Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለኢትዮጵያ ምርጫም፣ ብልጫም ነው!

0 373

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለኢትዮጵያ ምርጫም፣ ብልጫም ነው!

ወንድይራድ ኃብተየስ

የአገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አወቃቀራችን በዕውኑ ለቀውስ ዳርጓታል? አንዳንድ ሃይሎች ስለኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት የየራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡ ይታያሉ።  እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  የአገራችን ስኬቶች ሁሉ መሰረታቸቸው የፌዴራሉ ስርዓቱ ነው። እንደእኔ እንደእኔ የአገራችን የፌዴራል ስርዓት የታሰበለትን ግብ መቷል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል አገር ለመሆን በቅታለች።  

የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት የታሰበለትን ግብ መምታት ችሏል ያልኩት ስርዓቱ የአገሪቱን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች መቅረፍ በመቻሉ ነው።አንዱ ለዘመናት የአገራችን ችግር ሆኖ የኖረውን የፖለቲካ ችግር ማለትም የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነት ጥያቄዎች በአግባብ መመለስ በማስቻሉ ነው። ሌላው ደግሞ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ በመቻሉ የህዝቦች የመልማት ፍላጎት መመለስ የሚያስችል  ሁኔታዎች በመመቻቸታቸው ነው። እንዲሁም የፌዴራል ስርዓቱ ፍተሃዊ ልማትን በማስፈንና ድኅነትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። በእነዚህ ዋና ዋና መስፈርቶች የአገራችን የፌዴራል ስርዓት ስኬታማ ነው።  

የፌዴራላዊ አስተዳደር  እንደ እኛ ላሉ ብዝሃነት ለሚስተዋልባቸው  አገራት  አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው።  በተግባርም ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት  ድክመቶቹንም ራሱን በራሱ ማረም  የሚያስችል መንገድ  ያለው  ስርዓት ነው። በፌዴራል ወይም በማዕከላዊ  መንግስቱና በክልል መንግስታት መካከል ያለውን  የስልጣን ክፍፍል በሕገ መንግስቱ  በግልፅ  የተለየ በመሆኑ ሁሉም ድርሻ ድርሻውን መወጣት ከቻለ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ሁሉ  በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ያገኛሉ።

ለዘመናት በግጭትና ቀውስ ሳቢያ  በከፋ ድህነት  ውስጥ ስትዳክር የኖረችው አገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት  መከተል  በመቻሏ  በየዘርፉ በርካታ  ስኬቶች  ማስመዝገብ  ችላለች። የአገራችን ስኬቶች በሁሉም አካላት የተረጋገጡ የሚታዩና የሚዳሰሱ በመሆናቸው ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም።  ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን የስኬት መንገዳችንን ለማበላሸት የሚሯሯጡ አካሎችን እየተመለከትን ነው።   እነዚህ አካላት የችግሮቻችን  ምንጮች የፌዴራል ስርዓታችን እንደሆኑ አድርገው ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ናቸው።  ይሁንና  በእውኑ  እያስተዋልናቸው ያሉት  ሁከቶች ምክንያቶች የፌዴራል ስርዓታችን ነውን?  እውነታን ቆም ብሎ ላሰበው የፌዴራል ስርዓታችን  ሊሆን አይችልም።  ለዚህ በርካታ አስረጂዎችን ማንሳት ይቻላል።

በመጀመሪያ ደረጃ  ይህ ስርዓት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄሮችና  ህዝቦች መክረውና ዘክረው ይበጀናል ብለው የተገበሩት ስርዓት እንጂ መንግስት በዘፈቀደ ስለፈለገው ብቻ በህዝቦች  ላይ የጫነባቸው  ስርዓት አይደለም። የፌዴራል ስርዓታችን የኢትዮጵያ ህዝቦች  ራሳቸው መክረውና ዘከረው  ይሆነናል ይበጀናል ብለው ያጸደቁት ስርዓት በመሆኑም ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ አለው ስርዓት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበረውን   አህዳዊውን ስርዓትን ጠንቅቃ ታውቀዋለች። በአሃዳዊው ስርዓት ምን ይፈጸም እንደነበር መዘርዘሩ ለውድ አንባቢዎቼ  አሰልቺ ይሆናል ብዬ ስለማስብ ወደዛ መግባት አልፈልግም። ይሁንና አንድ እውነታ ግን  ማንሳት  ወደድኩ። አህዳዊው ስርዓት መላ አገሪቱን ለዘመናት በቀውስ ሲንጣት ቆይቶ በመጨረሻም  አገሪቱን ሊበትን አፋፍ አድርሷት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

