Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

          ግጭቶች እንዴትና በማን?

0 379

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

          ግጭቶች እንዴትና በማን?

                                                               ይልቃል ፍርዱ

በየትኛውም ሀገር የሚነሱ ግጭቶች የግጭቶቹ መነሻ ምክንያት አላቸው፡፡ ግጭቶችን ለመፍታት የግጭቶችን ስረመሰረትና ለምን ተነሱ? እንዴት ተነሱ? የሚለውን በመመርመር ነው መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው፡፡ የግጭት ተንታኞች እንደሚሉት ግጭት ግለሰብ ከግለሰብ፤ ግለሰብ ከቡድን፤ ቡድን ከቡድን፤ ድርጅት ከቡድን ሊጋጭ ይችላል፡፡ እነዚህ የሰውኛ የተፈጥሮ ባሕርይ ሆነው ኖረዋል፡፡ የሚነሱት ግጭቶች ግለሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበረሰባዊ ወይንም ቤተሰባዊ መነሻና ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡

በትንሹ የተነሳው ግጭት እየሰፋና መልኩን እየቀየረ ሲሄድ በሰው ሕይወትና በንብረት፣ በአካባቢ ብሎም በሀገር ሰላም ላይ ችግር ሊፈጥር፤ ግጭቶቹ በአጭሩ  ካልተፈቱ ደግሞ ያልተጠበቀ አደጋን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያው ሁኔታ በተረጋጋና በሰከነ መንገድ ለምን ግጭቶቹ ተነሱ? ገፊ ምክንያታቸው ምንድነው? የሚለውን ዋነኛ ሀሳብ በማንሳት በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑትን በግልጽና በቀጥታ በማነጋገር መሰረተዊ  ችግሩን ለይቶና አንጥሮ ማውጣት ነው፡፡ የምክንያቱ ምንነት ከተለየ መፍትሄ ለማስገኘት ቅርብ ነው ማለት ነው፡፡

ግጭቶችን በድርድር፣ በሽምግልና በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትና ዳኝነት ሁለቱንም ወገን በማነጋገር ዳግም ቁርሾ እንዳይዙ ችግሩ እንዳይከሰት አድርጎ በመፍታት የማያዳግም መፍትሔ ማስገኘት ይቻላል፡፡ ግጭቶች በሚከሰቱበት ቦታ በተለይ ደረጃው ከፍ ያለ ከሆነ በሀገርና በሕዝብ ሰላማዊ ሕይወት በመደበኛ ስራ በንግድ እንቅስቃሴውና በአጠቃላይም በሀገራዊ ምርትና ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ የግጭቶቹ አድማስ መስፋት የበለጠ ጉዳትን የሚያደርሰው በዜጎች ሕይወት ላይ ነው፡፡ ተጎጂው ከማንም በላይ ሕዝቡ ነው የሚሆነው፡፡ ግጭቶች መወገድ  ያለባቸውም ለዚህ ነው፡፡

በሀገራችን ከቅርብ አመታት ወዲህ እንግዳ በሆነ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት የሰላም መደፍረሶች ይሄንንም ተከትሎ የተፈጠሩት ግጭቶች በርካታ ከኋላ ያሉ ገፊ ምክንያቶችውን ማስተዋል ተችሏል፡፡ በዋነኛነት የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ ችግር፣  ሊገለጽ ከሚችለው በላይ የሙስና መንሰራፋት በሕዝብና በመንግስት ሀብት የከበሩና  የደለቡ ቡድኖችና ግለሰቦች መፈጠርና መንሰራፋት፤ ይሄንንም በተመለከተ በመንግስት በኩል ፈጥኖ እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉ ውሎ አድሮ መንግስት ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል፡፡

የጸረ ሙስና ትግሉን ለማኮላሸት በራሱ በመንግስት ጉያ ስር ተቀምጦ ቁልፍ ሚና ሲጫወት የቆየው ክፍል በየቦታው ገንፍለው ለወጡትና የሕዝብን ተቃውሞ ለቀሰቀሱት የግጭትና የሁከት መንስኤ ለሆኑት ሁሉ ዋነኛው አቢይ መነሻ ነው፡፡ ሕዝብ መብቴ ይከበርልኝ መብቴ ተነክቶአል ሲል ይህንን በጥሞና ማዳመጥ ችግሩን ከስሩ መመርመር መፍትሄ መስጠት የሚጠበቀው ከመንግሰትና ከመንግስታዊ ኃላፊዎች ነው፡፡

በእርግጥ መንግስት ከሙስና ጋር ተያያዥ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ግለሰቦች በሰሩት ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎችን ሰርቶአል፡፡ ይህ ጅምር እንጂ ገና ብዙ የሄደ አይደለም፡፡ እንደታየው በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በሙስና ላይ የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ትግል ትኩረቱ በሌላ ተተክቶ ድምጹ ጠፍቶአል፡፡ እያሰለሰም ቢሆን ትግሉ  መልሶ መቀጠሉ ግድ ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ የሚከሰቱ ግጭቶች ሀገራዊ ሰላምን ያውካሉ፤ የሕዝብን ሰላምና መረጋጋት ያደፈርሳሉ፤ በብዙ መልኩ ሀገራዊ ተጽእኖ ያስከትላሉ፡፡ ለዚህም ነው የግጭቶቹን መንስኤዎች በአግባቡ በማጥናትና በመለየት ፈጥነን መፍትሔ ማስቀመጥ ያለብን የምንለው፡፡

ግጭት ሲፈጠር ለምን ተፈጠረ ብሎ አካኪ ዘራፍ ማለት ሳይሆ፤ ትልቁ ነገር ፈጥኖ በውይይት፤ በድርድር፤ በሽምግልና፤ በሶስተኛ ወገን ዳኝነት ችግሮቹን መፍታትና ሰላም እንዲሰፍን ማድረጉ ላይ ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ ችግሮቹ ዳግም በማይከሰቱበት ሁኔታ መፍትሄ ማበጀቱ ነው ስኬታማ የሚያደርገው፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በድንበሩ አካባቢ የተነሳው አለመግባባት በቀላሉ ሊፈታ ሲችል እያደገ ሄዶ የብዙ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፎአል፤ ንብረት አውድሞአል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቅሎአል፤ ጉዳቱ ቀላል አልነበረም።

መንግስት ከመነሻው ጀምሮ ይህን ችግር ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ የሁለቱንም ክልሎች አመራሮች በጋራ በማነጋገር አልፎም የመንግስት ተወካይ ጉዳዩን በቅርብ በመከታተል መግባባት ላይ የተደረሰበት ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡

በመንግስት በኩል በሀገር ሽማግሌዎች እየተደረገ ያለው ተስፋ ሰጪ ሰላምን የማስገኘት ጥረት በተሳካ ሁኔታ መስመር በያዘበት ሁኔታ ውስጥ ያልተጠበቀ ግጭት በዛው አካባቢ ተከስቶአል፡፡ ጥያቄው የሚያርፈው እዚህ ላይ ነው፡፡ የመንግስትን የሰላም ጥረት ለማሰናከል ለምን ተፈለገ? ሰላማዊ መንገድ የያዘውን የሁለቱን ክልሎች ሰላም ዳግም ለማደፍረስ የተንቀሳቀሰው ኃይል የትኛው ነው? በእርግጥ ይህን ነውረኛ ድርጊት የፈጸመው ማነው? አላማውስ ምንድነው? የሚሉት ነጥቦች ሁሉ በጥልቀት መፈተሸ አለባቸው፡፡

ከመደበኛው ስሌት መውጣት አለብን፡፡ የኦሮሚያ ወይንም የኢትዮጵያ ሶማሎ ክልል ታጣቂ ነው ወይንም መከላከያ ገብቶ ነው የፈጸመው በሚለው ብቻ ከሄድን ትልቅ ስሕተት ውስጥ ከመግባታችንም ሌላ እውነቱን እንደ ሀገር እስክናውቅ ድርስ ከባድ ዋጋ ሊያስከፍልን ይችላል፡፡

ይህ ሀገራዊ ሰላምን የማደፍረስ ትልቅ ተልእኮ በግዛታችን ውስጥ ሰርገውና ጠልቀው ከገቡ የእኛን ሰላም መደፍረስና እርስ በእርስ መባላት አጥብቀው ከሚመኙት፤ ለዚህም ከሚሰሩት የአልሻባብ፣ የኦብነግ፣ የሻእቢያ፣ የግብጽ እጆች ከጀርባ የሉም ካልን ሙሉ በሙሉ ተሳስተናል፤ አሉ።

እንደሚታወቀው በክልሉ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት አካባቢውን ከአሸባሪዎች ለማጽዳት ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ታላቅ ተጋድሎ አድርጎአል፡፡ አብዲ ኤሌም የኦብነግ ኃይሎችንና አሸባሪዎችን ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ሆኖ በጽናት ታግሎአል፡፡ በዚህ የተነሳ የሀገራችን የምስራቅ ቀጠና ፍጹም የተረጋጋ ሰላም ተፈጥሮበት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌዎችና በኦሮሚያ ክልል በድንበር አካባቢ የተነሳውም ችግር ድሮም ይነሳ የነበረ ስለሆነ እንደተለመደው በሀገር ሽማግሌ አባቶች በእርቅ ሊፈታ የሚችል ነበር፡፡ ግን ሳናስበው አመለጠን፤ አሁንም ጊዜው ገና ነውና የተጀመረው መረጋጋት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ይህንን ሁኔታ ከጀርባ ሁኖ እያጋጋመና ግጭቱ ሳይበርድ እንዲቀጥል የሚያደርገው ኃይል ሰላም ወርዶ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ በተባለበት ሰአት ይህን ሰላም ያደፈረሱት ከእኛ ውጪ ያሉ ኃይሎች ቢሆኑስ? ብሎ መጠራጠሩ ሙሉ በሙሉ ተገቢ ነው፡፡ ለማንኛውም መንግስት እያደረገ ባለው ማጣራት ሁሉም ነገር ይደረስበታልና ችግር የለውም፡፡

