Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በጥቂቶች እኩይ ዓላማ የማይሸረሸሩት ድንቅ እሴቶቻችን

0 417

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በጥቂቶች እኩይ ዓላማ የማይሸረሸሩት ድንቅ እሴቶቻችን

                                                           ቶሎሳ ኡርጌሳ

ሀገራችን የውጭ ስደተኞችን እጆቿን ዘርግታ የምትቀበልና የምታስተናግድ ከመሆኗም በላይ፤ ባላት ውስን አቅም ስደተኞችን የምታስተምርና ለስራ የምታበቃ ናት። የሀገራችን ህዝብ እንግዳ ተቀባይ፣ ያለውን አካፍሎ የሚበላ፣ ደግና ሩህሩህ መሆኑም ለዚህ የስደተኞች ተቀባይነታችን ዓይነተኛ ሚና አለው።

ታዲያ እነዚህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ እሴቶች በጥቂቶች ድብቅና እኩይ ዓላማ ሊሸረሸሩ አይችሉም። እናም በእነዚህ ጥቂት ሃይሎች እኩይ እሳቤ የሀገራችን ሰላም መደፍረስ የለበትም፣ ልማቷም መደናቀፍ አይገባውም፤ መልካም ገፅታዋም መጉደፍ አይኖርበትም። በአሁኑ ወቅት ጥቂቶች ድብቅ እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉት ጥረት ህዝባዊ መሰረት የሌለው ነው። እናም ተግባሩን ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በፅናት ሊታገሉት ይገባል። ያስፈልጋልም።

ጥቂት እኩይ ሃይሎች ሀገራችን ህዝቦች እየጎለበተ የመጣውን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ለመሸርሸር እየተራወጡ ናቸው። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል። ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ስለሆነ ነው።

ርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል። በመሆኑም ፅንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎችና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት አይከሰትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው። ይህንን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋት ተገቢ ነው። የግድም ጭምር ነው።

ዛሬ ስለ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የምናወጋው የጥበትና የትምክህት ሃይሎችን የምንመክትበት ዓይነተኛ የዴሞክራሲ መሳሪያ ስለሆነ ነው። የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ የሚያራምዱ ጥቂት ሃይሎች የዴሞክራሲ ብሔርተኝነት ነገር አይዋጥላቸውም። ጠባቡ የጥበት መንገዱ ስለሚዘጋበት፣ ትምክህቱም የትምክህተኝነት አውራ ጎዳናው ሙሉ ስለሚዘጋበት ይህን አስተሳሰብ ለመስማት አይፈልግም። ዳሩ ግን ነገርዬው “ብዙሃን ይመውዑ” (ብዙሃን ያሸንፋሉ እንደማለት) ዓይነት በመሆኑ ለዚህች ሀገር ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ አይታበይም።

ምንም እንኳን ባለፉት 26 የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት ትምክህትና ጠባብነትን ለመዋጋት በርካታ ሥራዎች ቢከናወኑም፤ አመለካከቱ አልፎ አልፎ የሚያንሰራራው በኪራይ ሰብሳቢነትና ባልተገባ ጥቅም በሚሹት አካላት አማካኝነት በመሆኑ ሁለቱን ማነቆዎች ከህዝቡ ጋር በመታገል ለውጡን ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

ርግጥ በአንዳንድ አካባቢዎች በየሰበብ አስባቡ ‘የትምክህት ሐሳባችንን በነፃነት እንግለፅ፣ አትንኩን’ የማለት ነገር ይስተዋላል። ይህንን አመለካከት መጠጊያ የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውም ግልፅ ነው። እነዚህ ወገኖች በህገ መንግስቱ መሰረት ሃሳባቸውን የመግለፅ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ድርጊታቸው የህብረተሰቡን ሰላም በመንሳት ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ የሚፈጥር ከሆነ ከህግ የበላይነት አኳያ መታየት ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው። እናም በህዝባዊ ወገንተኝነት መንፈስ ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ የሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ‘የእኔ ህዝብ ብቻ ትክክል ነው’ ከሚል ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብ መውጣት አለበት። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲያከብር እርሱም በፊናው መከበርን ይጎናፀፋል።

ርግጥ ባለፉት ስርዓቶች አንድን ህዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ በድሎት ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ ግን በወቅቱ ከነበሩት ገዥ መደቦች ጋር የሚያያዝ እንጂ የትኛውንም ህዝብ የሚመለከተው ጉዳይ አይደለም።  

እኔ እስከሚገባኝ ድረስና እንደማውቀው ዛሬ ላይ አንድ ብሔር የበላይነት ሀገራችን ውስጥ የለም። ልኑር ቢልም ህገ መንግስቱም ይሁን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አይፈቅድለትም። እዚህ ሀገር ውስጥ እየተገነባ ያለው ስርዓት ለእንዲህ ዓይነቱ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በር የሚከፍት አይደለም። ‘የአንድ ብሔር የበላይነት’ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ አፈ ታሪክ እንጂ በገሃዱ ዓለም ላይ ያለ እውነታ አይደለም። አሊያም ልብ ወለድ ድርሰት ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩበት ህገ መንግስታዊ ስርዓት የየትኛውም ብሔር ወይም ብሔረሰብ የበላይነት ሊረጋገጥ የሚችልበት አግባብ የለም። ሊኖርም አይችልም። ታዲያ እንዲህ ዓይነቶቹን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በሌለ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ በርካሽ ፕሮፖጋንዳ በማጋጋም ትርፍ ለማግኘት መሞከር አስቂኝ ነው። ተግባሩም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሳካ አይሆንም። ምክንያቱም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ውጤት እያስገኘ ከመሆኑም በላይ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ ላይ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ቀጥሎ መከባበርን፣ መቻቻልንና በአንድነት ለጋራ ዓላማ መሰለፍን እያረጋገጠ ስለሆነ ነው።

ርግጥ አንዳንድ የትምክህትና የጥበት ኃይሎች ህብረተሰቡን በተሳሳተ ጎዳና ሊመሩት ይችላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለን የህዝቦች መስተጋብራዊ ግንኙነቶችን እየመዘዙ እነርሱ ራሳቸው የሚያምኑበትን ‘ከሁሉም የበላይ ነን’ የሚል የቁራ ጩኸታቸውን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሊግቱን ይፈልጋሉ። ዳሩ ግን ይህን መሰሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ምልከታ ሀገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጋር “ሆድና ጀርባ” በመሆኑ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም።

እንዲህ ዓይነቱ ፌዴራላዊ ስርዓቱም ይሁን ህዝቡ የማይደግፈውን የዴሞክራሲ ፀር አስተሳሰብን ሁሉም በየደረጃው ሊታገለው የሚገባ ይመስለኛል። አስተሳሰቡን ‘መንግስት ለብቻው ይወጣው’ ብለን የምናልፈው ከሆነ፣ ምንም ለውጥ ልነመጣ አንችልም። እናም ‘ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም፣ ለሃምሳ ሰው ጌጥ’ መሆኑን በተግባር በማሳየት ይህን መሰሉን እኩይ ሴራ የሚያራምዱ ጥቂት ኃይሎችን ልንታገላቸውና ልንኮንናቸው ይገባል።

ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የወል እሴት እየተገነባ ነው። ኢትዮጵያዊነት ከራሱ አልፎ እንግዳ ተቀባይነትም ጭምር ነው። አብሮ መብላትና መጠጣት ነው። ሆኖም ጥቂት እኩይ ዓላማን የሚያራምዱ በጠባብነት አስተሳሰብ ውስጥ የሚዳክሩ ሃይሎች እነዚህን ድንቅ እሴቶቻችንን ሊበርዙት እየሞከሩ ነው። እናም በጋራ “አይቻልም” ማለት ይኖርብናል።

እነዚህ ጥቂት የእኩይ ሰራ አራማጆች ሀገራዊ ጥቅሞችን በራሳቸው ምህዳር ውስጥ ብቻ እየተረጎሙ መጠቀም የሚሹ ናቸው። ይህም በጋራ ለማደግ ያሰብነውን የወል ምልከታ የሚሸረሽርና የሚያዛባ ሸውራራ እይታ ነው። እንዲህ ዓይነቱን የጠበበ መንገድ የምናስተናድበት ምህዳር እዚህ ሀገር ውስጥ እንደሌለ በመግለፅ፤ ድንቅ እሴቶቻችን እንይሸረሸሩ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy