Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝባዊ መሰረት የሌላቸው ተግባሮች

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝባዊ መሰረት የሌላቸው ተግባሮች

                                                         ደስታ ኃይሉ

በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የሚካሄዱት ህገ ወጥ ተግባሮች ጥቂቶች ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉት ጥረቶች አካል ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ፀረ ህዝብ እንቅስቃሴ ህዝባዊ መሰረት የለውም።

የአገራችን ህዝቦች እንኳንስ ዛሬ በጋራ ተስማምተው ባቆሙት ሕገ መንግስት እየተዳደሩ ይቅርና ድሮም ቢሆን አንዱ ብሔር ሌላውን በጥላቻ የመመልከት ባህል የሌላቸው ናቸው። በመሆኑም ዜጎች እነዚህን ህዝባዊ መሰረት የሌላቸውን ተግባሮች በማውገዝ የሀገራቸውን ሰላም አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል። በተለይ ወጣቱ የእነዚህ ሃይሎች ሰለባ ላለመሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ይህን የሰው ሃብታቸውን በአግባቡ ከተጠቀሙ ሃብቱ የዕድገታቸው ምንጭ መሆኑ አያጠያይቅም። ከሀገራችን ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይታወቃል። ይህን አፍላና ሁሉንም ነገር የመፈፀም ባህሪያዊ ተፈጥሮ ያለውን ወጣት በልማት ስራ ላይ ማሰማራት ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

ይህን ሃቅ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት ወጣቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን በማደራጀት ራሳቸውን ጠቅመው የሀገራቸውን ዕድገት እንዲደግፉ ማድረግ ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም ወጣቱ በልማት ስራው ላይ እንዲሳተፍ በፌዴራል መንግስት ደረጃ የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦ ወጣቱን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል። በዚህም ውጤት እየተገኘበት ነው።

ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮችም ከዚህ የፌዴራል መንግስት ፈንድ በተጨማሪ፤ ከራሳቸው በጀት መድበው ወጣቱ በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ችለዋል። በተያዘው የበጀት ዓመትም በዋነኛነት ለወጣቱ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ መግለፃቸው ይታወቃል። ይህም መንግስት እዚህ ሀገር ውስጥ ላሉ ወጣቶች ምቹ የልማት ተግባሮችን እያከናወነ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ይህ ለወጣቱ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሀገራችን ለወጣቶቿ፣ ወጣቶቹም ለሀገራቸው እንዲጠቅሙ ከማሰብ የመነጨ ነው።

እርግጥ ወጣቱ ለአገሩ ሰላም መሆን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ይታወቃል። በመሆኑም የእነዚህን ፀረ ህዝብ ሃይሎች ዓላማና ግብ በሚገባ መረዳት ይኖርበታል። ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ የትኛውንም የሀገራችንን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ሊወክሉም አይችሉም። ምክንያቱም ዓላማቸውና ግባቸው ከበስተኋላቸው የሚደጉማቸውን ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይል ፍላጎት ማስፈፀም ብቻ ስለሆነ ነው።

የእነዚህን ሃይሎች የአመፅ አቀጣጣይነት ፍላጎትን መረዳት ከወጣቱ የመኪጠበቅ ተግባር ነው። እውነታውን ከራሱ እማኝነት በመነሳት መገምገምም አለበት። አንድ ጉዳይ በፌስ ቡክ ዓይነት ማሀበራዊ ድረ ገፅ ብቻ ስለተነገረ እውነት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም።

ሆን ተብሎ የሀገራችንን ሰላም ለማወክ በፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች እንደሚቀነባበር መረዳት ያስፈልጋል። እናም ፀረ ህዝብ ኃይሎቹ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ስላለው ህገ መንግስታዊ ልዩ ተጠቃሚነትም ይሁን በየትኛውም ሀገር መንግስት ስራውን ለማከናወን የሚሰበስበውን ግብር አስመልክተው የሚያራግቡት አሉባልታ ቅስቀሳ መነሻውም ይሁን መድረሻው ይኸው ኢትዮጵያን የማተራመስ ተልዕኮ መሆኑን ወጣቱ ማወቅ ይኖርበታል። ማወቅ ብቻም ሳይሆን፤ የእነርሱን ማንነት በመገንዘብ ሊታገላቸውና ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፍ ይገባል።

የሀገራችን ወጣት ባለ ራዕይና ተስፋ ያለው ነው። የዛሬው ትውልድ ወጣት እንደ ትናንቱ ወጣቶች እየታፈነ ለጦርነት አይወሰድም። ይህ ወጣት ዛሬ “ሰርተህ ተለወጥ፤ እኔ የምትሰራበትን ምህዳር አመቻችልሃለው” የሚል መንግስት ባለቤት ነው። ችግሩን በህዝባዊ መንፈስ የሚጋራው መንግስት አለው። መፍትሔም በአፋጣኝ የሚሰጥ መንግስት አለው። በየዕቅዶቹ ሁሉ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ትልሞችን የሚይዝ መንግስት ባለቤትም ነው።

እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ችግሮች ይኖራሉ። እንኳንስ ለልማቱም ይሁን ለዴሞክራሲው ጀማሪ የሆነችው ሀገራችን ቀርቶ ባደጉት ሀገሮችም ውስጥ ቢሆን ችግር መኖሩ አይቀርም። የአልጋ በአልጋ መንገድ በየትኛውም ሀገር ውስጥ የለም። በመንግስት የስራ አስፈፃሚዎች ውስጥ ችግር ሊኖር ይችላል።

ዋናው ጉዳይ ችግሩን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንጂ የራሳቸው አጀንዳ ሳይኖራቸው የባዕዳን ተላላኪ በመሆን የፈጠራ ወሬን በሚረጩ ፀረ-ሰላም ሃይሎች አማካኝነት አይደለም። በመሆኑም በአንድ ተግባር ላይ ከመሳተፍ በፊት ጠለቅ አድርጎ ጉዳዩችን መገንዘብ ያስፈልጋል እላለሁ።

በሌላ በኩልም ወጣቶችን ከጥፋትና ካላስፈላጊ ተግባሮች እንዲታቀቡ ወላጆች ጠንካራ ሚናቸውን ሊጫወቱ ይሀገባል። እንደ ህዝብ ሆነውም የሀገራቸው ሰላም በአሉባልታ እንዳይደፈርስ የዜግነት ድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው።

ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሰለፉ ሃይሎችን ተግባር እንደ ዜጋና እንደ ህዝብ መገንዛብ ያስፈልጋል። እርግጥ የእነዚህ ሃይሎች ፍላጎት፤ የሰላም ሳይሆን የብጥብጥና የሁከት፣ የመብት ተጠቃሚነት ሳይሆን የመብት አዋኪነትና የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሁሉም በየደረጃው የሚጠቀምበት ሳይሆን የዜሮ ድምር ፖለቲካ መጫወትን የመከባበርና የመቻቻል ሳይሆን የጠባብነትና የትምክህተኝነት እንዲሁም የነጻነት መንገድ ሳይሆን የባርነት ቀንበር መሆኑን ለዚህ ኩሩ፣ ሰላምና ልማት እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት ፈር ቀዳጅ ለሆነ ህዝብ መንገር አይቻልም—እነርሱ የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ በተማሪዎች ለልማት በመትጋት ላይ በሚገኘው ወጣት እጅ እሳት ለመጨበጥ በበሞከር ከስሮ የወደቀ ፖለቲካቸውን ለማንሰራራት የሚከጅሉትን ፀረ-ሰላም ሃይሎችን ማንነት በሚገባ የሚያውቀው ዕውነታ ነውና።

በመሆኑም በሂደት እንደ አሜኬላ እሾህ ከመሃሉ እየነቀለ በማውጣት ህግ ፊት ማቅረቡ የሚቀር አይመስለኝም። ምክንያቱም በሀገር አቀፍ ደረጃም ይሁን በክልሉ እየተመዘገበ ካለው ባለ ሁለት አሃዝ ፈጣንና ተከታታይ ልማታዊ ዕድገት ተጠቃሚነቱ እንዲስተጓጎልበት አይሻም። እናም በአሸባሪዎችና በፀረ-ሰላም ሃይሎች አሉባልታ እንደ ቦይ ውሃ የሚነዳ ህዝብም ሆነ መንግስት አለመኖሩን ማወቅ የሚገባ ይመስለኛል።

ታዲያ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላሙ ባለቤት የሆነው ህዝብ፤ የፀረ-ሰላምና ፀረ ህዝብ ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ የሚታወቅ ነው። እያንዳንዷ ሰከንድ ለሰላም ያላትን ፋይዳ ስለሚገነዘብ ነገም ሆነ ከነገ በስቲያ ፀረ ህዝቦችንና ላኪዎቻቸውን በቂ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል ነው። አሁንም ወጣቶች ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እንዳያመሩ መምከርና መገሰፅ የሚጠበቅበት ይመስለኛል።

የዚህ ሀገር ህዝብ ከጥፋት ምንም እንደማይገኝ ጠንቅቆ ያውቃል። ብሔር ከብሔር ጋር እንዲጋጭ የሚሰሩ አሉባልታ ነፊዎችንም አሳምሮ ያውቃቸዋል። ተግባራቸውም ከማደናገር ውጭ ህዝባዊ መሰረት እንደሌለው ይገነዘባል። በመሆኑም አንዱን ከሌላው ጋር የሚያባሉ ህዝባዊ መሰረት የሌላቸውን ተግባሮች እየለየ ሊታገላቸው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy