Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕገ-ወጥ ስደት ዛሬም…

0 325

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕገ-ወጥ ስደት ዛሬም…

ወንድይራድ ኃብተየስ

ስደት አዲስ ክስተት አይደለም። የሰው ልጆች ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ  ስደት አብሯቸው የኖረ ክስተት ነው። ሰዎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አስገዳጅ ምክንያቶች አልያም በፍላጎት  ከተወለዱበት ወይም ከሚኖሩበትን አካባቢ ወይም አገር ለቀው ድንበር አቋርጠው ወደ ሌሎች አካበቢዎች ወይም አገራት በመሄድ መኖር ሲጀምሩ ተሰደዱ ይባላል።  ስደት በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሚታይ ይሁን እንጂ በታዳጊ አገሮች በተለይ ደግሞ ከሳሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ችግሩ ገዝፎ ይታያል።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እያስተዋልን ያለነው የስደት አይነት  ሕይወትን ሊያሳጣ አካልን ሊያጎድል የሚችል እጅግ ዘግናኝ ነገር ሆኗል። በየዓመቱ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ህገወጥ ስደት ምክንያት ነው። ሕይወት መተኪያ የሌላት አንድ ናት፤  በእርሷ ላይ ቁማር መጫወት አይቻልም። በቅርቡ በሰሜናዊቷ የአፍሪካ አገር ሊቢያ በአፍሪካ ስደተኞች ላይ የተከሰተውን ነገር  እጅግ አስፈሪ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚፈጸም ነው ብሎ ማሰብ እስከሚከብድ ድረስ በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን  አስፈሪም ጭምር ነው።

ሰዎች በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ከሚያደርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ጦርነት፣ ድሕነት ወይም ርሃብ፣ የስራ ዕድል አለመኖር፣ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ፣ የዴሞክራሲ ዕጦት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት (የትራንስፖርቴሽን መስፋፋት)፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የሰዎች ፍላጎት ማደግ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። የአብዛኛዎቹ ስደተኞች መዳረሻ አውሮፓና እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ይሁን እንጂ በርካታ  አፍሪካዊያን ወደ ጎረቤት አገራት ይሰደዳሉ።  

የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው ከ230 ሚሊዮን በላይ  ስደተኞች በመላው ዓለም እንደሚገኙ ይገልፃል። ከእነዚሕም መካከል 59 በመቶው የሚሆኑት ስደተኞች በአደጉት ሀገሮች የሚገኙ ሲሆን በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ቀሪውን 41 በመቶው በማስተናገድ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያስረዳል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የስደተኞች ቁጥር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  እያሻቀበ በመምጣቱ ሳቢያም አይ ኦ ኤም  ለስደተኞች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በአግባቡ  ማቅረብ እየከበደው እንደሆነም አስታውቋል።

 

ትላንት በጦርነት፣ በድርቅና ረሃብ ትታወቅ የነበረች አገራችን ዛሬ ለአካባቢው አገራት ህዝቦች እንደሁለተኛ አገርነት በመቆጠር ላይ ነች። ዛሬ ላይ አገራችን ከሰሃራ መለስ ካሉ አገራት ከፍተኛውን የስደተኛ ቁጥር የምታስተናግድ አገር ለመሆን በቅታለች።  በቅርቡ በተደረገ ጥናት አገራችን ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ኤርትራ ብቻ ለመጡ  ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።  ይህን ያህል ቁጥር ያለውን ስደተኛ ማስተናገድ እንደኢትዮጵያ ላሉ  ውሱን ሃብት ያላቸው አገሮች ኢኮኖሚ  ላይ የሚፈጥረው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አውሮፓዊያኖች ለስደተኞች በራቸውን ከርችመዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ  ያላትን ውሱን ሃብት ቀንሳ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን  ስደተኛን እየተቀበለች ታስተናግዳለች። ይህ የህዝባችንና የመንግስታችን  ተግባር በዓለም ዓቀፍ መድረኮች አስመስግኖናል።

 

የኢፌዴሪ መንግስት  በአገራችን ለሚገኙ ስደተኞች ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩላቸው በማድረግ ላይ ነው። ለአብነት የትምህት ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በርካታ ስደተኛ ወጣቶች በተሰጣቸው የትምህርት ዕድል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የመማር ዕድል አገኝተዋል። ከዚህ ባሻገር በርካታ ስደተኞች በአገራችን በስራ ተሰማርተው ኑሯቸውን በሰላም እየገፉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በዚህ ድርጊቷ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ምስጋ የተቸራት አገር ለመሆን በቅታለች። ይህ ለሁላችንም የሚያኮራ ተግባር ነው። በሌላ በኩል  በርካታ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች በተለያየ ምክንያት ወደተለያዩ አገራት በመሰደድ ላይ ይገኛሉ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በአሁኑ ጊዜ  በአገራችን ክፍያው ቢያንስም ስራ አለ። የክፍያው እንደመካከለኛው ምስራቅ ወይም እንደምዕራባዊያኑ ላይሆን ይችል እንደሆን እንጂ መስራት ለሚፈልግ፣ ስራ ለማይንቅ፣ ሰርቶ መብላት ለሚፈልግ ሁሉ ሰርቶ መለወጥ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።  

በአገራችን በርካቶች ከምንም ተነስተው ሰርተው መለወጥ እንደሚቻልም በተግባር አሳይተዋል። በማሳየትም ላይ ናቸው። በስደት ኑሮ ዕድለኛ ከተሆነ ገንዘብ ይገኝ ይሆናል።  ነገር ግን ስደት ዴሞክራሲያዊ መብትን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ክብርን የሚገፍ ነገር ነው። ሰሞኑን በሲኤን ኤን ቴሌቭዥን የተመለከትነው ዶክመንተሪ ስደት የአፍሪካዊያንን ሰብዓዊ ክብር ምን ያህል እንደገፈፈ አስገንዝቦናል። አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ ረዳት ላጡ፣ በበረሃ ለተንገላቱ፣ ለራባቸውና ለጠማቸው ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ያደረጉላቸው አቀባበል ከሰውነት ተግባር የወጣ ነው። እንደው የሊቢያን ሁኔታ እንደአብነት አነሳሁ እንጂ በርካታ አገሮች ለስደተኞች  የሚሰጡት ክብርና ስደተኛን የሚይዙበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው። በአገር ሰርቶ መኖር ከዚያም አልፎ መበልጸግ እየተቻለ ሕይወትን፣ አካልንና ስብዕናን በሚጎዳ መልኩ መሰደድ ተገቢ አይደለም።

አንዳንድ ወጣቶች ሕይወትና አካላችሁን ለሕገወጥ ደላሎች ኪስ ማደለሚያነት አሳልፋችሁ እየሰጣችሁ መሆኑን ልትገነዘቡት ይገባል። ህገወጥ ደላሎች ህሊናቸውን ሸጠዋል። ለእነርሱ ገንዘብ እንጂ የደሃ ልጅ ህይወት ቁብ አይሰጣቸውም። በአገራችን ሕገመንግስት ዜጎች ወደፈለጉት አገር ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደፈለጉት አገር መሄድና መስራት እየቻሉ  ለሕገወጥ ደላሎች  ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ሕይወታቸውንና አካላቸውን ለአደጋ ማጋለጣቸው  አግባብነት የጎደለው ነገሮችን ሰከን ብሎ ካለማሰብ የሚመጣ ነገር ነው። እኛ ወጣቶች ሕገወጥ ደላሎች ስለስደት መልካምነት የሚነግሩንን የተረት ተረት ታሪክ ቆም ብለን ልንፈትሽ ይገባናል።  አንዳንዶች ዛሬም ሕገወጥ ስደት በእህትና ወንድሞች ላይ ያደረሰውን እጅግ ዘግናኝ ነገር በአይናችን እየተመለከትን በሕገወጥ መንገድ በመሰደድ ላይ ነን።

በሕገወጥ ደላሎች የፈጠራ ወሬ ተደናብረው ስደትን የተከተሉ በርካታ እህትና ወንድሞቻችን በየበረሃውና በየባሕሩ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው ጠፍቷል፤ አካላቸው ጎድሏል። ሕገወጥ ስደት  በወገኖቻችን ላይ ካደረሰው  ጉዳት  ባሻገር  የአገራችንንም ገጽታ እጅጉን ጎድቶታል። መስራትና አገር መለወጥ የሚለውን የሰው ሃይል በማራቆትም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ነው።  በመሆኑም ወጣቶች ስደትን ሲያስቡ ውሳኔቸውን መልሰው መላልሰው ሊያስቡበት ይገባል።

ከፍተኛ ገንዘብ ለሕገወጥ ደላሎች  በመክፈል  ለአደጋ ከመጋለጥ ይልቅ ያንን ገንዘብ በአገር ውስጥ መነሻ በማድረግ መስራትና መለወጥ ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት አገራችን ማንም በአነስተኛ ገንዘብ መነሻ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ፈጥራለች። መንግስትና ህዝብም ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት  የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ በመሆናቸው ይህን ዕድል ወጣቱ ሊጠቀምበት ይገባል።   

አገራችንን ተባብረን ማሳደግ የሁላችንም ሃላፊነትና ግዴታ ነው። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ስደት፣ ወጣቱን፣ የተማረውንና  መስራት የሚችለውን ትኩስ ሃይል የሚያሳጣ ነገር በመሆኑ ለዕድገት ጸር  ነው። ዛሬ የምንሰደድባቸው አገሮች የተለወጡትና ያደጉት በዜጎቻቸው ጥረት መሆኑን  በመገንዘብ እኛም ተባብረን  በአገራችን በመስራት መለወጥና ማገልጸግ እንችላለን። አሁን ላይ በአገራችን በርካታ ነገሮች በመለወጥ ላይ በመሆናቸው ኢኮኖሚያችን በፍጥነት በመለወጥ ላይ ነው። ይህን ዕድገት ማስቀጠል ከቻልን በጥቂት ዓመታት እኛም ወደከፍታው እንደምንወጣ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።   

ሕገ-ወጥ ስደት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመሆኑ የችግሩ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነውን የሕገ-ወጥ ደላሎችን ምሽግ ለማፈራረስ መንግስትና ሕዝብ በቅርበት መስራት ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን መምከርና ማስተማር አለባቸው። መንግስትም  ወጣቶች በአካባቢያቸው የስራ ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ጥረቱን ማጠናከር ይኖርበታል። ሕገወጥ ደላሎች ከሕብረተሰቡ የተሸሸጉ፣ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡሮች ባለመሆናቸው ልናጋልጣቸውና ለህግ ልናቀርባቸው ይገባል። ሰውን የሚሸጡ፣ በሰው ደም ለመበልጸግ የሚፈልጉ  ሕገወጥ ደላሎችን ከመንግስት ጎን በመሰለፍ  ለሕግ አሳልፎ መስጠት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ ሊሆን ይገባል። ባለፉት 15 ዓመታት አገራችን ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሕብረተሰቡን አሳታፊ  በመሆናቸው ነው። ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ሕገወጥ ስደትን ለመግታት መንግስት ሕብረተሰብ አሳታፊ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ  መተግበር ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy