Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መጥበቅ ያለበት አገራዊ አንድነት

0 496

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መጥበቅ ያለበት አገራዊ አንድነት

ዳዊት ምትኩ

ወቅቱ አገራዊ አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። አገራዊ አንድነትን መፍጠር ዜጎች በትግላቸው ያገኙትን ህገ መንግስታዊ ስርዓት ለማስቀጠልና ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል። ከአንድነት እንጂ ከመለያየት የሚጠቀም አካል የለም። በአሁኑ ሰወቅት እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች ስርዓቱ የወለዳቸው ሳይሆኑ ስርዓቱን ለመናድ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ሴራ የፈጠሯቸው ናቸው።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንድነትን የሚያጠብቅ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት የድል ባለቤት ነው። ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ አንዳንድ ወገኖች ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም።

አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ሥራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኞችና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ዕድገትና አንድነት ሠላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም።

የአገራችን ህዝቦች የሚከተሉት የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን የመስኩ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

ከዚህ ዕውነታ የሚነሳው የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ- መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው።

ይህ የአገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለዚህም ይመስለኛል። ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችብን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።

ይህ ውሳኔያቸውም ለዛሬው እነርሱነታቸው ያበቃቸው ከመሆኑም በላይ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ አንዳንድ ወገኖችና ፅንፈኞች ሃቁን ካለመገንዘብ አሊያም ለመረዳት ካለመፈለግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት እንደሚሉት ዓይነት በድንቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አለመሆኑንም አሳይተዋል። ምክንያቱም ሥርዓቱ በህዝቦች ፈቃድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ከ26 ዓመታት በኋላም ቢሆን በሚገባ ማረጋገጥ ስለቻሉ ነው።

እርግጥ የእነዚህ ወገኖች የማምታታትና የማደናገር ሙከራ ምንም ውጤት የሚያስገኝላቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም መላው የሀገሪቱ ህዝቦች በደማቸው የፃፉት ህገ መንግሥት ፀድቆ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም በአንድነት ተሳስረው የእድገት ጉዟቸውን ስለተያያዙት ነው።

ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

በአገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል።

ይህ ሁኔታም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንድነትን ለሚያጠናክሩና መሰረቱን ለሚያሰፉ እንጂ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈፀም አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች እንዳይስፋፉ ያደረገ ይመስለኛል። የኢፌዴሪ መንግስት የታገለለትንና በህገ መንግሥቱ ውስጥ ተካትቶ ዛሬም ሆነ ነገ በፅናት የሚያምንበትን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማይገሰሱ መብቶች ላይ ከቶም ቢሆን ድርድር የሚያውቅ አይመስለኝም። ከ26 ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራቶች ስንቃኛቸው የሚያሳዩን ዕውነታዎች ይህንኑ ነውና።

እርግጥ የብሔረሰቦች መብት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለትና ለተግባራዊነቱ ህዝቦች በሙሉ የተረባረቡበት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ገዥው ፓርቲም ይሁን የሀገራችን ህዝቦች ያላቸው አቋም መቼም ቢሆን ሊቀለበስ የሚችል አይደለም።

እናም ከሚያራምዱት ፖለቲካዊ ርዕዩተ-ዓለም አኳያ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በህልም ዓለም ቅዠት ሲያፈርሱ የሚያድሩት የአገራችንና የህዝቦቿ ጠላቶች፣ አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎች እንጂ፤ በህገ መንግሥቱ ያገኘውን መብት ተጠቅሞ በሰላማዊ ሁኔታ ሥራውን በማከናወን 26 ዓመታትን የተሻገረውና የመብቱ ባለቤት የሆነው የአገራችን ህዝብ አለመሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል።

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከግጭት ጋር የተያያዙ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁንና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ተጫውቷል። ይህ የአገራዊ አንድነት ሁኔታ ይበልጥ መጥበቅ አለበት። ታዲያ ለዚህ ጥንካሬያችን ህገ መንግስቱን ምርኩዝ ማድረግ ይኖርብናል።

በህገ መንግስቱ ላይ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመገንባት ቃል ገብተዋል። በዚህ ሰነድ መሰረት እየተመሩም ኢኮኖሚቸውን አሳድገዋል። በአንድነታቸው ጥላ ስር ሆነው የቀጠናው መሪነት ሚናቸውን እያጠናከሩ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ ተደርገዋል። ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ተደርጓል።

በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ የተነሳበት ዋናው መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ መደርጀት አለበት። አንድነታችን መጠናከር ከቻለ የማንሻገረው ተግዳሮት የለም። በአንድነት ውስጥ ዘላቂ ዴሞክራሲ ሊገነባ ይችላል። በመለያየት ውስጥ ግን እርስ በርስ ከመበጣበጥ በስተቀር የምናተርፈው ነገር የለም። እናም ሁሌም አንድነታችን ሊጠብቅና ፈር ባለው መንገድ መጓዝ እንዳለበት ልንዘነጋው አያስፈልግም።  

  

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy