ህገ ወጥ ስደትን የመከላከል ጥረት
ደስታ ኃይሉ
በአሁኑ ሰዓት ህገ ወጥ ስደት የዓለማችን ብሎም የአገራችን አሳሳቢ ችግር ሆኗል። በሰው ልጅ ታሪክ እጅግ አስከፊ የሚባለው የባርያ ፍንገላ መገበያያ እየሆነ ነው። ይህን አስከፊ ስደትን ለመከላከል የኢፌዴሪ መንግስት በርካታ ተግባሮችን አከናውኗል። በተለይም በየአካባቢው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን በማስፋፋት የጉዳዩ ሰለባ እየሆነው ያለው ወጣት በአቅራቢያው የገንዘብ አቅርቦት እንዲያገኝ በማድረግ ወጣቱ በሀገሩ ውስጥ ሰርቶ እንዲለወጥ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
ይህ በአቅራቢያ የፋይናንስ ግኝትን የመፍጠር መንግስታዊ ስራ የጉዳዩ ሰለባ የሆኑ ወጣቶች በአገራቸው ውስጥ ሰርተው እንዲለወጡ፣ ራሳቸውንና አገራቸውን ይበልጥ እንዲጠቅሙ ከማሰብ የተደረገ ነው።
ዛሬ በርካታ ወጣቶች መንግሥት ባመቻቸው ሁኔታ በአገራቸው ውስጥ ሰርተው ማደግና መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሃብት ማፍራትና ጥሪት መቋጠርም ችለዋል። መንግስት ባመቻቸላቸው ሰፊ የስራ መስክ ውስጥ በመሰማራትም ራሳቸውንና ሀገራቸውንም እየጠቀሙ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በርካታዎችም የሚሊዩነርነት ጎራን በመሰለፍ ለሌሎች ወገኖቻቸው የስራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ይሁንና ከዚህ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለየ መልኩና በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ የሚቻልበት መንገድ እያለ ስደትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ዜጎች መኖራቸው የሚታበይ አይደለም። እርግጥ ህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር የሁሉም ታዳጊ ሀገሮች ችግር ነው። እናም ሀገራችንም በችግሩ ከሚጠቁት መካከል አንዷ እንዲሁም የድርጊቱ መነሻና መሸጋገሪያ ናት። በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው ህገ- ወጥ የስዎች ዝውውር ወይም ስደት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የዜጎቻችን መዳረሻ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል።
የህገ-ወጥ ዝውውሩ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ወጣት ሴቶችና ወንዶች በመሆናቸው በቀላሉ ለችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እነዚህ ዜጎች ውጭውን እንጂ ውስጣቸውን በቅጡ ማማተር ያልቻሉ ይመስለኛል። በዓለማችን ካለው የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሳቢያ የትኛውም ሀገር ማርና ወተት የሚዘንብበት አለመሆኑን በበቂ ሁኔታ የተገነዘቡ አይመስለኝም። እርግጥ በህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ከፊል ዕውነታ ያለው እሳቤ ሊሆን ይችላል። የተሟላ አስተሳሰብ ነው ማለት ግን አይቻልም።
እርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት ይገባኛል። ይሁንና የችግሩ መንስዔ ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻሉና እዚሁ ሀገር ውስጥ ሰርተው መበልጸግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለህገ-ወጥ ደላሎች ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ የትየለሌ በመሆኑ ነው፡፡
በላቡና በወዙ ጥሮ…ግሮ ህይወቱን ለመለወጥና ሀገሩን ለመጥቀም የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ዜጎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያስቆጭ ነው። ከዚህ ባሻገርም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና መለወጥ ሲቻል ህገ- ወጥ አካሄድን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ አግባብነት ያለው ተግባር አይመስለኝም።
እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። ዕድገቱም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ልማታዊ ሥራዎች ላይ በመሳተፋቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ለመዳን ችለዋል። እንዲያውም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም እየረዱ ነው። ይህ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሃቅ ነው።
እንደሚታወቀው ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡
በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።
ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው።
እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም።
ዜጎች በተለይም ወጣቶች መንግስት የቀየሰውን አዲስ የስራ ባህል በተግባር በመተርጎምና ያገኙትን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር ለመሆን የበቁ ዜጎቻችን ሊፈጠሩ ችለዋል። በአንፃሩ ደግሞ ለጥቂት አፍራሽ ሃይሎች አሉባልታ ተንበርክከውና ወደ ውጭ በማየት የማያውቁትን ሀገር ሲናፍቁ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖች ቁጥርም ቀላል አይደለም።
እርግጥ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅቶ በሀገር ሰርቶ ማደግና መለወጥ እየተቻለ የአጭበርባሪ ደላላዎች ሲሳይ ሆኖ ለችግር መጋለጥ አሳዛኝ ቢሆንም፤ አሁንም አልረፈደምና ዕውነታውን መገንዘብ ያስፈልጋል።
የውጭው ዓለም ወተትና ማር አያዘንብም። ተለፍቶ፣ ተደክሞና ተጥሮ የሚኖርበት ነው። ግን ይህ የሚመስላቸው ወገኖች በሚያካሂዱት ቅስቀሳ ለህገ ወጥ የሰው ዝውውሩ አለመቅረት ምክንያት ሆኗል።
ይሁን እንጂ አገሪቱ ድህነትን ለማስወገድ የምታካሂደውን ጥረት ለማደናቀፍ በሚደረግ የተሳሳተ ቅስቀሳ ስለባ ሆነው ውጪውን እንዲያማትሩ የተገደዱ ዜጎች ዛሬም ድረስ በርካታ ናቸው። የሚደርስባቸውን እንግልትና ስደት እያወቁ እንኳን ወደዚያው ከማምራት አይቆጠቡም።
ታዲያ እነዚህ ዜጎችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሃይሎች ከመኖራቸው በተጨማሪ፤ የዜግነት ርህራሄ ያልፈጠረባቸው ወገኖችም ችግሩን ዛሬ ላይም ቢሆን አሳሳቢ እንዲሆን ማድረጋቸው አልቀረም። እዚህ አገር ውስጥ መንግስት ወጣቶቭች እንዲበረታቱና ወደ ስራ እንዲገቡ በየቀያቸው የፋይናንስ ተቋማትን አቋቁሟል። ይህ ጥረቱ ዜጎች አገራቸው ውስጥ የሚያጥራቸውን የፋይናንስ ግኝት በአቅራቢያቸው አግኝተው ወደ ስራ በመግባት ለውጥ እንዲያመጡ ከማሰብ የመነጨ ነው። በመሆኑም በተለይ ወጣቱ ውጭውን ማማተር ትቶ በአገሩ ውስጥ በመስራት የነገ ሰውነቱን ማረጋገጥ ያለበት ይመስለኛል።