Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹መንግሥት እንኳን የሰው ሕይወት ይቅርና የውሻ ደም መፍሰስ የለበትም ብሎ ነው እየሠራ ያለው›› ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር

0 374

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ቅዳሜ ኅዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን፣ ስለህዳሴ ግድቡና አገሪቱ ስላለችበት የፀጥታ ሁኔታ የመግለጫቸው የትኩረት ነጥቦች ነበሩ፡፡

ሚኒስትሩ ቀዳሚ አድርገው የሰጡት መግለጫ ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ስለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲሆን፣ ‹‹ዜጎች በጋራ ባቋቋሙት መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምር የሚባል ዕድገት ላይ ያደረሳቸውን የከፍታ ጉዞ መቅዘፍ ከተያያዙ ውለው አድረዋል፤›› ብለዋል፡፡ ብዝኃነትን በአግባቡ በማሳደግና አገራዊ ሰላምና ብልፅግና ሊያረጋግጥ የሚችል በአገሪቱ የተሻለ አማራጭ የለም ብለው፣ ‹‹አገሪቱ ወደ ከፍታ የምታደርገው ጉዞም ሰምሮለታል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱን ውስጣዊ ሰላምና አንድነት የሚገዳደሩ ችግሮች አሁንም ድረስ እንዳሉ ግን ከመናገር አልተቆጠቡም፡፡

በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ግጭት በአሁኑ ጊዜ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና መረጋጋት እየታየ እንደሆነ፣ ይህ ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረው በፀጥታ አካሉ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ድጋፍና ትብብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዜጎችም በልማት ሥራ ላይ ተጠናክረው እየሠሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ዞኖች ለምሳሌ በበደሌና ሌሎች አካባቢዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶችን ሕዝቡ በራሱ በመከላከልና ችግር የደረሰባቸውን አካላትን መልሶ በማቋቋም ትልቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች በዚህ ሒደት ያሳዩት ሕዝባዊነትና ሰላም ወዳድነት የሚያስመሰግናቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ሲነሱ የነበሩ ችግሮች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሰላማዊ ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች መረጋጋት እንደታየባቸውና ሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮውን እየመራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብና የአገር ሽማግሌዎች ሕዝቡን በማስተማር ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ ንብረትነታቸው የውጭ ዜጎች ግለሰቦች የነበሩና የፈረሱ ፋብሪካዎችን ሳይቀር ሕዝቡ ራሱ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ‹‹የጠፋውን ንብረትም ሕዝቡ እንደሚክስ ቃል በመግባት ወደ ቀድሞው ሁኔታው እየተመለሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የተለያየ ፍላጎት ያላቸውና ሥልጣን በአቋራጭ ለመያዝ የሚፈልጉ አካላት ወጣቶች ስሜታዊ እንዲሆኑ በማድረግ አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ እንደነበር አስታውሰው፣ ትክክለኛና አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች በመለየትና በመቀበል ምላሽ እንዲያገኙ ሲሠራ መቆየቱን ወደፊትም እንደሚሠራ አክለዋል፡፡

በአገሪቱ ያለው ሰላምና መረጋጋት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነበሩ ትንንሽ ችግሮች ዕልባት እንዳገኙም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ፈተና የሚወስዱበት አሠራር እንደተፈጠረ አስታውሰው፣ አንዳንድ ተማሪዎች ይህንን በመቃወም ችግር ሲፈጥሩ መታየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ለተማሪዎች ምቹ አሠራር እንዲፈጥር የሚጠይቁበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች በየትኛውም መንገድ ጥያቄ ማንሳት መብታቸው እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ የሚደግፉ ወጣቶች ድጋፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ወደ ሁከት ይቀየር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምናያቸውን ጉዳዮች አብዛኛው ተማሪ የመማር ፍላጎት እንደሌለው አድርገን መውሰድ የለብንም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከትምህርት ሚኒስቴር በተገኘው መረጃም አንዳንድ ተማሪዎች እንደሚሰናበቱ ወይም እንዲቆዩ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ በሥነ ምግባር ጉድለት ዩኒቨርሲቲዎች ዕርምጃ ይወስዳሉ፡፡ የተወሰኑ ደግሞ ከጓደኞቻቸው ጋር በመጠጋት ዶርም ውስጥ መቆየታቸው የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ቤተሰብ መመለስ ትልቅ ሽንፈት የሚመስላቸው አሉ፡፡ መቶ በመቶ ያልተባረሩትና አንድ ዓመት እንዲቆዩ የተደረጉት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቆይተው የሚመለሱበት ዕድል አለ፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እንደዚህ ዓይነት ተማሪዎች ስሜታዊ በመሆን ሌሎችን የሚቀሰቅሱበት አጋጣሚ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ተማሪዎች የሚፈጠረውን ትንንሽ ግጭት ሰፋ አድርጎና ስያሜ ሰጥቶ የማባባስ አዝማሚያ መታየቱንም ጠቁመዋል፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ግጭቶች ሲፈጠሩ አድብተው የሚጠብቁ ጋዜጠኞች ደግሞ ግጭቱን የብሔር ግጭት አድርገው እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ትክክለኛውን ገጽታ ቀይሮ በዚህ ብሔርና በዚያ ብሔር መካከል ግጭት ተፈጥሯል በማለት የሚስሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤›› ብለዋል፡፡

ግጭቶች መረጋጋት እንደታየባቸው ጠቁመው፣ ተማሪዎችም ተመልሰው በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሒደትም ያልተመለሱትን መንግሥት እንዲመለሱ እያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህም አንፃር ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ያለው ከቁጥጥር ውጪ እንዳልወጣና ትክክለኛውን አቅጣጫ እየያዘ እንደመጣ መናገር ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ በኩልም ትምህርት ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከወራት በፊት ጀምሮ ተከስቶ ስለነበረው ግጭትም መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ‹‹በስፋት የነበረው ግጭት ከሞላ ጎደል ተረጋግቷል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ቦታ መቶ በመቶ ቆሟል የምንልበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለው፡፡ በተለይም ደግሞ ባለፈው ሳምንት በቦረና፣ በጉጂ፣ በሞያሌና በሶማሌ አጎራባች ወረዳዎች ችግሮች ተስተውለዋል፤›› ብለዋል፡፡

የችግሩ ዋነኛ መንስዔም በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ወሰን በትክክል አለመለየቱ እንደሆነ አስታወሰው በቦረና፣ በጉጂና በባሌ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት እንዲሰፋ ያደረጉት ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎችና ኮንትሮባንዲስቶች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ሰሞኑን በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭትም ከሃያ በላይ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋና ንብረት እንደወደመ ተናግረዋል፡፡

‹‹በግጭቱ በምሥራቅ ሐረርጌ አካባቢና በጅግጅጋ አካባቢዎች በወንጀል የተሳተፉ አካላት አሉ፡፡ በኦሮሚያ በተለይ በአወዳይ በኩል በተፈጠረው ችግር እጃቸው ያለባቸው ተጠርጣሪዎች በኦሮሚያ ክልልና በፌዴራል ፖሊስ አማካይነት የተወሰዱ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ መንግሥት በየትኛውም መሥፈርት በዜጎች ላይ ጥቃት ያደረሱትን ተጠያቂ ለማድረግ ይሠራል፡፡ ይህን ማስቆም የመንግሥት ድርሻ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጉዳት ያደረሰ እንኳን አገር ውስጥ ይቅርና ውጭ አገር ቢሄድም ከተጠያቂነት አያመልጥም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በኦሮሚያ በኩል በአጠቃላይ 98 ተጠርጣሪዎች በምሥራቅ ሐረርጌ አወዳይ ውስጥ በነበረው ግጭት የተሳተፉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 54 የሚሆኑ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተያዙ ናቸው፡፡ 44 ደግሞ ያንን ግጭት ለማርገብ በተሠማራው የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አማካይነት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል በኩል በፌዴራል ፖሊስ አማካይነት 38 ተጠርጣሪዎች እንደነበሩ አስታውሰው፣ ከእነዚህ መካከል 29 ተጠርጣሪዎች የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው፣ እስካሁን አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ አስረድተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል አመራሮችና የፀጥታ አካላት አማካይነት በቁጥጥር ሥር የዋለ አንድም ሰው እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት የተፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው፣ የማቋቋሙ ጉዳይ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳልሄደ ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመነጋገር በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል የሰላም ኮንፈረንስ ለኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ቢያዝም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በዕለቱ ኮንፈረንሱን ማካሄድ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡ ኮንፈረንሱ ያልተካሄደበት ምክንያትም የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር ክፍተቶች በመኖራቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱም ክልሎች የክልላቸውን ሕዝቦች እያወያዩ እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ለወደፊት የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ነዋሪዎች ጋር ለማካሄድ የታቀደው የሰላም ኮንፈረንስ በቅርብ ቀን እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እየሰጧቸው ባሉ መግለጫዎች፣ በአገሪቱ እየተፈጠረ ላለው ቀውስ መነሻው ራሱ ፌዴራሊዝሙና እየተተገበረ ያለበት መንገድ እንደሆነ ይተቻሉ፡፡ ወጣቶች የተቀረፁበት መንገድም ልዩነቶችን እያጎላ ነው ይላሉ፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ከአንድነት ይልቅ ልዩነቶች ተሰብከዋል፡፡ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከተነገረው በላይ ስለልዩነት ነው የተነገረው ይላሉና በዚህ ላይ አስተያየታቸው ምን እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ ሲመልሱም፣ ‹‹ተቃዋሚዎች ፌዴራሊዝምን የሚገልጹበት ሁኔታ በአንድ ዴሞክራሲያዊት አገር ውስጥ የሚጠበቅ ነው፡፡ ልዩነታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥልጣን ለመያዝ በሚሞክሩበት ጊዜ የሌለ ሳይሆን ያለውን አጀንዳ አንግል በመቅረፅ ነው ሕዝቡን ለማሳመን የሚሠሩት፡፡ ይህንን ችግር ያመጣው ፌዴራሊዝሙ ነው ብሎ መደምደም ትክክል አይደለም፡፡ እውነታውንና የእነሱን የፖለቲካ ስትራቴጂ ለይተን ማየት አለብን፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በእኛ በኩል የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ያመጣውን ውጤት ማንኛውም ሰው የሚያየው ነው፡፡ በተግባር የምናያቸው ውጤቶች አሉ፤›› ብለው፣ ሥርዓቱ የሕዝብ ሥርዓት ስለሆነ ሕዝቡን ማክበር ተገቢ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሥርዓቱ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን የሕዝብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ጥያቄ ለህዳሴ ግድቡ መዘግየት ምክንያት በግድቡ ግንባታ ሜቴክ ድርሻ ይዞ እየሠራ መሆኑ እንደሆነ እየተነገረ መሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹አዎ በትክክል በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ ነገር ግን አሁን ከአምስት ዓመት በላይ እንደሄደ እናውቃለን፡፡ በሜቴክ በኩልም የጎላ ችግር አለ አንልም፡፡ አንድ ወቅት አስፈላጊው ደረጃ ላይ ላይደርስ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይኼ መቶ በመቶ እንደ ምክንያት የምንወስደው አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ጥያቄ በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶች ምክንያቱ ዜጎች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚገልጹበት መንገድ ባለመኖሩ ነው ይባላልና በዚህ ላይ ምን ይላሉ የሚል ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ተገቢ እንዳልሆኑ ጠቁመው፣ ዜጎች ጥያቄ ካላቸው ጥያቄያቸውን በተገቢው መንገድ በማቅረብ ምላሽ እንደሚያገኙ አስረድተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት እንኳን የሰው ሕይወት ይቅርና የውሻ ደም መፍሰስ የለበትም ብሎ ነው እየሠራ ያለው፤›› ብለዋል፡፡ ወጣቶች ጥያቄ ሲያነሱ ብቻ የፀጥታ አካላት ዕርምጃ መውሰድ እንደሌለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የተጠርጣሪዎችን ማንነት እንዲገልጹ የተጠየቁት ሚኒስትሩ በምላሻቸው፣ ‹‹ተጠርጣሪዎች ነገዴዎች ናቸው? አርሶ አደሮች ናቸው? የፀጥታ አካላት ናቸው? ወይስ የሲቪል አመራር ናቸው? የሚለውን ለይተው አልሰጡንም፤›› ብለዋል፡፡

ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ የግብፅ አቋም ምን ይመስላል? ኢትዮጵያ የምታራምደው የአፀፋ ምላሽ ምንድነው? የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም፣ ‹‹የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሀብት ነው፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን መገለጫችን ነው፡፡ ግብፆች ውኃ የሞትና የሽረግ ጉዳይ ነው እንደሚሉት ሁሉ ልማት የእኛም የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለሚኒስትሩ የሼክ መሐመድ አል አሙዲን በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት መታሰር በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ባገኘነው መረጃ መሠረት በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ እየሠሩ ያሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ በመታሰራቸው ሳዑዲ ዓረቢያ ሉዓላዊ አገር ስለሆነ ጣልቃ መግባት አንችልም፡፡ ነገር ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑና ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ጉዳዩ የሚመለከተን ስለሆነ ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየተከታተልነው ነው፤›› ብለዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy