Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በመመካከር የማይፈታ ችግር የለም!

0 386

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በመመካከር የማይፈታ ችግር የለም!

                                                        ደስታ ኃይሉ

ኢህአዴግና ህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እያደረጉት ያሉት ድርድር አገራችን ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራለዊ ሥርዓት ያለበትን የዴሞክራሲ ደረጃ የሚያመላክት ነው። ይህ የፓርቲዎቹ ድርድር አገራችን ውስጥ የትኛው ዓይነት ችግር ቢፈጠር ሥርዓቱ በመመካከር፣ በመወያየትና በመደራደር ምላሽ መስጠት የሚችል መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ውስጥ ዴሞክራሲ የሞትና የሽረት ጉዳይ ሆኗል። እንደሚታወቀው ሁሉ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባሉባት አገራችን ውስጥ ሁሉንም መብቶች አቻችሎ ህዝቦችን ለመምራት ፌዴራሊዝም ተገቢ አማራጭ ነው። ሥርዓቱ የህዝቡን ሁለንተናዊ መብቶች በተሟላ መንገድ ለማስጠበቅ ወደር የማይገኝለት መስመር ነው።

በፌዴራላዊ ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል። ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል።

መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የሥርዓቱ ውጤት መሆኑ አይካድም።

ዴሞክራሲውን ለማጠናከርም መንግስት ጠንካራ ርምጃዎችን ወስዷል። ኢህአዴን ጨምሮ 16 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ድርድር የዴሞክራሲው መገለጫ ነው ማለት ይቻላል።

ሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች በዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ አንድ ሃሳብ በሌላኛው እንደሚሸነፍና ምናልባትም አንዱ በሌላኛው ሃሳብ ተማርኮ የራሱን በመተው የዚያኛውን ወገን አስተሳሰብ የሚያራምድበት ጊዜ መኖሩም መዘንጋት የለበትም። ይህ የሚሆነውም ዴሞክራሲ ለመሪው ሳይሆን ለተመሪው የሞራል ግዴታ ያለበት በመሆኑም ጭምር ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ “እኩይ” እና “ሰናይ” ተብለው የሚፈረጁ የሞራል ዘውጎች አሉ።

 

ዴሞክራሲ በማህበረሰቡ ዕይታ የተቃኘ በመሆኑ “ለሰናይ” ምግባሮች ቅድሚያ ይሰጣል—ተከታዩ ማህበረሰብ የሚፈልገውን የሞራል ፈርጅ ካልወገነ ሊከተለው የሚችለው ሊቅም ይሁን ደቂቅ የለምና።

 

በመሆኑም ተደራዳሪ ወገኖች ህብረተሰቡ የሚፈልገውን “ሰናይ’ መንገድ መከተል ብቻ ሳይሆን መንገዱንም ለህብረተሰቡ በማሳየት ፋና ወጊ መሆንም አለባቸው። አሊያ ግን ሁሉንም ተግበራት በአንክሮ በሚከታተለው ህዝብ ዓይን ውስጥ ለትዝብት መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም።

 

እርግጥ ህዝብ ሁሉንም ነገር የሚያይ፣ ሚዛናዊና ለየትኛውም ወገን የማይወግን በመሆኑ፤ ማን ምን እንደሚሰራ፣ የትኛው ወገን ሀገሩንና እርሱን ማዕከል አድርጎ እንደተንቀሳቀሰ፣ የትኛውስ ከዚህ ውጭ ሆኖ ራሱን ብቻ በማዳመጥ እንደተንቀሳቀሰ ያውቃል። እናም በእንቅስቃሴው ልክ ይሰፍረዋል። በሰፈረው ልክም ወገንተኝነቱን ያረጋግጣል፤ በካርዱም ይሁንታን ይቸራል።

 

ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያደርገው ድርድር በመወያየት እዚህ አገር ውስጥ የማይፈታ ችግር አለመኖሩን የሚያረጋግጥ ነው። የውይይቱ፣ የክርክሩና የድርድሩ ዋነኛ ጉዳይ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ይበልጥ ለማስፋት ታስቦ ሲሆን፣ በዚህ ቀና መንገድ ዙሪያ መጓዝ ደግሞ ተቃዋሚዎችም ይሁኑ ገዥው ፓርቲ መሰባሰብና የሚበጀውን ለህዝባቸው ማበርከት ይኖርባቸዋል።

 

መወያየት ዴሞክራሲያዊ ባህል ነው። ውይይት የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መገለጫ ነው። ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን በጠረጴዛ ውይይት የመፍታት አካሄድ የዘመናዊነት መገለጫ እየሆነ ነው። ይህ ሁኔታም በተለይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በሚከተሉ ሀገሮች ውስጥ ትክክለኛ አካሄድ እየሆነ መጥቷል። ይህን ማንም ሊሽረው አይችልም። ሰጥቶ መቀበልና ስምምነት በማይኖርባቸው ጉዳዩች ላይም ተከራክሮ ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት መንገድ ያለንበት ጊዜ መገለጫ ሆኗል።

 

እንደሚታወቀው የተቃውሞውም ይሁን ገዥው ፓርቲ እንወክለዋለን የሚሉት ይህንን ህዝብ ነው። የሌላን ሀገር ህዝብ አይደለም። በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች የሚደግፋቸውን ህዝብ ፍላጎት ብሎም የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለአደጋ ማጋለጥ አይኖርባቸውም። የሚወያዩት፣ የሚከራከሩትና የሚደራደሩት ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ነው።

 

ከዚህ ውጪ ለየትኛውም አካል አጀንዳ ማራገቢያነት ፍጆታ ሊውሉ አይገባም። በውይይታቸው ላይ ሊያነሱት የሚገባው የህዝባቸውንና የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ መሆን ይኖርበታል።

 

እርግጥ ተግዳሮቶች በየትኛውም ሀገር ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ። በመገንባት ላይ ያለው የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ጨርቃ ነው። በሚገባው ደረጃ አልጎለበተም። እናም በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ችግሮች መኖራቸው አይቀርም።

 

ዋናው ጉዳይ ችግሮቹን በአግባቡ ከመፍታት ላይ ነው። ቁም ነገሩ በውይይት የሚፈቱ ጉዳዩችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መፍታት መቻሉ ላይ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝብ እስካለ ድረስ በሰላማዊ መንገድ የማይፈቱ ችግሮች አይኖሩም።

 

ለዘብነት ያህል በቅርቡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያካሂደየት ደርድር በህዝቡ ግት አማካኘነት የተፈጠረ መሆኑን ሲገልፁ አድምጠናል። ውይይቱ ሁሉም ወገን ሊያገኘው የሚችለውን ህዝባዊና ሀገራዊ ጥቅምን ብቻ ሊማክል ይገባል። በየትኛውም የውጭ ሃይል አሊያም በሀገራችን ህጋዊ ስርዓት ውስጥ የማያልፉ ሃይሎች ሊጠለፍ አይገባም።

 

የአንድ ውይይት ማጠንጠኛ መሆን ያለበት የሀገራችን ጅምር ዴሞክራሲን ከማስፋትና ላላፉት 26 ዓመታት እየጎለበተ የመጣውን የፖለቲካ ምህዳር ይበልጥ እንዲሰፋ ለማድረግ ካለው ፋይዳ አኳያ ነው። እናም መወያየቱም፣ መከራከሩም ይሁን መደራደሩ ግቡ በአገር ውስጥ ያለን ችግር ከመፍታት አንፃር መታየት አለበት። እስካሁን ኢህአዴግና 15 ተቃዋሚዎች ያደረጉት ድርድር በመመካከርና በመወያየት የማይፈታ ምንም ዓይነት ጉዳይ አለመኖሩን አረጋጋጭ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy