Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በባለጋራነት የሚያተያዩ ቀዳዳዎችን እንድፈን

0 295

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በባለጋራነት የሚያተያዩ ቀዳዳዎችን እንድፈን

ብ. ነጋሽ

የሃገር አንድነት የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሁሉም ወገኖች፣ ተቃራኒ በሆኑ ጭምር የሃሳብ ማንጠልጠያ ሆኖ ሲነገር ኖሯል። አጼ ቴዎድሮስ እስካሁን ስማቸው የሚነሳው የኢትዮጵያን አንድነት ለመፍጠር አደረጉት በተባለው ጥረትና ራዕይ ነው። ዘመናዊ በሚባለው የሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ በዘውዳዊ ሥርአት የተስፋፈኒነት ስትራቴጂ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ወሰን የፈጠሩት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ የኢትዮጵያን አንድነት በመፍጠርና በማጽናት በአውራነት የሚጠቅሷቸው በርካቶች ናቸው። ከአጼ ምኒልክ የተረከቧትን ኢትዮጵያ እንደወረደ ሲገዙ የኖሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም በሃገር አንድነት ቃፊርነት ይጠቀሳሉ። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥልጣን የተረከበው ዘውዳዊውን ሥርአት ሲያገለግል የነበረው ወታደራዊ ደርግም የሃገር አንድነት ጠባቂ ከእኔ በላይ ለአሳር ባይ ነበር። ወታደራዊው ደርግ የብሄሮችና ብሄረሰቦች ነጻነት ጥያቄ ይንጠው በነበረበት ወቅት፣ ህዝቡን ከጎኑ ለማሰለፍ የሃገር አንድነት ሊፈርስ ነው! የሚል አጀንዳ ነበር የሚያነሳው።

በሌላ በኩል፤ የመጨረሻውን አሃዳዊ የመንግሥት ሥርአት የነበረውን ደርግ ያስወገዱት የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በ1983 ዓ/ም ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ ቀጣይ የሃገሪቱን እጣ ፈንታ ለመወሰን ሲመክሩ፣ ዋና አጀንዳቸው የሃገር አንድነት ነበር። እኛ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ላይ የምንኖር ብሄሮችና ብሄረሰቦች፣ ፈጣሪ አንዳችንን ከሌላችን በቋንቋ፣ በመገኛ መልከዓምድር ለያይቶናል፤ የየራሳችን ባህልና ወግ አለን፤ የጋራ ታሪክ ሊኖረን ቢችልም የየራሳችን ታሪክም አለን፤ ይህ ልዩነት እንደተጠበቀ አንድነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው የሚል አጀንዳ ላይ ነበር የመከሩት።

ልብ በሉ፤ የአሃዳዊ መንግሥት ፈጣሪዎችና ገዢዎችም፣ የህብረ ብሄራዊ ሥርአት ወይም የብዝሃነት ሥርአት አመለካከት አራማጆችም ስለ ሃገር አንድነት ነው የሚያወሩት። ይህ እንደቀላል የምንናገረው አንድነት የሚል ቃል የተሸከመውን እሳቤ ትኩረት ሰጥቶ መመለከትን የግድ ይላል። አንድነት ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እንዴት ይታያል?

ስለአንድነት ሲወራ በውስጠታዋቂ ልዩነት አለ። አንድ የሚሆኑት የተለያዩ ነገሮች ናቸውና። አንድ ነገር ብቻ ባለበት ሁኔታ አንድነት የሚለው እሳቤ ትርጉም ያጣል። አንድነትና ልዩነት ተያያዥ እሳቤዎች ናቸው። እንግዲህ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ያነሳናቸው ሁለት ወገኖች – የአሃዳዊ ሥርአትና የብዝሃነት ሥርአት አራማጆች ስለሃገር አንድነት ሲያነሱ፣ ሃገሪቱ የልዩነቶች ስብስብ ወይም ብዝሃነት ያላት መሆኗን ታሳቢ አድርገዋል። ይሁን እንጂ በሁለቱ ወገኖች መሃከል ሰፊ የአመለካከት ልዩነት አለ። ልዩነቱ የመነጨው ብዝሃነት በሚስተናገድበት መንገድ ላይ ነው። አሃዳዊያኑ ለብዝሃነት ወይም ለልዩነት እውቅና መስጠት አይፈልጉም። ልዩነቶች በአንድ ብሄራዊ ማንነት ተጨፍልቀው አንድ ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊነት የመፍጠር አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ለእነዚህ ወገኖች አንድነት፣ የተለያየ ማንነት ያላቸው ህዝቦች አንድነት ሳይሆን፣ ልዩነቶች ተጨፍልቀው የሚፈጠር አንድነት ነው። በመሆኑም አንድነቱ የህዝቦች ሳይሆን የመልከዓምድር ይሆናል። የዚህ አይነት አንድነት መነሻ ህዝብ ሳይሆን ግኡዘ መሬት ወይም የሃገር ወሰን ነው።

በሌላ በኩል፣ የብዝሃነት አንድነት አመለካከት አራማጆች፣ እያንዳንዱ የየራሱ ማንነት (ቋንቋ፣ ባህልና ወግ፣ ታሪክ) ያለው ህዝብ (ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ) በቋንቋው የመስራት፣ የመዳኘት፣ የመማር፣ ባህሉን የማጎልበት፣ ታሪኩን የመንከባከብና የማሳወቅ . . .ቡድናዊ  መብትና ነጻነት አለው፤ ይህን ቡድናዊ መብትና ነጻነቱን እውን ለማድረግ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ሊጠበቅ የግድ ነው ከሚል እምነት ይነሳሉ። አንድነት ልዩነቶች እንደጠጠበቁ በህዝቦች መሃከል የሚፈጠር የልዩነቶች አንድነት ነው ባዮች ናቸው። ስለአንድነት ሲያነሱ ስለወሰን ሳይሆን ስለብዝሃ ህዝብ አንድነት ነው። የሃገር ወሰን እነዚህ የተለያዩ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩ ኩታ ገጠም ህዝቦች በአንድነት ለመኖር ተስማምተው የሚፈጥሩት መልከዓምድር ወሰን ነው።

እንግዲህ፤ የአሃዳዊ ሥርአት አራማጅ ነገሥታትና የወታደራዊ  ቡድን መንግሥታት በሃገሪቱ ያሉ የተለያዩ ብሄራዊ ማንነቶችን ጨፍልቀው አሃዳዊ ሥርአት ለመመስረት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የተከተሉት ስትራቴጂ የየራሳቸው ማንነት ባላቸው ህዝቦች የመብትና ነጻነት ትግል ሳይሳካ ቀርቷል። ማንነቶች የተጨፈለቁበት አሃዳዊ ሥርአት መዝለቅ ያልቻለው በአንድ ቡድን ፍላጎት አይደለም። በሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄና ትግል እንጂ።

የሚገርመው ሃገሪቱን አሁንም በመልከዓምድር ሸንሸነው ብሄሮችና ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር በማይችሉበት ሁኔታ በማስተዳደር አሃዳዊ ሥርአት የመመስረት ህልም ያላቸው የቀድሞ ሥርአት ቅሪቶች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የመሰረቱትን የሃገር አንድነት ኢህአዴግ፣ ከኢህአዴግም ህወሃት ያመጣው ይመስላቸዋል። የአብዛኞቹ ተቃውሞ ኢህአዴግና ህወሃት ላይ ማተኮሩ ለዚህ አስረጂ ነው። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ህወሃት ብሄራዊ ጭቆና ከወለዳቸው የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የነጻነት ትግል ድርጅቶች አንዱ ነው። እርግጥ በሆነ ታሪካዊ አጋጣሚ በትግሉ ሂደት ከሌሎች ጎልቶ ወጥቶ ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ግን ሥርአቱ እንዲፈጠር የማድረግ አቅምና ብቃት አያስገኝለትም። ሥርአቱ በሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ትግል በተገኘ ድል መሰረት ላይ በሁሉም ስምምነት የተገነባ ነው። የሃገሪቱ ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ የወለደው እንጂ፣ በአንድ ቡድን ፍላጎት ወይም በአጋጣሚ የተገኘ አይደለም።

ያም ሆነ ይህ፤ አሁን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሚኖሩበት ፌደራላዊ አንድነት ያላት ሃገር መስርተዋል፤ በልዩነት ውስጥ ያለ የህዝቦች አንድነት ያለው ፌደራላዊ ሥርአት። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነት ያለውን ፌደራላዊ ሥርአት ተስማምተው የመሰረቱበት የቃል ኪዳን ሰነድ በሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመመስረት ባሻገር በመሃከላቸው ያለውን ትስስር፤ የወንድማማችነት ስሜት ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 88 ፖለቲካ ነክ አላማዎች በሚል ርዕስ ስር፣ በንኡስ አንቀጽ 2 ላይ፤ መንግስት የብሄሮችን፣ የብሄረሰቦችን፣ የህዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነት፣ አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት ይላል። ይሄው ድንጋጌ ምንም ሳይለወጥ በዘጠኙም ክልሎች ህገመንግስቶች ላይ ሰፍሮ እናገኛቸዋለን። ይህ ድንጋጌ የፌደራል መንግስትም፣ የየክልል መንግስታትም የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችን፣ ህዝቦችን ማንነት የማክበርና ትስስራቸውን፤ ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩ እርምጃዎችን የመውሰድ ህገመንግስታዊ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ያመለክታል።

ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሃከል አንድነትንና ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ እርምጃዎች በመውሰድ ረገድ የፌደራል መንግስቱም ሆነ የክልል መንግስታት እስካሁን የሚገባቸውን ያህል ሰርተዋል የሚል እምነት የለኝም። የፌደራል መንግስት በዓመት አንድ ጊዜ በየክልሉ በመፈራረቅ ከሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ያለፈ ሊጠቀስ የሚችል እርስ በርስ የሚያስተዋውቅና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር ተግባር አከናውኗል ለማለት አያስደፍርም። ክልሎችም ቢሆኑ ከዚህ የተለዩ አይደሉም። ሁሉም በየራሳቸው ጉዳይ ተጠምደው ነው ያለፉ ሁለት ተኩል አስርት ዓመታትን ያለፍነው። እናም በመሃከላችን ሸለቆ እየተፈጠረ የመጣበት ሁኔታ በተጨባጭ ታይቷል። ትምክህተኞችና ጠባቦች ደግሞ ሸለቆውን ማስፋት የሚያስችላቸው እድል አግኝተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥሩ ጅምሮች ይታያሉ። ከእነዚህ መሃከል በአማራና በትግራይ ክልሎች መሃከል ሁለት ጊዜ የተካሄዱ የህዝብ ለህዝብ የምክክር መድረኮች፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች መሃከል እንዲሁም ከአንድ ሳምንት በፊት በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ክልሎች መሃከል የተካሄዱት የህዝብ ለህዝብ የጋራ የምክክር መድረኮች ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ የህዝብ ለህዝብ የምክክር መድረኮች በሁለም ክለሎች መሃከል ቢጀመሩና የየወቀቱ የጋራ ጉዳዮችን መሪ ሃሳብ እያደረጉ ሁኔታዎች በጠየቁትና በፈቀዱት ልክ ቀጣይነት ቢኖራቸው መልካም ነው።

ሁላችንም እንደምናወቀው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድንበርን ሰበብ በማደረግ በተዋሳኝ ክልሎች መሃከል ገጭቶች የሚቀሰቀሱበት ሁኔታ አጋጥሟል። በትግራይና በአማራ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል የተፈጠሩትን ግጭቶች ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያየ ሰበብ የብሄር ግጭት ገጽታ ያላቸው መቆራቆሶች እዚያም እዚህም በተለያየ የማይረባ ሰበብ እየተለኮሰ ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሚሆንባቸው አጋጣሚዎችን ማስተናገድ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

እነዚህ ግጭቶችና መቆራቆሶች ብሄርን መሰረት ያደረጉ ቢመስሉም ጠለቅ ብለን ስንመለከታቸው የብሄር ግጭት አለመሆናቸውን መረዳት ይቻላል። አንዱ ብሄር ሌላውን ብሄር በበዳይነት ፈርጆ ወይም ጠርጥሮ ለማጥቃት በመነሳት የተፈጠሩ ግጭቶች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ አጋጣሚዎችን በመጠበቅ ግጭትን ለራሳቸው የጠባብነትና የትምክህት የፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያነት በሚለኩሱ ወገኖች ቅስቀሳ በተወሰኑ አካባቢዎች ዪያጋጥም ነው። ግጭቶቹ፣ በዋና ተዋናይነት ግጭቱ ውስጥ ለመሳተፍ ተመልምለውና ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ፊትአውራሪነት የሚከናወኑ ናቸው። የህዝብ ለህዝብ ግጭቶች አይደሉም።

ለምሳሌ በአማራና በትግራይ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው ግጭት ቀመስ ሁኔታ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ህዝቦች መሃከል የተፈጠረ አልነበረም። እርግጥ ነው በአካባቢው ሊፈታ ይገባው የነበረ ብንዝህላልነት ችላ የተባለ ከወሰን መካለል ጋር የተያያዘ ጥያቄ ነበር። ይህ የወሰን ጥያቄ ቢኖርም ሁለቱ ህዝቦች በወሰን ይገባኛል ጥያቄ ጠመንጃ አልተታኮሱም፤ አንተ ከዚህ ውጣ፣ አንተ ከዚያ ወጣ አልተባባሉም። በዘመናት አብሮነት ባካበቱት ወንድማማችነትና መከባበር ላይ ተመስረተው፣ አላስፈላጊ ግጭት ተቀስቅሶ ደም እነዳይቃቡ ተጠንቅቀው ሰላማቸውን አስጠብቀው መኖራቸውን ቀጥለው ነበር።

ከዚህ ከሁለቱ ክልሎች ከአዋሳኝ አካባቢ ርቆ ግን በአሜሪካ ጭምር በለው! በለው! መባባሉ ተጧጡፎ ነበር። ከወሰን ራቅ ባሉ አካባቢዎች ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረበት፣ ሰዎች የተፈናቀሉበት ሁኔታም ነበር። ይህ ጽውነታ ግጭቱና በጥርጣሬ መተያየቱ በህዝቦች መሃከል የተፈጠረ አለመሆኑን፣ የወሰን መካለል ጥያቄን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ትምክህተኞች የፈጠሩት መሆኑን በግልጽ ያሳያል። የዚህ አይነት ችላ ከተባለ ከራርሞ ለግጭት መልካም አጋጣሚ ሊሆን የሚችል ችግር እንዳይፈጠር፣ የጋራ ጉዳዮችን ተማክሮ ለመፍታት የሚያስችሉ የህዝብ ለህዝብ የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት ወሳኝ ወሳኝ ነው። የህዝብ ለህዝብ የጋራ መድረኮች ዘላቂ ወንድማማችነትንም ያጠናክራሉ። የአማራና የትግራይ ህዝቦች የጋራ መድረክ ተዘጋጅቶ ህዝቡ ተቀራርቦ የሚወያይበት እድል ካገኘ በኋላ ተንጠልጥሎ ለግጭት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮ የቆየው ወሰን የማካለል ተግባር በሰላማዊ መንገድ መከናወኑ ለዚህ ተጨባጭ አስረጂ ነው።

ከዚህ በኋላ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ህዝቦች መሃከል የተደረገው የጋራ የምክክር መድረክም ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ የመጣውን በጥርጣሬ የመተያያት ዝንባሌ በማስቀረት ወንድማማችነትንና መከባበርን የሚያጠናክር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ሁለቱ ህዝቦች በመሃከላቸው ችግር ተፈጥሮ አያውቅም። ይሁን እንጂ ትምክህተኞችና ጠባቦች ለራሳቸው ዓላማ በሚነዙት ውዥንብር አንዱ ሌላውን በባለጋራነት እንዲጠረጥረው የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህን የባላጋራነት ጥርጣሬ በማጥፋት ወንድማማችነትንና መከባበርን፣ ብሎም ሰላምን ለማረጋገጥ ሁለቱን ህዝቦች የሚያቀራርቡ መድረኮች ማዘጋጀት የማይተካ ሚና አላቸው።

ጎልቶ የወጣ በጥርጣሬ የመተያያት ችግር ባይኖርም በቤኒሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ህዝቦች መሃከል የተካሄደው የጋራ መድረክም አንዱ ሌላውን እንዲፈልገው በማድረግ ወንድማማችነትን ለማጠናከር የሚያስችል ነው። የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በቅርቡ ቢሾፍቱ ላይ ባካሄዱት የጋራ የምክከር መድረክ አዋሳኝ አካባቢዎች የጋራ የማህበራዊና የመሰረተ ልማቶችን ለማካሄድ መስማማታቸው ይህን ያረጋግጣል።

በአጠቃላይ በልዩነት ውስጥ ያለውን የሃገሪቱን የህዝቦች አንድነት ለማጠናከር፣ የህዝብ ለህዝብ ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ መድረኮች በሁሉም ክልሎች መሃከል ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታችን መነሻ በማድረግ ሊካሄዱ ይገባል። የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ህዝቦች በባለጋራነት እንዲተያዩ ሊያደርጉ የሚችሉ ክፍተቶችን ይደፍናሉ፤ በዚህም ሰላምን ያረጋግጣሉ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy