Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለህዝባዊ ወገንተኝነትን የተንበረከከ ድርድር ያሻናል

0 425

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለህዝባዊ ወገንተኝነትን የተንበረከከ ድርድር ያሻናል

ዮናስ

በ2008 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍሎች ከተቀሰቀሰው አመጽ በኋላ በተከፈተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ንግግር ለማድረግ የተገኙት ዶ/ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፤ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት እስከ ማሻሻል የሚደርስ ተሃድሶ መንግሥት እንደሚያከናውን በገቡት ቃል መሰረት የተጀመረው ድርድር ሲወድቅ ሲነሳ፣ ሲደገፍ ሲጣጣል፣ ሲሞካሽና ሲብጠለጠል በርካታ ወራትን ካስቆጠረ በኋላ ከሰሞኑ አብላጫን እና ተመጣጣኝ ውክልናን በሚቀላቅለው ቅይጥ የምርጫ ስርአት ላይ በመስማማት ከባዱን ዳገት የወጡት መስለዋል። ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በምክር ቤቱ ተገኝተው በፕሬዝዳንቱ ንግግር ላይ ለቀረበው ማሻሻያ ሞሽን ለምክር ቤቱ አባላት ባብራሩበት ወቅት፣ መንግሥት ከሚያከውናቸው ዓበይት ተግባራት መካከል የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት ማሻሻል አንዱና ዋነኛው እንደሚሆን በገቡት ቃል መሰረት የተከናወነ ነው።

በዚሁ መሰረት በአጠቃላይ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓትና ሕጎች፣ እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ አዋጆችና ሕጎች ላይ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር በመደራደር ላይ የሚገኙት 15 አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁን የተወሰኑ አንቀጾች ለማሻሻል ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይፋ ሆኗል።

በድርድር ኮሚቴው በኩል የወጡት መረጃዎች እንዳመለከቱት በድርድሩ እየተሳተፉ የሚገኙት አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ ላይ መሻሻል አለባቸው ያሉዋቸውን፣ እንዲሰረዙ የሚፈልጉትንና እንደ አዲስ እንዲካተቱ የሚፈልጉዋቸውን ነጥቦች አቅርበዋል። በዚህም መሠረት ለዚሁ ድርድር ዓላማ ሲባል አንድነት የፈጠረው የ11 ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ 39 አንቀጾችን ካካተተው አዋጅ ውስጥ፣ 11 እንዲሻሻሉ፣ አራቱ እንዲሰረዙና ሁለት ሌላ አንቀጾች እንዲጨመሩ በድርድሩ ወቅት ያቀረበ ሲሆን፤ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ደግሞ ሃያ አንድ አንቀጾችና ንዑስ አንቀጾች እንዲካተቱ፤ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) በበኩሉ አሥር አንቀጾችና ንዑሳን አንቀጾች እንዲሻሻሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ግን በአዋጁ ላይ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሐሳብ እንዳላቀረበ የጠቆሙት እኒህ መረጃዎች፤ ከአገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሻሻሉ የቀረቡት በዋነኛነት ብሔራዊ የጋራ ምክር ቤት አወቃቀር፣ ፓርቲዎች ስለሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ፣ እንዲሁም ፓርቲዎቹ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸውን ሚና ስለሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ስለመሆናቸው አመልክተዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላው እንደ አዲስ እንዲካተት ያቀረቡት ሐሳብ ደግሞ፣ የምርጫ ውጤት የማሳወቅ ኃላፊነት ለታዛቢዎች ይሰጥ የሚለው ቢሆንም ኢሕአዴግ ግን ውድቅ አድርጎታል። ኢሕአዴግ ለዚህ ያቀረበው ምክንያት የምርጫ ታዛቢዎች ድርሻ መጠሪያቸው እንደሚያመለክተው መታዘብ ብቻ  ነው የሚል ነው። ይህን ሐሳብ ውድቅ ቢያደርም ግን በአብዛኛው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው ሐሳቦች ጠቃሚ ናቸው በማለት፣ በሕግ አሠራር ታይተው ሊሻሻሉ እንደሚችሉ ኢሕአዴግ ማስታወቁም ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራሮች መካከል ከገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር እየተደረገ ባለው ድርድር ምክንያት አለመግባባት መፈጠሩን የተመለከቱ መረጃዎች የፓርቲው የጥናትና ምርምር ኃላፊ በሆኑት አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ በኩል ወጥተዋል። አለመግባባቱ የተፈጠረውም በድርድሩ ሒደት ደስተኛ ያልሆኑ የፓርቲው አባላት የፓርቲውን ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/) አንስተው፣ አቶ አዳነ ታደሰን ፕሬዚዳንት አድርገው መምረጣቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ማሠራጨታቸውን ተከትሎ መሆኑም በመረጃው ተመልክቷል።

የጸቡ መንስኤ ምንም ይሁን ምን፤ የትኛው ትክክል የትኛው ደግሞ ቀጣፊ መሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይጠቅምም። የኢትዮጵያ ሕዝብን መነሻ አድርገው ከተቋቋሙ ፓርቲዎች ህዝብ የሚፈልገው አማራጭ ሐሳቦችን ይዞ ለተሻለ ሃገር የሚደራደረውን እና የሚሟገተውን ብቻ ነው። ተቃዋሚዎቹ እስካሁን የሄዱበት ግለሰቦችን ያማከለ መንገድ የትም የማያደርስ እንደሆነ ህዝቡ አሁን በሚገባ ተገንዝቧል። ህዝብ አሁን የሚፈልገው ለሰላሙ፣ ለልማቱ እና ለሃገሪቱ  የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚበጀውን በአማራጭ ሐሳቦች የተደራጀ ድርድርን ብቻ ነው። ዴሞክራሲ የሐሳብ ገበያ ነው የሚባለው፣ ለአገር እስከጠቀመ ድረስ ማንኛውም ሰው የሚሰማውን ማንፀባረቅ ስለሚችልበት እንጂ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል ከሚሉት ጋር ለመጓዝ አይደለም። በድርድር ሂደቱ ላይ  ተቃራኒ ሐሳብን ላለማዳመጥ ሲባል ብቻ ማናናቅን ወይም በኃይል ገለል ማድረግን መርሃቸው ያደረጉ ሃይሎችን ህዝብ አይፈልግም። በድርድሩ ላይ የሚወጡና ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ሐሳቦችን ቀጭተው ለእነርሱ ብቻ የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ለማራመድ የሚተጉ ሃይሎችን ህዝብ አይፈልግም።  

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እኔ ብቻ የምፈጥረው አንዳች ነገር የለም ብሎ ወደተቃዋሚው ለመጣበት መንገድ ዋጋ ሰጥቶ መደራደር ህዝባዊ ወገንተኛ ከሆነ የትኛውም ፓርቲ ይጠበቃል።  

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በጣም በርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ እምነቶች ወዘተ ያሉባት የብዝኃነት አገር መሆኗን መነሻ በማድረግ፤ ይልቁንም በዚህች ብዝሃነት ባለባት አገር ውስጥ በአንድ ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ አገር መምራት የማይቻል መሆኑን በመረዳት በራሳቸው መንገድ ሊመጡ ያልቻሉ ሃይሎች የሚመጡበትን መንገድ ላመቻቸ የድርድር ጉዳይ ዋጋ መስጠት ከምንም በላይ ህዝብን ማክበርና በእርግጥም ህዝባዊ ወገንተኝነትን ማረጋገጥ ነው። የሐሳብ ብዝኃነት ባለው ሕዝብ ውስጥ የእኔ ወይም የኛ ብቻ ነው ትክክል የሚለው አካሄድ ጤናማ አይደለም። ይህ አካሄድ በግልም ሆነ በቡድን ሐሳቤ ተወክሎልኛል ለማለት የማይደፍር ኅብረተሰብ ፈጥሯል። ይህ ማብቃት አለበት። ይህ እንዲያበቃ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ምኅዳሩ የሚስተካከልበትን የድርድር እርምጃ ወስዷል። በተቃውሞው ጎራ ውስጥ ያሉት ደግሞ የጠነዛና የማይረባ ትርክታቸውን ትተው ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ በሚያበቃ ቅኝት ውስጥ ሆነው ሊደራደሩ ይገባል። ከጅምላ ፍረጃና ከእኛ በላይ ለአሳር ከሚባልለት ነጋሪት ጉሰማ በመውጣት ለሐሳብ ብዝኃነት ሊታገሉ ይገባል። ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የተለያዩ ሐሳቦች በሚያደርጉት ግልጽ፣ ነፃና ፍትሐዊ ውይይትና ድርድር እንጂ በጉልበት ወይም በጩኸትና ክስ አይደለም።  

በአጠቃላይ ነፃ ማኅበረሰብ የሚፈጠረው ለነፃነት ትርጉም ያለው አማራጭ ይዘው ለውይይትና ድርድር ክፍት የሆኑ ፓርቲዎች ሲኖሩ ነው። ሐሳቦች በነፃነት ሲወዳደሩ መራጩ ሕዝብ የተሻለውን ለመምረጥ ዕድሉን ያገኛል። ለዚህ ደግሞ ነፃና ግልጽ የሆነ የፓርቲዎች ውይይትና ድርድር  መኖር አለበት።  ፓርቲዎች ህዝብን ታሳቢ  አድርገው መወያየትና መከራከር ሲችሉ ሐሳቦች እንደ ጅረት ይፈሳሉ። ፓርቲዎች አሉን የሚሉዋቸውን አማራጮች ለማቅረብም ይችላሉ። ለአገር የሚጠቅም ሐሳብ አለን የሚሉ ወገኖች በነፃነት አደባባይ ይወጣሉ። ኃላፊነት የሚሰማቸው ብርቱና ትንታግ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ይፈጠራሉ። ሐሳብን በሐሳብ የሚሞግቱ ብርቱ አሰላሳዮች ይገኛሉ። ከዚያ ውጭ ያለውና በውሃ ቀጠነ የምንሰማቸው ክሶችና ማንገራገሮች ህዝብና ሃገርን አይጠቅሙምና አንቅረን ልንተፋቸው እንገደዳለን ።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy