CURRENT

ባንኩ ጥቁር ገበያን የሚያዳክም መመሪያ በማዘጋጀት የንግድ ባንኮች እንዲያስፈፅሙት እያደረገ ነው

By Admin

December 18, 2017

አስመጪዎች ለሚያስመጡት እቃ የሚጠይቁትን የውጭ ምንዛሪ በአለም አቀፍ ዋጋ እንዲሆን በማስገደድ የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያን ለማዳከም መመሪያ ማውጣቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

ባንኩ አስመጪዎች የባንክ ፍቃድ ለማግኘት ብቻ ለሚያስመጡት እቃ የማይመጥን የውጭ ምንዛሪን በመጠየቅ ቀሪውን ከጥቁር ገበያ እንደሚያሟሉ ደርሼበታለሁ ብሏል ።

አሁን የንግድ ባንኮች ተግባራዊ እንዲያደርጉት የሰጠሁት መመሪያ ግን የትኛውም አስመጪ ለሚያስመጣው እቃ በአለም አቀፉ ዋጋ መሰረት የውጭ ምንዛሪ እንዲጠይቅ ያስገድዳል ነው ያለው።

በዚህም አስመጪዎች ሌላ የውጭ ምንዛሪ ገበያን እንዳይጠቀሙ በማድረግ ጥቁር ገበያን አዳክምበታለሁ ብሏል ባንኩ።

የብሄራዊ ባንኩ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው፥ የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ማሻሻያ የታለመለትን ጥቅም እንዲያስገኝ ጥቁር ገበያን የሚያዳክም መመሪያ መውጣቱን ተናግረዋል።

መመሪያው አስመጪዎች እቃን ለማስመጣት ከባንክ ፍቃድ ወስደው የውጭ ምንዛሪ ሲጠይቁ፥ የሚጠይቁት የውጭ ምንዛሪ የሚያስመጡት እቃ በሚያወጣው አለም አቀፍ ዋጋ ልክ እንዲሆን የሚያስገድድ ነው፤ ይህ ካልሆነ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ወይም ኤል ሲ መክፈት እንደማይችሉ በመጥቀስ።

ዋና ኢኮኖሚስቱ እንደሚሉት፥ ይህ የሆነበት ምክንያት አስመጪዎች የባንክ ፍቃድ ለማውጣት ሲሉ ብቻ ለሚያመጡት እቃ የማይመጥን የውጭ ምንዛሪ እየጠየቁ ቀሪውን ከጥቁር ገበያ እንደሚያሟሉ ስለተደረሰበት ነው።

አሁን ላይ ባንኩ ያዘጋጀው አዲሱ መመሪያ ለንግድ ባንኮች ተላልፎ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩንም ይናገራሉ።

ስለዚህ ከአሁን በኋላ አንድ አስመጪ ለሚያስመጣው እቃ የሚያስፈልገው አለም አቀፍ ዋጋ 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከሆነ መጠየቅ ያለበት 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የግድ መሆን አለበት ብለዋል።

እንደ ብሄራዊ ባንኩ እምነት፥ አዲሱ መመሪያ ቢያንስ በባንኮች በኩል በህግ ክፍተት ምክንያት የተበረታታውን ጥቁር ገበያ የማዳከም ብቃት አለው።

አንድ አስመጪ ለሚያስመጣው እቃ የግድ አለም አቀፍ ዋጋን ጠይቅ ከተባለ፥ ዋጋ አሳንሶ የውጭ ምንዛሪ ስለማይጠይቅ ላነሰው ዋጋ ጥቁር ገበያ ሄዶ ምንዛሪን መሙላት አይችልም።

ይህ ደግሞ በሌላ በኩል በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ይቀንሳል፥ የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ የውጭ ምንዛሪን ወደ ባንክ የመውሰድ አቅም ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የወጪ ንግድ አፈጻጸምን በማሳደግ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማስተካከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲዳከም አድርጎ ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ የንግድ ባንኮች ለሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚሰጡት ብድር ዓመታዊ እድገቱ ከ16 በመቶ እንዳይበልጥ በማድረግ፥ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ ላላቸው ዘርፎች የሚሰጠው ብድር ግን ገደብ እንዳይጣልበት የሚያደርግ መመሪያን አውጥቶ ተግባራዊ እንዲሆን ለንግድ ባንኮች መመሪያ አስተላልፏል።

በአምራች ዘርፍ ላይ ላሉ ላኪዎችም የውጭ ምንዛሪ የሚስፈልግ በመሆኑ የግል ንግድ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ በገዙበት ዋጋ እንዲሸጡ በማድረግ ንግድ ባንክ ብቻውን የሚሰራውን ስራ እንዲጋሩት በማድረግ ላይ ነው።

በካሳዬ ወልዴ