በሶርያ ምድር የተመታው አይሲስ ሙሉ በሙሉ ጓዙን ጠቅሎ የገባው ሶማሊያ ምድር ነው፡፡ አልሻባብ ያለው ሶማሊያ ምድር ነው፡፡ በተለይም የአልሻባብ ተዋጊዎች እንደእኛው ሶማሌዎች መልካቸውም ቁመናቸውም አንድ አይነት ስለሆነ ለመለየት አስቸጋሪ ነው፡፡ የእኛን ሶማሌዎች መስለው የአልሻባብ፣ የኦብነግ፣ የአይሲስ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል በመዝለቅ በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ ይህ ቁጣ ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ በቀል ሊወልድ ይችላል፡፡

እንዲህ አይነቶቹ ነገሮች እንዲደረጉ ሻእቢያም ሆነች ግብጽ በዚሁ ቀጠና በኩል ቀደም ባሉት አመታት ብዙ ሞክረው እንደነበር መርሳት አይገባንም፡፡ ይህ ሀገራዊ ቀውስን ለመፍጠር ካላቸው እቅድ አንዱ አካል ነው፡፡ አሁን እርስ በእርስ ከመወነጃጀል መውጣት አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌዎችም ኦሮሞዎም ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሁለቱም የሀገራቸውን የሕዝባቸውን ሰላም ፈላጊ ናቸው፡፡ ታዲያ ማነው የሚያፋጀን? የሚያባላን? ከጀርባ ማንአለ? የሚለውን ጥያቄ በመመለስ በሕዝባችን ውስጥ ሰላም በመፍጠር ሀገራችንን ወደ ሰላምና መረጋጋት መመለስ አለብን፡፡

እንደሚታወቀው በምስራቅ በኩል ድንበራችን እጅግ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ  የውጭ ኃይሎች ወኪሎች ተመሳስለው ገብተው የሕዝብ ፍጅት በመፍጠር እርስ በእርስ መጋጨቱ እንዲሰፋ ሊያደርጉ ይችላሉ ብሎ መጠራጠሩ አይከፋም፡፡ በዘርና በጎሳ ላይ ያተኮረ ግጭት መቸም ሆነ መቼ ለኢትዮጵያ አይበጃትም፡፡ አይጠቅመንም፡፡ አንድም ሰው በተወለደበት ጎሳና ዘር ምክንያት ሊጠቃ ሊደበደብ ሊገደል አይገባም፡፡ ይህ እጅግ አደገኛ የሆነ ከኢትዮጵያዊነት እምነትና መንፈስ ተጻራሪ በሆነ አስተሳሰብ የቆመ  ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ዥንጉርጉርነት ነው፡፡ ሕብረ ቀለም፤ ሕብረ ባሕል፤ ሕብረ ኃይማኖት ሕብረ ብሔራዊነትን ያቀፈ ነው፡፡ በብዙ የተለያዩ ቀለማት ውበት የተመሰለች ናት ሀገራችን፡፡ ግጭቶች ሁሉ በውይይት በሽምግልና በድርድር መፈታትና መወገድ አለባቸው፡፡ እኛ እርስ በእርስ ስንባላ ሀገራችንን የጠላቶችዋ ሲሳይ እንዳናደርጋት በእጅጉ መጠንቀቅ አለብን፡፡ የእራሳችንን ችግር በእልህ በጀብደኝነት በስሜታዊነት በአካኪ ዘራፍ አይደለም የምንፈታው፡፡ በዚህ መንገድ መሄድ ከመረጥን ሀገሪቱን ለከፋ ውድቀት እንዳርጋታለን፡፡ የተፈጠሩ ስህተቶችን በእርጋታ ነቅሶ ማውጣት፤ በማንና እንዴት እንደተፈጠሩ በግልፅ መረዳት፣ ተጠያቂዎችን መለየት፤ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ፤ የሕዝቡን ሰላማዊ ሕይወት በተረጋጋ መንገድ እንዲቀጥል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሀገራችን የበዛ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy