Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕዝቡ ኢህአዴግን በተስፋ ይጠብቃል

0 635

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕዝቡ ኢህአዴግን በተስፋ ይጠብቃል

 

ሰዒድ ከሊፋ

 

ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የተስፋ መቅረዝ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመራራ ትግል ህዝቡ ከአፈና አገዛዝ የተላቀቀበትን ትግል በአመርቂ ሁኔታ መርቷል፡፡ ኢትዮጵያን ከአፈና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ አሸጋግሯል፡፡ ሐገራችን ታዳጊ የገበያ ስርዓት አቅጣጫን በመከተል ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአዲስ ፈለግ እንደትጓዝ አደርጓል፡፡

 

በርግጥም ያለፍንባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት በሁሉም የህይወት መስኮች የሐገራችን የማሽቆልቆል ምዕራፍ የተዘጋባቸው አዲስ እና የማያቋርጥ የዕድገት ምዕራፍ የተከፈተባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ለዘመናት ከኖርንባቸውና ከተጓዝንባቸው አቅጣጫዎች የተለዩ አዳዲስ መንገዶች ተከትለናል፡፡ በቅድሚያ ሐገራችን ከምንም ነገር በላይ በዴሞክራሲ እጦት የምትሰቃይ ሐገር እንደሆነች በመገንዘብ የተሟላ ዴሞክራሲን ለማስፈን ጥረት ተደርጓል፡፡ መጀመሪያ በሽግግሩ ወቅት ቻርተር የጀመረው የዴሞክራሲ ለውጥ ሂደት፣ በህገ-መንግስቱ ተሟልቶና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ በህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ተዘጋጅቶ የቀረበውና ሁሉንም አማራጭ ድንጋጌዎች ለህዝብ ውይይት ያቀረበው ረቂቅ ህገ-መንግስት በ1986 ዓ.ም እስከ አስራ ስምንት ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎች ከመከሩበት በኋላ በህዝብ በተመረጡ ተወካዮች እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡

 

በዚህ ዴሞክራሲያዊ አኳኋን የፀደቀው ህገ-መንግስታችን በይዘቱም ቢሆን ዴሞክራሲያዊና የተዋጣለት ነበር፡፡ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት አሟልቶ ሊይዛቸው የሚገባ ዴሞክራሲያዊ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ በተጨማሪም ህገ-መንግስታችን በሌሎች ህገ-መንግስቶች ተፈልገው የማይገኙ ተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ አንቀፆችን ይዞ የተቀረፀ ከመሆኑም በላይ በተግባርም በኢትዮጵያ የሚገነባውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገዛና የሚመራ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ይገኛል፡፡ የዜጎችና የማህበረሰቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አሟልቶ በመጓዝ የተቀረፀው ህገ-መንግስታችን እነሆ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ያስቻለን ቁልፍ የለውጥ መሣሪያችን ለመሆን በቅቷል፡፡

 

በዚህ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ከሌሎች መሰል አገሮች በተለየ ሁኔታና ደረጃ መንግስታዊ ስልጣን የህዝብ መገልገያ መሣሪያ መሆን እንዳለበትና በዚሁ በመመራት የሚገነባው ስርዓትም ይህን ያለማወላወል ለማረጋገጥ የሚያስችል ማዕቀፎችን ይዞ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ ህገ-መንግስታችን የሐገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅጣጫ የህዝብና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ መሠረታዊ መርሆች እንዲመራ አድርጓል፡፡ በዚህም ባህርይው በሐገራችን የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሰፋ በተለይ ደግሞ በድህነትና በጉስቁልና የሚኖሩ ህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከምንም ነገር በላይ ትኩረት እንዲሰጥ ያደረገ ዴሞክራሲያዊና ተራማጅ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለመገንባትም እጅግ የተመቸ ሁኔታ የፈጠረ ነበር፡፡

 

በተጨማሪም ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ቀርፆ ያስፈፀማቸው ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ሐገሪቱ በፈጣን የዕድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ ያስቻለ እና ከሞላ ጎደል ከመላው የአፍሪካ አህጉር አማካይ የዕድገት ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ከፍ ብሎ የሚታይ የዕድገት ግስጋሴ የፈጠረ ነበር፡፡

 

ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም የማይነጣጥሉ ሐገራዊ ግቦች እንዲሆኑ ያደረገው ኢህአዴግ፤ ዛሬ መገንባት የጀመረውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚፈታተኑ ልዩ ልዩ ችግሮች ገጥመውታል፡፡ የህዝብ መብት እና ጥቅም እንዲከበር አልሞ የተነሳው ድርጅት፤ ይህን ግብ ከዳር ለማድረስ በሚያደርገው ትግል ልዩ ልዩ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ገጥመውታል፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች አንዱ የኅብረተሰብ ህይወት መለወጫ መሣሪያ አድርጎ የሚመለከተውን የድርጅት እና የመንግስት ሥልጣን ወደ ዝርፊያ መሣሪያነት ሊቀይር የሚችል የጥገኝነት አስተሳሰብና እንቅስቃሴ ነበር፡፡

 

ድርጅቱ ይህ የገጠመው የጥገኛ ዝቅጠት አደጋ መሠረታዊ ምንጩ ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ ችግሩን ከአመራሩ ማህበራዊ ምንጭ ጋር አያይዞ ይመለከተዋል፡፡ አመራሩ ከንዑስ ባለሃብት መንደር የፈለቀ በመሆኑ፤ ከማህበራዊ ምንጩ የተነሳ የያዘውን ሥልጣን ቀስ በቀስ ያለአግባብ  የመጠቀም ዝንባሌ ሊያሳይ እና መንግስታዊ እና ድርጅታዊ ስልጣንን የግል ህይወቱን መቀየሪያ መሣሪያ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህ አመራር ከንዑስ ባለሃብት መደባዊ ተፈጥሮው የተነሣ፤ ትግሉ (በተለይ የአርሦ አደሩ ትግል) የተጠናከረ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ አብዮታዊ የአመራር ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡ ከዚህ ለየት ባለና አርሶ አደሩ በተቀዛቀዘ ሁኔታ በሚያልፍበት ጊዜ ደግሞ በያዘው ስልጣን ራሱንና የቅርብ ወዳጆቹን እየጠቀመና እየተጠቃቀመ በመጓዝ ወደ ግል ብልፅግና ሊሸጋገር የሚችል ነው፡፡

 

ይህ ዝንባሌ በንድፈ ሃሳብ የሚታወቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በሐገራችን ሁኔታ በተጨባጭ መከሰት የጀመረው፤ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት ነበር፡፡ ስለሆነም በሁሉም ክልሎችና ብሔራዊ ድርጅቶች የመንግስት ስልጣን በያዙ ግለሰቦች ዘንድ ቀስ በቀስ በስልጣን የመጠቀም አዝማሚያቸው እየጠነከረ መሄድ ጀመረ፡፡ ይህም ደርጅቱ የአርሦ አደሩ ጥያቄዎች የነበሩትን የዴሞክራሲና የብሔር እኩልነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የምርት ነፃ ተጠቃሚነት መብቶችን በማረጋገጡ የአርሦ አደሩ ትግል ስለተቀዛቀዘ አመች ሁኔታ ስለተፈጠረለት የታየ ዝንባሌ ነበር፡፡

 

ከዚህ በመነሳት ሲታይ እንደ እኛ በሐገራዊ የለውጥ ሂደት ውስጥ ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች አንዱና መሠረታዊው የመንግስትን ስልጣን አላግባብ ለመጠቀምና በዚህም እየታገዙ ለመበልፀግ ማሰብና መንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ እስከ ተወሰነ የዕድገት ደረጃ አብሮ የሚቆይና በማንኛውም ሁኔታ ቸል ሳይባል ሊታገሉትና ሊቆጣጠሩት የሚገባ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ አርሦ አደሩ የነበሩት ጥያቄዎች ሁሉ ተመልሰውለት በሰላም አርሶ መብላት በሚፈልግበት ወቅት ይበልጥ የተመቸ ሁኔታ እንደሚፈጠርለት ግንዛቤ ተይዞ ተገቢው ጥንቃቄና ትግል ካልተደረገበት በስተቀር ስርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ የማያጠያይቅ ነው፡፡ በ1993 እና በ1994 ዓ.ም የተካሄደው ድርጅታዊ ተሃድሶ ዋነኛ መነሻዎችም እነዚህ ነበሩ፡፡

 

ተሃድሶው እስከ ተወሰነ የታሪክ ምዕራፍ በተለይ ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የተሟላ ልዕልና እስኪይዝ ድረስ ባለው የለውጥ ምዕራፍ፣ የመንግስት ስልጣን በማያቋርጥ ደረጃ ከታለመለት ዓላማ ውጭ የግል ብልፅግና መሣሪያ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለ፣ ከዚህም አልፎ ይህ ዝንባሌ ከስርዓቱ ጋር በማይነጠል ሁኔታ አብሮ የሚኖርና ቀጣይ ትግል የሚጠይቅ እንደሆነ ድርጅቱ ያውቃል፡፡ በአንፃሩ ይህን ችግር ለመቋቋም አስፈላጊ የሆነው የህዝብ ትግል ደግሞ እንደሁኔታው ሊኖርም ላይኖርም፣ሊቀዛቀዝም ላይቀዛቀዝም እንደሚችል ተገዝቧል፡፡

 

ይህ የህዝብ ትግል በሌለበት ጊዜ ሁሉ የመንግስት ስልጣንን ካለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ከመኖሩ አልፎ፣ የበላይነት ሊይዝ ይችላል፡፡ ስለሆነም በመፍትሄ ደረጃ የህዝቡን ትግል በቀጣይነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ለዚህም ሲባል በህብረተሰባችን ውስጥ ዴሞክራሲና ልማትን ማስፋፋትና የህዝብን ተጠቃሚነት እያረጋገጡና እያሰፉ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም ህዝቡ ኢህአዴግን በተስፋ ይጠብቃል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy