Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሠላማችን ይብዛ…

0 389

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሠላማችን ይብዛ…

አባ መላኩ

አሁን ባለንበት ወሣኝ ወቅት ላይ ኪራይ ሰብሳቢነትን የማድረቅና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ትግል ይበልጥ ተጧጥፎ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ እዚህ ላይ ኢሕአዴግ ዕድለኛ ነው ሊያሰኘው የሚገባ ጉዳይ ይታያል። ህዝቡ እያንዳንዷን ክፍተት ለይቶ የመናገር ድፍረቱ ዛሬ ላይ በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ምንም እንኳን ህዝቡ በግልፅ እንዲናገር ህገ መንግሥቱ ያጎናፀፈው መብት ቢኖርም ሀሳቡን ሳይሸማቀቅ እንዲገልጽ ያስገደደው ግን ለአገሪቷ ልማት ያለው ቀናኢነትና ተቆርቋሪነት ነው፡፡

በየደረጃው በሚታዩ መድረኮች በህዝቡ የሚስተዋለው ግልፅ አቋም በተመጽዋችነት  ሳይሆን በሥራና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ብቻ የኢትዮጵያ ዕድገት እንደሚረጋገጥ ግልፅ ስምምነትና አቋም ተይዟል። እንደ ኢሕአዴግ ላለ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ለያዘ ድርጅት የህዝብን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ አገር ለመምራት ስለሚረዳው ነው ዕድለኛ የሚያስኘው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሉ ያለ የሌለ አቅሙን በመጠቀም መሸሸጊያ ለማግኘት መፍጨርጨሩ የሚጠበቅ ነው። ለዓመታት ህዝብን ከህዝብ የማለያየት አጀንዳ ቀርጾ ሲንቀሳቀስ ሰንብቷል። በመካከላቸው ከፍተኛ ቅራኔ ያላቸው ትምክህተኛና ጠባብ ኃይሎች ሳይቀሩ አንድ ግንባር ላይ የተሰለፉበት ሁኔታ ተፈጥሮ አይተናል። ለዚህ ጉዳይ ሁነኛ ማሣያዎችን መጠቃቀስ ይቻላል። ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የታየው ግጭት ከማሣያዎቹ ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል።    

መንግሥትና ህዝብ በያዙት ቁርጠኛ አቋም የተደናገጡና በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ ሆኖ የነበሩ አካላት በትግሉ ሂደት ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ መሆኑ እንቅልፍ ነስቷቸዋል። እረፍት አሳጥቷቸዋል።  የተጠያቂነት ሂደቱ ተጀምሯል። ተጠናክሮም ቀጥሏል።  

የተከሰተውን ይህን አጋጣሚ በመጠቀምና ሁከት ብጥብጡን መነሻ በማድረግ መንግሥትን በኃይል በመገልበጥ ሥልጣን ለመያዝ ምኞት ያላቸው ጠባብና የትምክህት ኃይሎች ሴራቸውን ጎንጉነዋል፡፡ ወዲያ ወዲህ ሲራወጡም ተስተውለዋል። እነዚህ ኃይሎች በተለይ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ግብ የሌለው ጥፋታቸውን ቀጥለውበታል።  

በተለይ እነዚህ ኃይሎች የጠባብነትና የትምክህት ያልተሳካ ጋብቻ በመፍጠር በህዝብ አመኔታ ወደሥልጣን መውጣት ሲያቅታቸው የመጨረሻ ዕድላቸውን ተጠቅመው በአመፅ ለማሳካት መሞከራቸው አይቀሬ ሆኗል። ዋና መንደርደሪያቸው በየትኛውም መልኩ ሥልጣን በመያዝ አገሪቷን ለኒዮሊበራል ኃይሉ አሳልፎ በመስጠት የራሳቸውን የግልና የቡድን ጥቅም ማስጠበቅ ይሆናል።

የኪራይ ሰብሳቢዎች አጀንዳ ለህዝቡ ምንም ጥቅም ባይሰጥም ዜጋውን በአካባቢና በኃይማኖት ወይም በሌላ ስሜት ሰለባ በማድረግና ወደቀረፁት አጀንዳ በማስገባት መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከራቸውም የሚጠበቅ ይሆናል። ሁሌም አንግበው የሚይዙት አጀንዳ የህዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ ባለመሆኑ አይቀናቸውም። ወደፊትም ቢሆን ይሳካላቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳው ግጭት በዚህ ቅኝት ሊታይ ይችላል።  

መንግሥት መላ አገሪቱን የማረጋጋት ሥራውን እያከናወነ ለችግሩ ተጠያቂ የሚሆኑ ኃይሎችን ለህዝብ በማጋለጥ ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ጀምሯል።  የወንጀል ሀሳቡ ጠንሳሽና አራማጆች ከየምሽጋቸው ከተደበቁበት እየወጡ ለህግ የመቅረባቸው ጉዳይ ጅማሮውን ይዟል። ተሸሽገው ከህዝብ እይታ ሊያመልጡ አይቻላቸውም። ተገቢውን ዋጋ ያገኛሉ፡፡

የነዚህ የጠባብ ኃይሎች ዋና ዓላማ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ትግሉን መጥለፍ ነው። መንግሥት ህዝብን አሳትፎ እነዚህን ኃይሎች የማጋለጥ ሥራውን ይበልጥ አጠናክሮ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሊገነዘቡት የሚገባ ቁምነገር ነገር ቢኖር መቼውንም ቢሆን ከህዳሴ ጉዟችን እንደማያስቆሙን ነው፡፡

በኢሕአዴግና አጋሮቹ የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት፤ በህዝቡ የተቀናጀ የፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ወደኋላ የሚጎትቱ አመለካከቶችንና ተግባራትን ለማስወገድና የህዝቡን የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ለመምራት አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በአጀንዳው ዙሪያም ህዝቡ በሙሉ አቅሙ በመሳተፍ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡

በዚህ ወቅት የህዝቡንና የመንግሥትን ትግል ለማኮላሸት ታጥቀው የተነሱ ፀረ ሠላምና ጥገኛ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ርብርብ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። ይህ ጥረታቸው የመጨረሻ የመፍጨርጨሪያ እድሜያቸው መሆኑ በግልጽ እየታየ መጥቷል። እነዚህ ቡድኖች ሁኔታዎችን ተረጋግቶ ማስተዋል የጎደላቸው የተወሰኑ የኅብረተሰብ አካላትን በማሳሳት ችግር ውስጥ መክተታቸው አልቀረም።

ዛሬ ላይ ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ በነበረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ሂደት ሁለት ቦታ ረግጠው የነበሩ አካላት በየጊዜው ከየተቀበሩበት ሁሉ ሳይቀር ነፍስ ዘርተው ብቅ ማለት ጀምረዋል። ይሁንና ህዝብና መንግሥት አንድ ሆነው የመረረ ትግል ለማድረግ መወሰናቸው ሳይገባቸው አልቀረም። ይህ የተደራጀ የህዝብና የመንግሥት የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደማይለቃቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።     

በ1999 ዓ.ም በወጣው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ስትራቴጂ ላይ በፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ከሚገጥሙ ፈተናዎች አንዱ በኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ውስጥ የሚደበቁ ትምክህትና ጠባብነት መሆናቸው በግልፅ ሰፍሮ ይገኛል። በዚህ መፅሃፍ ገፅ 84 ላይ የተቀመጠው እንዲህ ይላል። “ህዝቡ ከኪራይ ሰብሳቢነት ተጠቃሚ ባይሆንም ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ተፅዕኖ ውጭ ስለማይሆን ለመንግሥትና ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ባለህ ቀረቤታ ፍርፋሪ ይገኛል የሚል እምነት እንዲይዝ በሚያደርጉ ኃይሎች አስተሳሰብ ሥር እንዲወድቅ ስለሚደረግ በአካባቢ፣ በኃይማኖት፣ በብሄር ወዘተ…‘ላንተ ቆመናል’ በሚሉ አካላት አዝማሚያ ይኖረዋል” ይላል፡፡

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ውይይት በተካሄደበት አንድ መድረክ ላይ እንዲህ ብለው ነበር። “ካሁን በኋላ ሃሳባችንን እዚህ ጨርሰን እንውጣ፡፡ ውይይቱን ጨርሰን ስንወጣ የአካባቢና አብሮ አደጋችን እንዳይጠቃብን የሚለውን አስተሳሰብ ማቆም አለብን” የሚለው ቁርጠኝነት የተሞላበት ንግግር ዛሬም ድረስ ተጠቃሽ ነው።

እዚህ ላይ አንድ ነጥብ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል። ከሁሉም በፊት በመላ አገሪቱ ውስጥ ሠላም ከሌለ ስለ ልማትም ይሁን ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማሰብ አይቻልም። ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማቀንቀንም ብሎም መናገር ትርጉም አይኖረውም። ያለምክንያት አይደለም። እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም። አንዱ ያለሌላው አይቆምም። ይህን እውነታ ለማየት የኢትዮጵያን ያለፉት 27 ዓመታት ጉዞ መለስ ብሎ መቃኘት በቂ ይሆናል። ኢትዮጵያ በመላ አገሪቱ ሠላምን በማስፈን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን እውን ለማድረግ የተጓዘችበትን ረዥም መንገድ መፈተሽ ተገቢ ይሆናል።  

ይህ ጉዞ ጋሬጣዎች ነበሩበት። ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም። በአንድ በኩል ሠላማዊ መስለው በህገ ወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ፤ በሌላ ወገን ፀረ ኢትዮጵያ በሆኑ ኃይሎች ድጋፍ በተላላኪነት በተሰለፉ፤ በሌላኛው ዘውግ ደግሞ በጽንፈኛ የፖለቲካ አቋማቸው በሚታወቁና አገር ውስጥ ሆነው “በህጋዊ መንገድ እንታገላለን” በሚል ሽፋን አገሪቱ ከምትመራባቸው የህግ ማዕቀፎች ውጭ በመውጣት የተገኘውን አስተማማኝ ሠላም ለማደፍረስ በሚጣጣሩ ቡድኖች በርካታ ያልተሳኩ ጥረቶች ተደርገዋል።  

ይሁንና ሠላምን በፅኑ የሚሹት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያገኟቸው የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውጥኖች እንዳይቀለበሱ አድርገዋል። በመንገዳቸው ላይ ደንቃራ የሆኑትን ጠራርገው ጥሎ ለማለፍ ብርቱ ትግል አድርገዋል። ቀናው መስመር እንዳይጎረብጥ፣ ጉዞውም የኋሊት እንይታጠፍ በብርቱ ታግለዋቸዋል።  

በተለያዩ ወቅቶች እነዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በህጋዊና በሠላማዊ መንገድ ብቻ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ ተጠይቀዋል። ሠላምን አጥብቆ የመሻት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ እነዚህ ኃይሎች ቀናውን መንገድ ይከተሉ ዘንድም ተማጽዕኖ ቀቦላቸዋል – ምንም እንኳን ጆሮ ዳባ ልበስ ቢሉም። ለማንኛውም ለእኛ ሠላማችን ይብዛልን።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy