በግጭቶቹ በተጠቁ ሰዎች ወይም በፖለቲካ ሳይሆን በእነዚህ አካላት ብቻ እንደሆነ ብዙዎች እየመሰከሩ ነውና የታሪክ ተወቃሽ ሳይሆኑ ከላይ በተመለከተው አግባብ ሊሰሩ ይገባል። ከዚህ ውጪ ግጭቶችን ለመፍታት ኃይል የምንጠቀም ከሆነ መፍትሔ ሳይሆን ሌላ ግጭት እንደምናመጣ ማስተማር አለባቸው። በባህላዊ ግጭት አፈታትም ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው ታዋቂ ግለሰቦች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወዘተ የመሳሰሉ ገለልተኛ ወገኖችን የመሰለ ባለድርሻ እንደሌለ ታሪካችንም ሆነ የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብት ይነግሩናል። የእነዚህ ወገኖች ተሳትፎ ያስፈለገበት ምክንያት እርስ በርስ ስለሚተዋወቁ፣ ጨቋኙንና ተጨቋኙን፣ ወይም ግጭት አነሳሹንና አቀጣጣዩንም ለይቶ የማወቅ ዕድል ስላላቸው እና ተሰሚ ስለሆኑም ጭምር ነው።

 

የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ከባድ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል። በተለይ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ሕዝቡ ጎራ ለይቶ እየተጨራረሰ ዝም የሚሉ ከሆነ፣ በፈጣሪና በሕግ ፊት ተጠያቂዎች ናቸው። እምነትና ፀሎት ብቻ በቂ አይደለም። ፍትሕ ሲጓደል እያዩ ዝም ማለት የለባቸውም። ከአገር ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ተልዕኮ እንጠብቃለን። ሰው መከበር ያለበት በተግባሩና በአስተሳሰቡ እንጂ በማዕረጉ አይደለም። ከሁሉም በላይ ለዚች አገር የሚያስፈልጋት ሰላም ነው። ሰላም! ሰላም! ሰላም! ዘላቂ ሰላም! ሰላም ደግሞ ሮናልድ ሬገን እንዳለው “ሰላም የግጭት አለመኖር አይደለም፣ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም ነው”፤ ይህ አቅም ያለው ደግሞ ከእነዚሁ የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች እጅ ላይ ነውና ብዙ እንጠብቃለን።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy