Artcles

ብልህ ከጎረቤት ይማራል

By Admin

December 28, 2017

ብልህ ከጎረቤት ይማራል

 

ስሜነህ

 

ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ አልሳተፍበትም ባለው የኬንያ ዳግም ምርጫ ተፈጥሮ የነበረውን እና ለብዙ ሰዎችም ህይወት ማለፍ ምክንያት የነበረውን ውጥረት ስለምናነሳው ጉዳይ መጀመሪያ ብናስታውስ ጠቃሚ ይሆናል። በምርጫ ሃላፊዎች ላይ ያነጣጠረ የዛቻ ንግግርና ጥቃት በሃገሪቷ ውስጥ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ እንቅፋት ሆኖ የነበረ መሆኑም ውጥረቱን እንዴት አባብሶት እንደነበርም በተመሳሳይ የማይዘነጋ ነው። ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያት አሸናፊ መሆነቸውን ካወጀ በኋላ በተነሱ ግጭቶች ከ70 በላይ ሰዎች ህይወታቸውንአጥተዋል። የአሜሪካ አምባሳደር ቦብ ጎዴግ የ20 ሃገራትን ልዑካን ወክለው ባደረጉት ንግግር ‘ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ ይቀላል። ይህም አደገኛ ነው። መቆም አለበት’ ሲሉ አሳስበው የነበረ መሆኑም ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ ታዲያ የውጪ ሃገራት ልዑካን በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ኬንያን ርቀዋት ከህይወት ባሻገር ለሆነ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ዳርገዋታል። ዋነኛ የሆነው የቱሪዝም ፍሰቷ ላሽቆ የውጭ ምንዛሬ ያለህ አስብሏታል፤ ትመራው የነበረውንም ኢኮኖሚ ለኛይቱ ሃገር ታስረክብ ዘንድ ግድ ሆኖባታል። ከርሷ መማር የተሳነን እኛ ደግሞ ወደነበርንበት ለመመለስ እየዳከርን መሆኑ ነው እንግዲህ አሳሳቢው ጉዳይ።

 

ስታንዳርድ ሚዲያ የተሰኘው ድረ-ገጽ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የፈጣን ኢኮኖሚ እድገቷን ሪከርድ በሆነ የ7.1 በመቶ የጂዲፒ እድገት አስጠብቃ መጓዝ መቻሏን በእንግሊዝ እና ዌልስ መቀመጫውን ያደረገው ኢንስትዩት ኦፍ ቻርተር አካውንታትስ ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ ባሰፈረው ሰሞንኛ ዘገባው፤ ባለፉት አራት ወራት የኬንያ ጂዲፒ 4.6 በመቶ እድገት ቢያሳይም ከኢትዮጵያ አንጻር ሲለካ ግን ኢትዮጵያ የ7.1 መጠነ ሰፊ የሆነ የእድገት እምርታ ማስመዝገቧን እና የኬንያ ወደኋላ መመለሱን አረጋግጧል። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የፈጣን ኢኮኖሚ እድገትን በሰፊ ልዩነት መምራት መቻሏንም አመላክቶ፤ ባለፉት የመጨረሻ ሩብ አመታት ኢትዮጵያ ለቀጠናው ዋንኛ የኢኮኖሚ እድገት ባለድርሻ መሆኗን የድርጅቱ ሪፖርት ማስቀመጡን ድረገጹ አስታውቋል። ሁለቱ ሀገራት ይህን እድገት ማስመዝገብ የቻሉት በረጅም ጊዜ ድርቅ በተጠቁበት እና በምርጫ ውዝግብ ባሉበት ወቅት ነው ሲል ሪፖርቱ  ማስታወሱ የሚነግረን መልእክት የፖለቲካውን ሁኔታ ካላስተካከልን የኬንያ እጣ ፈንታ የሚገጥመን መሆኑን ነው።  

 

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በዜጎች መካከል የሚፈጠሩ መጠነኛ ግጭቶች ወደ ለየለት ብጥብጥና ግርግር በማምራት፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት እያስከተሉና በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ የሽግግር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ እንቅፋት ሲፈጥሩ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።   በሒደትም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በሕዝቡ ላይ ውጥረት ማንገሳቸውና ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንቅስቃሴ ማወኩ ተጠቃሽ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎችም ይፋ የወጣና በድብቅ የሚከናወን የፖለቲካ ትግል ይህን ውጥረት እንዳባባሰው ብዙዎች ይስማማሉ።  አሁን ባለው ሁኔታ እንኳንስ የውጮቹ ኢንቨስተሮች ቀርቶ የሃገር ውስጡ ተራ ነዋሪ አልፈራሁም ካለ እርሱ ውሸታም ነው።

 

ባልጠበቅነውና ባላሰብነው ሁኔታ የሰው ሕይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ መሆኑን ስናይ ሁላችንም ሰግተናል። ከዚህ ቀደም የነበሩት ችግሮች በፓርቲዎች ወይም በመንግሥት የሚወሰኑ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ብዙም አስጊ አልነበሩም። የአሁኑን ችግር የከፋና አሥጊ የሚያደርገው በሕዝቡ መካከልም መቆራቆዝ የተጀመረ በመሆኑ ነው።

 

በእርግጥ አገሪቱ የተለያዩ የመሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት በዕድገት ጎዳና ላይ ነች። በዕድገት ውስጥ ደግሞ ግጭት ተፈጥሯዊ ነው። ፍላጎት በበዛ ቁጥር ግጭት አይቀሬ ነው። ያም ሆኖ ግን ግጭቶቹ  በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በብሔረሰቦች፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች፣ በከተማና በገጠር ነዋሪዎች፣ ባላቸውና በሌላቸው፣ አዋቂ በሆኑና ባልሆኑ ሰዎች፣ እንዲሁም በሃይማኖቶች መካከል ሲሆን አስደንጋጭ ነው። ኬንያን ብዙ ሃብት አሳጥቶ ወደኋላ ያስቀራት ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ መሆኑ ሊያስጨንቀው ይገባው የነበረ ህዝብ የኔ ወይም የእርሱ ጎሳ በሚል የምርጫ ውጤቱንም ሆነ ሂደቱን በጎሳ መነጽር መመልከቱ ነው። የውጭ ኢንቨስትመንት ደግሞ ጎሳ ምንም ነገሩ አይደለም። ሰላምን ብቻ ነው የሚሻው። የምንቀናበት ያጣን ይመስል እኛም በኬንያ መንገድ የቀናን ይመስላል።

 

ሃገሪቱን ወደ ብጥብጥ ለመግፋት የሚደረጉ አሳዛኝ ጥረቶች በስፋት እየተስተዋሉ ነው። መነሻቸውም መድረሻቸውም የሕዝብ አጀንዳ ባልሆኑ ምክንያቶች ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ የተሠለፉ ኃይሎች ብሄርና ጎሳን ከፊት አስቀድመው እየተናጩ ነው። ለመንግሥት ሥልጣን ከሚደረገው ሽኩቻ ጀምሮ ብሔርተኝነትን በማራገብ፣ የሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመናድ እየተደረገ ያለው ጥረት ከከፈልነው የህይወት ዋጋ በላይ በደህና መንገድ ላይ ያለውን ልማትና የውጭ ኢንቨስትመንት ወደኋላ የመመለስ  አዝማሚያ እያሳየ ነው።

 

ከዚህ ቀደም የነበሩ አላስፈላጊ ጭቅጭቆች፣ የመብት ረገጣዎች፣ በቂምና በበቀል የተጀቦኑ ጥላቻዎችና ጨለምተኛ አስተሳሰቦች አደባባይ ወጥተው እንኳንስ የውጮቹን እኛንም እያስጨነቁ ነው። በዚህ መሠረት ሁሉም ወገን አደብ ገዝቶ መነጋገር ወይም መደራደር ካልተቻለ ግን አገር ወደ ብጥብጥ ታመራለች በማለት እየሰጋ ያለው ዜጋ ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ሁሉም ጎራ ለይቶ የብጥብጡ ተዋናይ ሲሆን ደግሞ የውጭ ሃይሎች ያላቸውን ይዘው ውልቅ ይሉልናል።

 

የኢትዮጵያ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ በአስተዋይነቱና በአርቆ አሳቢነቱ ሳቢያ እርስ በርሱ ከመደጋገፍ በላይ፣ የሚወዳት አገሩ ክፉ እንዳይነካት ሲል በርካታ ችግሮችን በስሙ ከሚነግዱበት ጀምሮ በአጉል ተስፋ እስከሚቀልዱበት ድረስ ከሚፈለገው በላይ ታግሷቸዋል። ይህ ጨዋ ሕዝብ ውሸትን የሚፀየፍ፣ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በፍፁም የማይቀበል፣ በአገሩ ህልውና የማይደራደር፣ ያለችውን ትንሽ ነገር ከወገኖቹ ጋር የሚካፈል፣ ህሊናውን የሚኮሰኩሱ ነገሮችን አጠገቡ የማያስደርስ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደ ባህሉ በሽምግልና የሚፈታ፣ ለሰላም ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ቢሆንም፤ ይህን እሴት የሚገዳደሩ አጀንዳዎች አሁን እየተረጩበት ነው።  በዚህ ደግሞ ውድ የሆነውን ህይወት ከመክፈል ባሻገር ከላይ በተመለከተው መልኩ የተመሰከረለት ኢኮኖሚን መቀመቅ ይከተዋል።

 

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እስካሁን ያሳየውን እድገት ጠብቆ ሁሉን አቀፍ እና የተጠቃሚነት እድሎችን እያረጋገጠ ሊሄድ ይገባዋል ሲሉ አስተያታቸውን መስጠታቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች ማስታወስም ጠቃሚ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ እድገቱን ሊያጠናክሩ የሚያስችሉ አካሄዶችን በመከተል  የእድገቱን ቀጣይነት ሊያረጋግጥ ይገባዋል ሲሉ ማሳሰባቸውም እነዚህን እና ግጭትን የተመለከቱ ጉዳዮችን ታሳቢ አድርገው እንደሆነም ለመገመት አይከብድም።

 

ከሰሞኑ እንኳን ኢትዮጵያ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በገቢ ግብር፣ በገቢ እና በወጪ ምርቶች ቀረጥ በመሳሰሉ ጉዳዮች ሰፊ ማበረታቻዎችን እየሰጠች የምትገኝ በመሆኑ የህንድ ባለሃብቶች እድሉን በመጠቀም ሃብታቸውን በኢትዮጵያ በማፍሰስ እንዲሰማሩ በህንድ ቤንጋሊ ግዛት በተካሄደው የህንድ ባለሃብቶች ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቀዳሚ ንግድ አታሼ አቶ ሞላልኝ አስፋው መጠየቃቸውን ዘ ታይም ኦፍ ኢንዲያ በዘገባው አመላክቷል። ግን ደግሞ እኒህ ባለሃብቶች ከላይ ከተመለከቱት ማበረታቻዎች ባሻገር ይልቁንም ከሁሉም በላይ ሰላምን መሻታቸው አያጠያይቅም።

 

ስለሆነም አገሪቱ ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥታ በሕዝቦቿ ሙሉ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማቆም ሂደት ላይ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ሰአት ከላይ በተመለከተው መልኩ እየተስተዋሉ የሚገኙት መናጨቶች በህዝብ ተሳትፎ ሊቆሙ ይገባል። ያለፉት ሁለት ዓመታት ግጭቶች መብረድ አቅቷቸው አሁንም የዜጎች ሕይወት እየጠፋ፣ አካላቸው እየጎደለ ነው። በዚህ ምክንያት በየቦታው ሰላም እየደፈረሰ አገሪቱ በየቀኑ ከድጡ ወደ ማጡ እየተንሸራተተች  ለሌላኛው የውጭ ኢንቨስትመንት ተጽእኖ ተጋላጭ ከመሆኗ በፊት እንደ ብልህ ከኬንያ ትርፍና ኪሳራ ልንማር ይገባል።  

 

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በየጊዜው ‹ጥልቅ ተሃድሶ› እያለ በሩን ዘግቶ በርካታ ማንነትን መሠረት ካደረጉ ጥያቄዎች ጀምሮ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ጉዳዮች ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች በመንግስት በኩል ፈጣን ምላሽ መስጠትም ተገቢ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና በመዝናኛዎች በግለሰቦች ጠብ የሚጀመሩ ግጭቶች ወደ ብሔር እየተቀየሩ ሕይወት እየጠፋ መሆኑ ተስተውሏል። ለተቃውሞ የሚወጡ ወጣቶች መንገድ ሲዘጉ ግጭት እየተፈጠረ የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ እየተቀጠፈ፤ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው መንቀሳቀስ አስፈሪ እየሆነ ነው። ሕዝብ እየተሳቀቀ ነው። እኛው በእኛው እንዲህ ከሆንን ደግሞ የኢኮኖሚያችን አውታር የሆነው የውጭ ኢንቨስትመንት ምን ሊሆን እንደሚችል ከጎረቤት ኬኒያ ተምረን፤ ለሀገራችን ሰላምና ለህዝቦች ደህንነት ሁላችንም የየድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።