በአህዳዊ ስርዓት ማንነቱ እንዲጠበቅለት የሚፈልግ ከ80 የሚበልጥ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎት ሊረጋገጥ አይቻልም። በኢትዮጵያ  በርካታ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች መናበብና መጣጣም የቻሉት አገራችን በተከተለችው የፌዴራል ስርዓት ሳቢያ ነው። ኢትዮጵያ በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች የሚስተዋሉባት አገር ከመሆኗ ባሻገር ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የምትገኝ አገር ናት። ኢትዮጵያችን በዚህ  አስቸጋሪ  በሚባለው የምስራቅ አፍሪካ  አካባቢ  የሰላም ደሴት ለመሆን የቻለችው  የህዝቦቿን   ልዩነቶችና ፍላጎቶች  አጣጥማ መኖር የሚያስችላት የፌዴራል ስርዓት መተግበር በመቻሏ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ የህዝቦች  የዘመናት  ጥያቄዎች የሆኑት እኩልነት፣ ሰላምና ልማት  የተረጋገጡት በዚህ የፌዴራል ስርዓት ነው። እንደእኔ እንደኔ ፌዴራሊዝም   ለአዲሲቷ  ኢትዮጵያ   የህልውናዋ  መሰረት  በመሆኑ  “ምርጫም ብልጫም”  ነው ባይ ነኝ።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  እንደኢትዮጵያ ላሉ  በርካታ ልዩነቶች የሚስተዋሉበት አገር  የፌዴራል ስርዓት  መከተል  ብቸኛውና ትክክልኛው  አማራጭ  ነው።  አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከፌዴራል ስርዓቱ ውጪ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም።  እንደእኔ እንደኔ  ይህን የፌዴራል ስርዓት ለማፍረስ  መሞከር ኢትዮጵያን እንደማፍረስ  መሞከር ይመስለኛል።  በእርግጥ ችግሮች እንዳሉ አይካድም፤  እነዚህን ችግሮች ደግሞ ማስተካከል የሚቻልበት ሁኔታዎች ምቹ ናቸው። በመሆኑም  ሁሉንም መጥፎ ነገሮች የፌዴራል ስርዓቱ እንዳመጣቸው አድርጎ ማቅረብ ተገቢነት የጎደለው አስተያየት  በመሆኑ ከእንደዚህ ያለ አስተያየት  መቆጠብ ተገቢ ይመስለኛል። ይህ አይነት  ሩጫ ለማንም የሚበጅ ውጤት እንደማያመጣ ሊታወቅ ይገባል።

በነውጥና ሁከት የሚመጣ ለውጥ ለማንም የሚበጅ አይሆንም። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት  በሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያና የመን  የተካሄዱ ነውጦች  በህዝቦች ላይ  ምን እንዳመጣባቸው መመልከቱ ለአገራችንም የሚበጃት ይመስለኛል። ብዝሃነት በህብረብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚኖር  ትልቅ አሴት ነው። በአገራችን በርካታ ልዩነቶች በአግባቡ የተስተናገዱት በዚህ የፌዴራል ስርዓት ነው። በፌዴራል ስርዓታችን  ውስጥ ከሚታዩ ማንነቶች መካከል የክልል ወይም የቡድን ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች  ሳይዛነፉ እኩል ሊዳብሩና ሊተገበሩ ይገባል።

 

ኢትዮጵያዊ ማንነት ሌሎች ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲገኝ አለማድረግ በተመሳሳይ የቡድን ወይም የብሔር ማንነትን ከሌሎች ማንነቶች በተለይ ከኢትዮጵያዊ ማንነት  በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም ስርዓት  እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሁሉንም በልክ በልክ የማናስኬደው ከሆነ ዋጋ ያስከፍለናል። የብሄር ማንነቶችንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስታርቀን መሄድ ካልቻልን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አይቻልም። ምክንያቱም  ሌባና ቀማኛ ሁሉ በብሄር ቡሉኮ  መጀቦኑ ስለማይቀር ነው።  ይህ ስሆን የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ መውደቁ አይቀርም። በመሆኑም  መንግስት በዘርፉ  በቂ ልምድና እውቀት ካላቸው ምሁራን ጋር በቅርበት በመስራት ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ራሱን በራሱ ማስተካከል የሚችልበት አሰራር ያለው በመሆኑ ይህን መጠቀም አስፈላጊ  ነው።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ጭምር ኢ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት እየተስተዋለ ነው። በአንዳንድ  አካባቢዎች አንድነትን የሚሸረሽሩ አካሄዶችና የቡድንተኝነት ስሜት በስፋት ሲራገቡ በአመራሩ ጭምር ተስተውለዋል። ራስን በራስ የማስተዳደር ፅንሰ ሐሳብም ፈሩን የሳተ ይመስላል። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት የራስን ቋንቋና ባህልን መጠቀምና ማዳበር እንጂ  አናሳዎችን ማጥቃት አይደለም። እንዲህ ያሉ አካሄዶች በክልል መንግስታትም ይሁን በፌዴራል መንግስቱ በወቅቱ ተገቢው እርምጃ መወሰድ ይኖርባቸዋል። ተገቢው እርምጃ በወቅቱ የማይወሰዱ ከሆነ ውጤቱ አያምርም።  አንዳንድ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን በሂደት ልዩነትን የሚያሰፉ ነገሮችን ነቅሶ በማውጣት  ማስተካከል ይገባል።

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነትም ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ መሆን መቻል ይኖርባቸዋል። በፌዴራል አስተዳደር ክልሎች ያለመዕከላዊ መንግስት እንዲሁም መዕከላዊ መንግስት ያለክልሎች ህይወት አይኖራቸውም። አንዱ ክልል ቀውስ ሲገጥመው ችግሩ የዚያ ክልል ብቻ የሚቆም ሳይሆን አገር አቀፍ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ተመልክተናል። በመሆኑም “ሞኝን እባብ ሁለቴ ነደፈው፤ አንዴ ሳያይ ሁለተኛ  ሲያሳይ” እንደሚባለው እንዳይሆን ከደረሰብን ችግሮች ጥሩ ትምህርት ልንቀስም ይገባናል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy