Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጠ/ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሀገሪቱ የተወሰኑ አከባቢዎች የዜጎች ህይወት በማለፉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

0 980

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጠ/ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሀገሪቱ የተወሰኑ አከባቢዎች የዜጎች ህይወት በማለፉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ማቋቋሙንና የማጣራቱ ሂደት እንደተጠናቀቀም አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወሰድና የማጣራት ሂደቱን ውጤት ለሕዝቡ በዝርዝር እንደሚገለጽ ጠ/ሚንስትር ኃይለማርያም ተናግረዋል፡፡

የጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፡

የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች- እንደምን አመሻችሁ
በቅርቡ በተለያዩ የሐገራችን አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሐገራችንን ሰላም እና መረጋጋት የሚያውኩ ችግሮች ታይተዋል፡፡ በተከሰቱት ግጭቶች ምክንያት የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የህዝብ ሐብት እና ንብረት ወድሟል፡፡ እጅግ የምሳሳለትን የሰላም፤ የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግባንታ ሥራችንን የሚጎዱ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት መከሰቱ ይታወቃል፡፡ የፈዴራል መንግሥት ከሁለቱ የክልል መንግሥታት ጋር በቅርበት በመሥራት ችግሩ እንዲቀረፍ ያለሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ጉዳዩ እልባት ወደ ሚያገኝበት ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ነበር፡፡ ሆኖም በቅርቡ ግጭቱ እንደገና ያገረሸ ሲሆን በነጹሀን ዜጎቻችን ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳትና የሐብትና ንብረት ውድመት በማስከተል ላይ ይገኛል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ በድሮሎቢ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ ለደህንነታቸው ሲባል በአካባቢው በአቅራቢያ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች የጅምላ ግዲያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በራሴና በፌዴራል መንግሥት ስም በንጹሐን ዜጎች ላይ በደረሰው አዳጋ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተጎጅዎቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ለመላው የአገራችን ህዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ፡፡መንግሥት ድርጊቱን እያወገዘ ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ያቋቋመ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የማጣራቱ ሂደት እንደተጠናቀቀም አስፈላጊውን እርምጃ የሚወሰድ ሲሆን የማጣራት ሂደቱን ውጤት ለሕዝቡ በዝርዝር እንደምንገልጽ ከወዲሁ ለማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡ በተመሳሳይም በጨለንቆና ሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በአካቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ አጋጥሟል፡፡

በድጋሚ በመንግሥትና በራሴ ስም በዜጎቻችን ህልፈተ ሕይወት ምክንያት የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ለመላ የአገራችን ህዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ የጸጥታ ኃይሎቻችን መንግሥት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰላምን እንዲያረጋግጡ ተልዕኮ ሰጥቷቸው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የጨለንቆን ግጭት ጨምሮ ተልዕኳቸውን እየፈጸሙ ባሉበት ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶች ካሉ አሰራሩን ተከትሎ መንግሥት የሚጣራ ሲሆን፣ የማጣራቱ ሂደት እንደተጠናቀቀም ውጤቱን ለሕዝቡ በዝርዝር ይፋ የምናደርግ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

በተጨማሪም በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ አንዳንድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ እንዲሁም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ክቡር የሰው ህይወት መጥፋቱ፤ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው እና የዜጎች ሐብት እና ንብረት መውደሙ ብቻ ሳይሆን፤ ችግሩ በፍጥነት ካልተወገደ እንደ ሐገር አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሊጥለን የሚችል ነው፡፡

በመሆኑም፤ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በቦረና፣ በጉጂና በባሌ የተለያዩ አካባቢዎች እና በቅርቡም ጨለንቆ አካባቢ በተከሰተው ግጭት፤ እንዲሁም በአዲግራት፣ በወለጋ፣ በደብረ ታቦር፣ በወልድያ፣ በባህርዳር፣ በጎንደር እና በአምቦ ዩኒቨርስቲዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በተማሪዎች የአካል ጉዳት መድረሱ እና በአንዳንዶቹም የሰው ህይወት መጥፋቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ህይወታቸውን ባጡ ተማሪዎች የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተማሪ ወላጆችም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ትምህርትን በፍትሐዊነት ለማዳረስ እና የተማሩ ዜጎችን ቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከ50 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተው፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እነዚህ የሐገር ተስፋ ተደርገው የሚታዩ የትምህርት ተቋማት የሚታዩ አስተዳደራዊ ችግሮችን እና ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ሌሎች ችግሮችን በማዳመጥ መፍትሔ ለማስቀመጥ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተጠቀሱት ዩኒቨርስቲዎች ተከስቶ የነበረው ችግር የክልል እና የፌዴራል መንግስታት፤ እንዲሁም የየዩኒቨርስቲዎች አመራሮች እና የየአካባቢው የመስተዳድር አካላት፤ ከተማሪዎች፣ ከሐገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች እና የጸጥታ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ችግሩ ተወግዶ፤ ሁኔታዎች ተረጋግተው የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ተችሏል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠረውን ይህን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ችግር በተፈጠረባቸው የትምህርት ተቋማት በተማሪዎች ዘንድ የተፈጠረውን የደህንነት ሥጋት ለማስወገድ እና ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በተቋማቱ የሰዓት እላፊ ገደብ እንዲኖር፣ የተቋማቱን ሰላም ለማስከበር የጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እንዲኖር ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ በክፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ ችግር አንዳይኖር፤ የዜጎች ህይወት ዋስትና እንዲያገኝ እና በዜጎች ሐብት እና ንብረት ላይ የሚደርስ ውድመት እንዳይኖር ለማድረግ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግላችንን የሚጎዱ፤ ሐገረችንን ወዳልተፈለገ አለመረጋጋት ውስጥ የሚከቱ እና በመራራ ትግል የተገኘውን ብሩህ ተስፋ የሚያጨናግፉ ክስተቶች ናቸው፡፡ ለዘመናት የቆየ የአብሮ መኖር እሴቶቻችን የሚጎዱ ችግሮች በመሆናቸው መንግስት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ችግሮቹን በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡

ለዘመናት በድህነት የኖረውን ህዝባችንን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት እና ከኋላ ቀርነት ለማለቀቅ፤ እንዲሁም የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጥረታችን ለማጠናከር በማሰብ፤ በከፍተኛ ወጪ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች የተገነቡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ የሐገራችንን ህዝብ ችግር ለመፍታት በጥናት እና ምርምር ዘርፍ ተሰልፈው የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ታስበው ከፍተኛ ገንዘብ ፈሶባቸው የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ተቋማት ገብተው የሚማሩ እና ሐገሪቱ በከፍተኛ ተስፋ የምትጠብቃቸው ተማሪዎች ምክንያታዊ አስተሳሰብን በመከተል፣ ከግጭት በመራቅ ለሐገራቸው ተስፋ ይሆኑ ዘንድ ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው ጠንክረው መማር ይኖርባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ መረጃን በማሰራጨት ተግባር የተሰማሩ የተለያዩ አካላት የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት መስጠት እና በኃላፊነት መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ህዝቡ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የሚያገኛቸውን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥና መረጃዎቹን በተለያየ አግባብ ለማጣራት የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በመደበኛው የሚዲያ ዘርፍም ሆነ በሌሎች የመረጃ ማሰራጫ አግባቦች በመጠቀም መረጃን የሚያሰራጩ ተቋማት ህግን አክብረው ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ ሐሰተኛ እና የተጋነኑ መረጃዎችን በማሰራጨት የህዝቡን ሰላም፣ ደህንነት እና አኩሪ የአብሮ መኖር እሴቶች የሚንዱ እና ህግን በሚያስተላልፉ የግልም ሆነ የህዝብ የመገናኛ ብዙሃን ከዚህ መሰል ተግባራት መራቅ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግስት እንዲህ ያሉ ችግሮችን በሚፈጽሙት ላይ ተከታትሎ እርምጃ የሚወስድ መሆኑም በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች እያጋጠሙ ያሉትን ግጭቶች መሰረታዊ መንስኤን በመለየት ችግሩን ከሥር መሰረቱ የሚፈታ እርምጃ የሚወስድ ሲሆን መላ የአገራችን ሕዝቦችም እንደ ወትሮው ከመንግሥት ጎን በመቆም ያልተቆጠበ ድጋፋችሁን እንዲትቸሩን በመንግሥትና በራሴ ስም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ በተለይም ግጭቱ በሚከሰትባቸው የኦሮሚያና የኢትዮጰያ ሶማሌ ክልል ነዋሪ የሆኑት ወንድማማች ሕዝቦች ለሰላምና ለወንድማማችነት ቅድሚያ በመስጠትና ለግጭት ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በጋራ በመንቀሳቀስ ሰላማቸውን እንዲያስከብሩ በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ጥሪዬን እያቀረብኩ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በቅንጅት ችግሩን ለመቅረፍ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
በድጋሚ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች ሳቢያ በዜጎቻችን ላይ በደረሰው የሞት አደጋ የተሰማኝን መራር ሐዘን እየገለጽኩ፣ ለመላ ቤተሰቦቻቸው፣ ዘመድ አዝማዶቻቸውና ለአገራችን ሕዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy